የኦሮሚያው የሰላም ድርድር
ሰኞ፣ ሐምሌ 29 2016
ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ ዙሪያ ማብራሪያ ስሰጡ ከሰላምና ፀጥታ ጋር በተያያዘ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ከሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ሃይሎች ጋር ድርድር መጀመሩን አረጋግጠዋል፡፡
በተለይም ከሁለት የድርድር ምዕራፎች በኋላ የተቋረጠው የኦሮሚያውን ግጭት በሰላም የመቋጨት ውጥኑ ይፋ የተደረገው በክልሉ ባሁን ወቅት እገታን ጨምሮ በርካታ የፀጥታ ተግዳሮትና ደምመፋሰሱ በቀጠለበት ነው፡፡
አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ የክልሉን ፖለቲካዊ ሁናቴ በቅርበት የሚከታተሉ አስተያየት ሰጪዎች ነገሩ አዲስ ባለመሆኑ ሁነኛ ቁርጠኝነት የሚስፈልገው ነው ይላሉ፡፡
“አሁን እኮ ዓለም ለልማት ስትጣደፍ እኛ ያለንን በማውደም ተጠምደናል፡፡ ንብረትም ህይወትም እየጠፋ ስለሆነ በእውነት ላይ የተመሰረተ እርቅ የሚስፈልገን አሁን ነው፡፡” ይህን ያሉት በአሮሞ ማህበረሰብ ውስጥ እጅግ አንጋፋ የሚባለውን የመጫ እና ቱለማ ማህበርን የሚመሩትና በክልሉ ፖለቲካዊ ሁናቴ ክፉ-ደጉን ያሳለፉት አቶ ድሪቢ ደምሴ ናቸው፡፡
አቶ ድሪቢ ሰሞነኛውን የኦሮሚያ ክልል የሰላም ጥሪ እና የጠቅላይ መሚኒስትሩ የሰላም ድርድር ጅማሮ ይፋ መሆኑን በማስመልከት ይህን አክለውም “ንግግሩ ለኦሮሞ ህዝብ ብሎም ለመላው ኢትዮጵያ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ነገር ግን የጎላ ግልጽነት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በፊት ድርድሩ ለምን ተቋረጠ የሚለውም በግልጽ መነገር አለበት፡፡ ግልጽነት ሰፍኖ ያጠፋውም አጥፍቻለሁ ብሎ እርቅ ቢወርድ ኢኮኖሚው ይሻሻላል፡፡ ጤናው፣ ትምህርቱ እንዲሁም ምርቱ ይሻሻላል፡፡ ተፋላሚ ሃይሎች መሃል መንገድ ላይ መገናኘት አለባቸው” ብለዋል፡፡
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ከፍተኛ ባለስልጣኑ አቶ ሙላቱ ገመቹ በፊናቸው ተፋላሚ ሃይሎቹ ካለፉት የድርድር ምእራፎች ሊማሩ የሚገባው ነጥብ አለ ይላሉ፡፡ “ለእርቅ መንገድ የሚከፍቱ አንደኛው ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ማጠናከር ነው፡፡ በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ የፖለቲካ ድርጅቶችን እያሳደዱ ጫካ ካለው ጋር ሰላም ላይ መድረስ ያዳግታል፡፡ በፖለቲካ ጉዳይ የታሰሩ ፖለቲከኞችንም መፍታ ያስፈልጋል” ነው ያሉት፡፡
አቶ ድሪቢ ደምሴ በፊናቸው እንዳብራሩት መንግስት ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጋር ለማደደረግ ያቀደው የሰላም ድርድር ለክልሉ ሰላም መደላድል ብሆንም ብቻውን ግን ዘላቂ እልባት አይሆንም፡፡ “ድርድሩ ትልቅ መፍቻ ቁልፍ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን በሂደት አጠቃላይ ኦሮሞ የሆነም ኦሮሞ ያልሆነም በሰላም ድርድር ምእራፎች ላይ ሊሳተፍ ገባል” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ በፊት በኦሮሚያ ክልል ለአምስት ዓመታት ገደማ በትጥቅ ከሚወጋው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጋር በታንዛንያ በሁለት ምዕራፎች ያደረገው የድድር ጥረቶች በዝርዝር ባልተነገሩ ምክንያቶች መክሸፉ ይታወሳል፡፡
ስዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር