1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእንቅልፍ መዛባትና እጦት

ማክሰኞ፣ ግንቦት 6 2016

በቂ እንቅልፍ ይተኛሉ? በቂ የሚባለው የእንቅልፍ መጠን ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ መለወጡ ተፈጥሯዊ ነውና እጅግ አያሳስብም ይሆናል። ያለምንም በቂ ምክንያት በተደጋጋሚ እንቅልፍ የሚያጡ ከሆነ ግን የሀኪም እርዳታ ሳያስፈልግዎ አይቀርም። ስለእንቅልፍ ማጣት መንስኤ ከአድማጭ ለተላከ ጥያቄ የባለሙያ ማብራሪያ እነሆ።

https://p.dw.com/p/4fqjd
ፎቶ ከማኅደር፤ የእንቅልፍ እጦት
ለረዥም ጊዜያት የሚዘልቅ ተደጋጋሚ የእንቅልፍ እጦት የጤና ችግር አመላካች ሊሆን እንደሚችል ነው የህክምና ባለሙያዎች የሚጠቁሙት። ፎቶ ከማኅደር፤ የእንቅልፍ እጦት ምስል Colourbox

የእንቅልፍ መዛባትና እጦት

እንቅልፍ በዐይንዎ ሳይዞር አድረው ያውቃሉ? እርግጥ ነው አንዳንዴ እቅልፍ አልባ ሌሊት ሊያሳልፉ ይችላሉ። እንቅልፍዎ በቀጣይ ቀናት የሚካካስ ከሆነ ሃሳብ አይግባዎ። ሆኖም በሳምንት ውስጥ ለሦስት ቀናት ብሎም ለወራት ከተደጋገመ ግን የአእምሮ ሀኪም ማማከር እንደሚበጅ የህክምና ባለሙያዎቹ ይመክራሉ። 

አድማጫችን የመቶ አለቃ ውቤ ታሪኩ፤ ከሳምንታት በፊት የላኩልን ጥያቄ እንዲህ የሚል ነው፤ ዛሬ እንቅልፍ የሚባል ነገር በአይኔ ሳይዞር አደርኩ ።የሌሊቱ እርዝማኔ አይጣል ነው። ነግቶ ከሰው እስከምገናኝ ቸኮልኩ። ጭንቅላቴን ወጥሮ ይዞኛል። እጅና እግሬን ድንዝዝ ያደርጋኛል። በአጠቃላይ ጥሩ ስሜት አይሰማኝም።  እንቅልፍ ማጣት አንዱ የጤና ችግር እንደሆነ ብረዳውም መንሴኤው ምንድን ነው የሚለውን ግን ምርምር ያደረጉ ሰዎች የሚሰጡት መልስ ይሆናልና በዚህ ዙሪያ ጥናት ያደረጉ ሰዎች ጋብዛችሁ መንሴኤውንና መፍቴተሄውን ብታሰሙኝ። ይህ ችግር ዛሬ ባሰብኝ እንጅ አልፎ አልፎ ያጋጥመኝ ነበር። ተኝቸ ስነቃ ሰውነቴ ይብረከረካል። የደስታ ስሜት አይሰማኝም። በትንሹ በትልቁ ብስጭትጭት እላለሁ። ቁጥሮችን እገድፋለሁ። ይኸ የጤናነው ይባላል?» ይላሉ። የዘወትር ተከታታያችን የመቶ አለቃ ውቤ፤ የእርስዎን ጥያቄ መነሻ መማድረግ የአእምሮህክምና ከፍተኛ ባለሙያ ለሆኑትና በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በዘርፉ የህክምናምና የማስተማር አገልግሎት በመስጠት ላይ ለሚገኙት ለዶክተር እሸቱ ቱኒሶ በዝርዝር አቅርበናል። በቅድሚያም የእንቅልፍ እጦት በሽታ ነው ማለት ይቻላል ወይ ያልናቸው ዶክተር እሸቱ የእንቅልፍ እጦት በሦስት ደረጃ ተከፍሎ ሊታይ እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።

የእንቅልፍ እጦት ደረጃዎች

ተኝተው የእንቅልፍ መቆራረጥና መዛባት የሚያጋጥማቸው ይኖራሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ ሊነጋጋ አካባቢ ነቅተው እንቅልፍ ሊያጡ ይችላሉ፤ ሌሎች ደግሞ በሣምንት ሦስት ቀናት በተከታታይ ለሦስት ወራት የእንቅፍ እጦት የሚያጋጥማቸው ሲሆኑ እነዚህኞቹ የእንቅልፍ እጦት ህመም ላይ ደርሰዋል ማለት እንደሚቻል ጠቁመዋል።

የእንቅልፍ እጦት የሰዎችን ባህሪይ እና ስሜት እንደሚረብሽና ማኅበራዊ ግንኙነታቸውም ላይ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ነው ዶክተር እሸቱ የሚናገሩት። ተማሪዎች ከሆኑ ደግሞ ለትምህርታቸው ትኩረት ያለመስጠት፤ የቤት ሥራዎችን ተከታትሎ ያለመሥራትና የመሳሰሉ እክሎችን ሊያስከትል እንደሚችልም አመልክተዋል። እንዲያም ሆኖ ዶክተር እሸቱ የእንቅልፍ እጦትን እንደበሽታ ከመውሰዳችን በፊት መለየት የሚኖርብን ነገሮች እንዳሉ ያሳስባሉ። 

ምንም አነቃቂ ቅመሞችን ሳይጠቀሙ ህመምን መድኃኒቶችም ሳይወስዱ እንቅልፍ ማጣት ሲደጋገም ከድብር እንዲሁም ከጭንቀት ጋር ሲገናኝ፤ የዘርፉ ባለሙያሀኪም የሚያደርገውን ምርመራ ውጤት ተከትሎ ችግሩ ህመም ወደመሆን መሸጋገሩ ሊረጋገጥ ይችላል። 

 

ፎቶ ከማኅደር፤ ሰዓት የሚያስፈልገው የኤሌክትሮኒክስ አጠቃቀም።
ስልክም ሆነ ኮምፕዩተር እንዲሁም ቴሌቪዝን አልጋ ላይ ሆኖ መጠቀም ለእንቅልፍ ማጣት ምክንያት ሊሆኑ ከሚችሉ ልምዶች አንዱ ነው። ፎቶ ከማኅደር፤ ሰዓት የሚያስፈልገው የኤሌክትሮኒክስ አጠቃቀም።ምስል Ute Grabowsky/photothek/picture alliance

ሰዎች እንቅልፍ ለረዥም ቀናት በተከታታይ ባይተኙ ለሕይወት ሊያሰጋ እንደሚችል ነው ባለሙያው ያመለከቱት። ምንም እንኳን በሰዎች ላይ የተሠራ ጥናት ባይኖርም በእንስሳት ላይ የተካሄደው ጥናት ይህን ማሳየቱንም አንስተዋል። በመላው ዓለም ከሦስት ሰዎች አንዱ የእንቅልፍ እጦት ችግር እንዳለበት ጥናቶች ያመለክታሉ። ይህም የእንቅልፍ እጦት ከፍተኛ ችግር መሆኑን እንደሚያመለክት ነው ዶክተር እሸቱ የገለጹት። እንዲያም ሆኖ አብዛኞቹ የእንቅልፍ ችግሮች በቀላሉ መፍትሄ ሊገኝላቸው እንደሚችል ገልጸዋል። በተለይም አነቃቂ ቅመሞች ያሉባቸውን እንደቡና፤ ሲጋራ፣ ጫት፤ ኮካኮላ እና ቸኮላት የመሳሰሉ ነገሮችን የሚያዘወትሩ ሰዎች ለእንቅልፍ መዛባት ሊጋለጡ እንደሚችሉም ነው የጠቆሙት።

መፍትሄ ይኖረው ይሆን?

የእንቅልፍ እጦት ችግር በቀላሉ በሀኪም ሊረዳና ሊስተካከል የሚችልባቸው አጋጣሚዎች እንደሚበዙ ነው ዶክተር እሸቱ ያመለከቱት። በቀዳሚነትም እንደ መፍትሄ የገለጹት የተጠቀሱትን አነቃቂ ቅመም ያላቸውን ነገሮች መጠቀም ማቆም ሲሆን፤ እንቅልፍን የሚያጠፉ የኤክትሮኒክስ አጠቃቀሞችን፤ ለምሳሌ ስልክን በመኝታ ሰአት መጠቀም፤ ኮምፕዩተርንም ሆነ ቴሌቪዥንን መመልከት አእምሮን አንቅቶ እንቅልፍን ሊያሳጣ ስለሚችል ከመኝታ ሰዓት አስቀድሞ እነዚህን መዝጋት እንደሚገባ መክረዋል። የእስፖርት እንቅስቃሴም የእንቅልፍ ይዞታን ሊያሻሽል እንደሚችል፤ ሆኖም ከመሸ መሆን እንደሌለበት ገልጸዋል። እነዚህን ጥንቃቄዎች እያደረጉ እንቅልፍ ማጣቱ የሚቀጥል ከሆነ ግን ወደአእምሮ ሀኪም ዘንድ ሄዶ በቂ ክትትል በማድረግ መፍትሄ ማግኘት እንደሚቻል አስረድተዋል። ከጤና ይዞታ አኳያ እንቅልፍ ብዙ ነገርን ጠቋሚ መሆኑን ነው ዶክተር እሸቱ ያመለከቱት። እናም ተደጋጋሚ የእንቅልፍ እጦት ሲያጋጥም ሀኪም ማማከሩ መንስኤውን ለመረዳት እንደሚረዳ ገልጸዋል። ለሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ ዶክተር እሸቱን ከልብ እናመሰግናለን።

ሸዋዬ ለገሠ 

ታምራት ዲንሳ