1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ያልሰመረው የመንግስት እና የኦነግ-ኦነሰ ድርድር

ረቡዕ፣ ኅዳር 12 2016

መንግሥት «ሸኔ» በሚል በአሸባሪነት በፈረጀው ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን እና በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት መካከል ታንዛንያ - ዳሬሰላም ሲካሄድ የቆየው «ንግግር» አለያም «ውይይት» ያለስምምነት መጠናቀቁን ሁለቱም ተደራዳሪ አካላት በተናጥል ባወጡት መግለጫ ዐሳውቀዋል።

https://p.dw.com/p/4ZKC8
የዳር ኤ ሳላም ከተማ ከፊል ገጽታ፤ ታንዛኒያ
ያልሰመረው የመንግስት እና የኦነግ-ኦነሰ ድርድር የተካሄደባት የዳር ኤ ሳላም ከተማ ከፊል ገጽታ። ፎቶ ከማኅደርምስል Ericky Boniphace/AFP/Getty Images

የከሸፈው ምሥጢራዊ ንግግር

መንግሥት «ሸኔ» በሚል በአሸባሪነት በፈረጀው ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን እና በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት መካከል ታንዛንያ - ዳሬሰላም ሲካሄድ የቆየው «ንግግር» አለያም «ውይይት» ያለስምምነት መጠናቀቁን ሁለቱም ተደራዳሪ አካላት በተናጥል ባወጡት መግለጫ ዐሳውቀዋል። ይህ በሁለቱ ተፋላሚዎች መካከል ለሁለት ሳምንታት ገደማ ምሥጢራዊ ሆኖ የዘለቀው ድርድር በስኬት ባለመጠናቀቁም አንዱ አካል ሌላኛውን እየወቀሰ ነው ። የድርድሩ ይዘት እና ዝርዝር ነጥቦች አሁንም በምሥጢር ተይዘው እንደቆዩ ነው ። መንግሥት በስተመጨረሻ ንግግሩ «ያለ ውጤት ተቋጭቷል» ሲል በይፋ ከመናገሩ በፊት በድርድሩ ላይ መሳተፉ የተነገረው እንኳን ለመንግሥት እና ለታጣቂ ቡድኑ ቅርበት ባላቸው የመገናኛ አውታሮች ነበር ። ድርድሩ መክሸፉን ተከትሎ ጉዳዩን በተለየ አንክሮ ሲከታተሉ የቆዩ የተለያዩ አካላት አስተያየታቸውንም እየሰጡ ይገኛሉ ። 

በኦነግ-ኦነሰ (የኦሮሞ ነጻነት ግንባር - ኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት) እና በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት መካከል ታንዛንያ - ዳሬሰላም ሲካሄድ የቆየው የሰላም ድርድር ያለስምምነት መጠናቀቁን ሁለቱም ተደራዳሪ አካላት በተናጥል ባወጡት መግለጫ አሳውቀዋል፡፡  በኅብረተሰቡ ዘንድ ሰላምን ያመጣል በሚል ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ይህ ለሁለት ሳምንታት ገደማ የዘለቀው የሰላም ድርድርታንዛንያ በስኬት ባለመጠናቀቁም አንዱ አካል ሌላኛውን እየወቀሰ ነው፡፡

ስላልሰመረው ስምምነት የመንግስት አቋም

ለ15 ቀናት ገደማ በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲካሄድ የነበረው የሁለቱ ተፋላሚ ቡድኖች የሰላም ስምምነት ድርድሩ አለመሳካቱን አስቀድሞ የገለጹት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የደህንነት ጉዳዮች አማካሪ እና የሰላም ድርድሩ የመንግስት ተወካይ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ናቸው፡፡ «በሁለት ዙር ከሸኔ ጋር ስናደርግ የነበረው ውይይት ያለ ስምምነት ተጠናቋል» በሚል በይፋዊ የማኅበራዊ ገጻቸው የገለጹት አምባሳደር ሬድዋን የፌዴራል መንግስት በኦሮሚያ በተለያዩ አከባቢዎች ሲካሄድ በነበረው ጦርነት ሲደርስ የነበረውን ቀውስና እንግልት ለማብቃት ቁርጠኛ ነበር ብለዋል፡፡ ይሁንና «በሌላኛው ወገን ግትርነት» ውይይቱ ያለ ስምምነት መጠናቀቁን ነው ያስረዱት። ይህ ለሁለት ሳምንታት ለተጠጋ ጊዜ በታንዛንያ ሲካሄድ የነበረው የሁለተኛ ዙር የሰላም ስምምነት ጥረቱ የኦነግ-ኦነሰ ከፍተኛ አመራሮች እና የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትን በማሳተፍ ነበር ሲካሄድ የቆየው፡፡ 

የነቀምት ከተማ ከፊል ገጽታ
ኦሮሚያ ክልል፤ የነቀምት ከተማ ከፊል ገጽታ ። ፎቶ ከማኅደርምስል Negasa Desalegn/DW

የኦነግ-ኦነሰ አስተያየት በተደናቀፈው ስምምነት

አምባሳደር ሬድዋን ከዚህ ካልተሳካው ድርድር በኋላ በጽሑፍ ባወጡት መግለጫ፤ «ሌላኛው ወገን (ኦነግ-ኦነሰ) በፈጠረው እንቅፋት እና በሚያራምደው እውን ሊሆን በማይችለው ፍላጎት ምክንያት ስምምነቱ አልሰመረም» ነው ያሉት፡፡ አክለውም መንግስት ያሉትን ፍላጎቶች በማገናዘብ በሁለቱም ወገኖች ተቀባይነት ሊኖራቸው የሚችለውን የመፍትሄ አካል ሲፈልግ ነበርም ብለዋል፡፡
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ሸኔ) በፊናው «በታንዛንያ ዛንዚባር እና ዳሬሰላም ውስጥ ሲካሄድ በነበረው ሁለት ዙር የሰላም ስምምነት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ ለውጥ እንዲመጣ ያቀረብነውን ሐሳብ መንግስት ባለመቀበሉ» ድርድሩ ሳይሳካ ቀርቷል ብሏል፡፡ ኦነግ-ኦነሰ «የኢትዮጵያ መንግስት ፍላጎት የኦነሰ አመራሮችን ከመቀላቀል ባሻገር መሰረታዊውን የአገሪቱን የሠላምና ፖለቲካ ችግሮችን ከመፍታት የራቀ» ነው ብሏልም፡፡ 

በስምምነቱ አለመሳካት የመንግስት ቀጣይ አቅጣጫ

በምስራቅ አፍሪቃ በይነ-መንግስታት (IGAD)፣ በአሜሪካ፣ ኖርዌይ እና ኬንያ መንግስታት አሸማጋይነት ሲካሄድ የነበረው ይህ ድርድር ጥረቱ መክሸፉን ተከትሎ  የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴርም ትናንት አመሻሹን ባወጣው ይፋዊ መግለጫ፤ «መንግስት በአገሪቱ ሰላም ሰፍኖ ኢትዮጵያ ያሏትን ጸጋዎች ወደ ተጨባጭ ሀብትና አቅም ቀይራ ብልጽግናዋን ታረጋግጣለች የሚል ተስፋ ተይዞ ከግማሽ መንገድ በላይ ተሂዶ ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት» መሞከሩን በመግለጽ፤ «የሽብር ቡድን» ያለው ሌላኛው ወገን ባለመቀበሉ ውይይቱ ያለ ውጤት ተበትኗል ነው ብሏል።  የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት በመግለጫው «መንግስት በሰላማዊ መፍትሄው ላይ ያለው አቋም እንደተጠበቀ ሆኖ ሕግና ሕገመንግስታዊ ስርዓቱን የማስከበር ተልእኮው ይቀጥላልም» ብሏል፡፡ 
ያለውጤት ተጠናቀቀ ስለተባለው ድርድር ዶቼ ቬለ ከሁለቱም ተደራዳሪ ቡድኖች ተጨማሪ ዝርዝር መረጃዎችን ለማግኘት ያደረገው ጥረት ግን ለጊዜው አልሰመረም፡፡  

በስምምነቱ ያለውጤት መጠናቀቅ የተሰጡ አስተያየቶች

ድርድሩ ከሸፈ መባሉን ተከትሎም ጉዳዩን በተለየ አንክሮ ሲከታተሉ የቆዩ የተለያዩ አካላት አስተያየታቸውንም እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ በኦሮሚያ ከፍተኛ ተደማጭነት ያለው የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ ከፍተኛ አመራር አቶ ሙላቱ ገመቹ ሰላም ያመጣል በሚል ተስፋ የተጣለበት የስምምነቱ ጥረት አለመሳካቱ፤ ለሁሉም ወገን የማይበጅ ብለውታል፡፡ «እንግዲህ የሰላም አለመውረዱ ለመንግስትም ሆነ ለተፋላሚው እንዲሁም ለህዝቡ የሚበጅ አይደለም» ያሉት ፖለቲከኛ ሙላቱ በሁለቱ ወገኖች የቀረቡ የስምምነት ሂደቱ ግልጽ ሃሳቦች ለህዝብ ባይቀርቡም ዞሮ ዞሮ የኦሮሞን መሰረታዊ ጥያቄ ዘላቂ ሰላም አያመጣም ነው ያሉት፡፡ «ሥልጣን ላይ ላለው አካል እጅ ሰጥቶ፤ የተወሰኑ አመራር ገብተው ከዚያ በኋላ ነገሮች ወደ ነበሩበት ቦታ እንዳይመለሱ የእኛ ሥጋት ነበር» ብለዋል ፖለቲከኛው። ይህ ሳይደረግ ቀርቶ ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ መፍረሱ ነገሮች በነበሩ ይዞታቸው እንዲቀጥሉ የሚል መልእክት እንዳለውም በአስተያየታቸው አስረድተዋል፡፡  

የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ የድርድሩ ያለስምምነት መቋጨት ተከትሎ «ትልቅ ሐዘን ተሰምቶኛል» ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ጽፈዋል፡፡ በዳሬሰላም ሲካሄድ የነበረው ውይይት የጠፋውን ባይመልስም ወደፊት ጥፋቶችን ለማስቀረት ትልቅ ተስፋ ነበር ያሉት አቶ ታዬ፤ የስምምነቱ ጥረት መክሸፉ ትልቅ ሀዘን ከመሆኑም ባሻገር የነበረው ስቃይና ችግር እንዳለ ይቀጥል እንደማለት ነው ሲሉም አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡  

የኦሮሚያ ክልል  መልክዐምድር
የኦሮሚያ ክልል መልክዐምድር ከፊል ገጽታ ። ፎቶ ከማኅደር

ሌላው አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት ሊቀመንበር አቶ ደስታ ዲንቃ በድርድሩ የሆነው የተጠበቀው አይደለምብለዋል፡፡ «ሁላችንም ከድርድሩ የሰላም አየር እንድንናፈስ ያደርገናል ያልነውን ውጤት ነበር የጠበቅነው» ያሉት አቶ ደስታ በተጠበቀው መንገድ ድርድሩ አለመቋጨቱ ተደራዳሪዎች እርስ በርሳቸው ጠንካራ ጥያቄዎችን ማንሳታቸውን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡ ተቀናቃኞቹ በድርድር ላይም ሆነው ጦርነት ስካሄድ ነበር ያሉት ፖለቲከኛ ደስታ አሁንም ከሁለቱ ወገኖች መግለጫ መረዳት የሚቻለው ጦርነቱ እንደሚቀጥል ነው ብለዋልም፡፡

አቶ ደስታ አክለውም በዚህ የድርድር ውጤት ተስፋ መቁረጥ ግን አይገባል ይላሉ፡፡ «የሰላም ስምምነቱ ለሁለተኛ ጊዜ ያለስኬት ተጠናቀቀ ማለት ሁለቱ ወገኖች ዳግም ወደዚያ አይገቡም ማለት አይደለም፡፡ አደራዳሪዎችም እጃቸውን አጣጥፈው ገብተው ይቀመጣሉ የሚል ግምት የለም፡፡ ሕዝብና አገርን ማዕከል ያደረገ ድርድር ይቀጥላል ተብሎ ይታመናል፡ ሕዝባችንም ተስፋ ሳይቆርጥ ግፊት ማድረግ አለበት» ሲሉም አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡  

አምባሳደር ሬድዋን ቀደም ብለው ባወጡት መግለጫ በስምምነቱ ያለስኬት መጠናቀቅ ላይ መጸጸታቸውን ገለጸው ውይይቱ እንዲደረግ ላስተባበሩ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡ 
የኦነግ-ኦነሰ ከፍተኛ አዛዥ ኩምሳ ድሪባ (ጃል መሮ)  በዚህ ስምምነት ላይ በአካል መሳተፋቸውን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች የአሁኑ የሰላም ድርድር በስኬት ይጠናቀቃል በሚል በበርካቶች ተጠብቆ  ነበር፡፡ ጃልመሮ ከሰሞኑ በዙም በኩል ውጭ  አገር ለሚገኙ ደጋፊዎቻቸው ባስተላለፉት መልእክት «ኦሮሞ በተግባር መደራጀት ይኖርበታል» ማለታቸውም ይታወሳል፡፡ 

የኢትዮጵያ መንግስት እና የኦነግ-ኦነሰ በኦሮሚያ በተለያዩ አከባቢዎች የሚያደርጉትን ጦርነት ለመቋጨት ከስድስት ወራት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ በታንዛንያ ዛንዚባር ወደብ ያደረጉትን ውይይት በመረዳዳት ስሜት እና ለቀጣይ ስምምነት በር ከፋች በሆነ አኳኋን ስምምነቱን ማጠናቀቃቸውን በተናጥል መግለጫቸው አሳውቀው ነበር፡፡

 ሥዩም ጌቱ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር