1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጤናዎ፤ ታካሚን ከመድሃኒትና ከሀኪም ጋር የሚያገናኘው መተግበሪያ

ሐሙስ፣ ሰኔ 16 2014

«ጤናዎ» መተግበሪያ ታካሚው የሚፈልገው መድሃኒት የሚገኝበትን የመድሃኒት ቤት የሚጠቁም ሲሆን፤ ሰዎች ባሉበት ሆነው በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው የጤና አገልግሎት መረጃዎችን የሚያገኙበትም ነው። መተግበሪያው ታካሚዎችን ከህክምና ባለሙያዎች አና በወጭ ሀገር ካሉ የጤና ተቋማት ጋር ጭምር ያገናኛል።

https://p.dw.com/p/4D59f
TENAWO-Anwendung
ምስል Privat

መተግበሪያውን ለመጠቀም ዕድል ለሌላቸው የ24 ስዓት የጥሪ ማዕከል በአማራጭነት ቀርቧል


እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የጤና አገልግሎት ስርዓት ደካማ በሆኑባቸው ሀገራት ቴክኖሎጅ የሚያደርገው እገዛ ቀላል አይደለም።ይህንን በመገንዘብ ይመስላል በቅርቡ «ጤናዎ» የተባለ ሰለ ጤና አገልገሎት መረጃ የሚሰጥ  መተግበሪያ አገልግሎት ላይ ውሏል።የዛሬው የሳይንስ አና ቴክኖሎጅ ዝግጅት ይህንን መተግበሪያ ያስተዋውቃል።
ዾክተር ሲሳይ አበበ፣ የህክምና ባለሙያ ናቸው።ለአራት አመታት ያህል በግል እና በመንግስት የህክምና ተቋማት በሙያቸው ሰርተዋል።በነዚህ በሰሩባቸው አመታት ታዲያ ታካሚዎቻቸው የታዘዘላቸውን መድሃኒት ከመድሃኒት ቤቶች ማግኘት እና መግዛት እንዳልቻሉ በተደጋጋሚ ነግረዋቸዋል።የታዘዘላቸውን የናሙና ምርመራ እንዲሁም የሚመለከተውን የጤና ባለሙያ ለማግኘትም ሲቸገሩ ተመልክተዋል። 
ይህንን የታካሚዎች ችግር በቅርበት የተመለከቱት ዶክተር ሲሳይ ታዲያ አውጥተው አውርደው ችግርሩን ይፈታል ያሉትን አንድ መላ ዘየዱ።እናም ችግሩን መነሻ አድርገው  በሀገር ውስጥ እና በውጭ  ከሚኖሩ ወዳጆቻቸው ጋር በመነጋገር የጤናውን ዘርፍ በቴክኖሎጅ መደገፍን ዓላማ ያደረገ እሳቸው በስራ አስፈፃሚነት የሚመሩት ኬ.ኤም.ኤስ ሄልዝ ትሬዲንግ  የተባለ አንድ የጤና ድርጅት መሰረቱ።

TENAWO-Anwendung
ምስል Privat

በኢትዮጵያ፣  በካናዳ፣ በእንግሊዝ በአሜሪካ በሚገኙ ትውልደ ኢትዮያዊያን  የተመሰረተው ይህ  ድርጅት፤  ህብረተሰቡን  ከእንግልት ለመታደግ  በመጀመሪያ መድኃኒቶችን የሚያፈላልግ ድረ ገጽ፣ ከዚያም «ጤናዎ» /TENAWO/ የተባለ የስልክ መተግበሪያ ቀጥሎ ደግሞ የስልክ  የጥሪ ማዕከልን ከጥቂት ወራት በፊት ለተገልጋይ ይፋ አድርጓል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ከውጭ ምንዛሬ እጥረት  ጋር ተያይዞ ከሚከሰተው የመድኃኒቶች  ዋጋ መናር ባሻገር  መድሃኒቶች ከነአካቴው መጥፋትም ሌላው ችግር መሆኑ ይነገራል።አሁን አሁን ደግሞ የጠፉ መድኃኒቶች ብቻ ሳይህን  አሉ የሚባሉትም  ቢሆን  በየትኛው መድሃኒት ቤት እንደሚገኙ ማወቅ ጊዜና ጉልበትን የሚጠይቅ ሌላው ፈታኝ ነገር ነው።የጤናዎ መተግበሪያም ከሚያቃልላቸው ችግሮች አንዱ  ይህ ነው። መተግበሪያው  ከበርካታ መድሃኒት ቤቶች ጋር ትስስር በመፍጠር እና መድኃኒቶችን በአንድ የመረጃ ቋት በማስገባት  ታካሚው የሚፈልገው  መድሃኒት የሚገኝበትን የጤና ተቋም ወይም የመድሃኒት ቤት ይጠቁማል። በዚህም ጊዜና ጉልበትን እንዲሁም የታካሚዎች እንግልት እንደሚቀንስ ዶክተር ሲሳይ ገልፀዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የጤናዎ መተግበሪያው  ሰዎች ባሉበት ሆነው ሁለገብ የጤና አገልግሎቶችን ለማግኘት የሚያስችሉ መረጃዎችን በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው  በማድረስ  አገልግሎት ፈላጊዎችን ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት  ጋር ያገናኛል።
መተግበሪያው  የበይነ መረብ ግንኙነት የሚፈልግ ሲሆን ፤ከ«አፕ ስቶር» ወይም ከ«ፕሌይ ስቶር»  በነፃ የሚጫን ነው። በቋንቋ ረገድ  ለጊዜው በአማርኛ፣ በኦሮምኛ እና በእንግሊኛ ቋንቋዎች የሚሰራ ቢሆንም፤ለወደፊቱ ግን ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን የማካተት ዕቅድ እንዳላቸው ባለሙያው ገልፀዋል።

TENAWO-Anwendung
ምስል Privat

መተግበሪያውን ለመጠቀም  ዕድል ለሌላቸው ማለትም  የስማትርት ስልክ ለሌላቸው ፣ ማንበብና መፃፍ ለማይችሉ እንዲሁም ከቴክኖሎጅ ጋር ትውውቅ ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችም 9456 የተባለ የ24 ስዓት የጥሪ ማዕከል በአማራጭነት ቀርቧል።
በጥሪ ማዕከሉ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች በርካታ ሰዎች  አገልግሎት የሚያገኙ መኖራቸውን የሚናገሩት ዶክተር ሲሳይ በዚህም  ለምርመራ እና ለህክምና የሚያስፈልጋቸውን 50 በመቶ መረጃ እንዲሁም ሙያዊ ምክር ያገኛሉ ብለዋል።ይህም ያለ አግባብ ብዙ ምርመራዎችን እንዳያደርጉ ያግዛቸል ብለዋል።
በዚህ ቴክኖሎጅ ወደ 200 ከሚጠጉ ሀኪሞች እና ከ60 በላይ ከሆኑ መድሃኒት ቤቶች ጋር ትስስር በመፍጠርም የቤትለቤት ህክምና እንዲሁም መድሃኒት ለታካሚዎች የማድረስ አገልግሎት እንደሚሰጥም አብራርተዋል።እንደ ዶክተር ሲሳይ በድረ-ገፅ፣ በመተግበሪያ እና በስልክ ጥሪ የሚሰጡት  የጤና አገልግሎቶች፤ ተቋማትም ሆኑ ግለሰቦች በነፃ የሚጠቀሙባቸው ናቸው። 
በስልክ ጥሪው  በቀን እስከ 200 መቶ ሰዎችን እናስተናግዳለን የሚሉት ባለሙያው መተግበሪያውን የሚጠቀሙና ድረ-ገፁን የሚጎበኙ ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ ነው። ባለሙያዎቹም የቴክኖሎጅውን  የመረጃ ቋት ብዛትና ጥራት ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሳደግ ይዘዋል።

TENAWO-Anwendung
ምስል Privat

በዚህም ከተጠቃሚው ሆነ ከተቋማት  የሚያገኙት ግብረ መልስም መልካም መሆኑን  ዶክተር ሲሳይ ገልፀዋል። 
በዓለም አቀፉ የጤና አገልግሎት ሽፋን  ጠቋሚ መረጃ በሥነ ተዋልዶ፣ በእናቶች ፣ በአራስ እና በሕጻናት ጤና፣ በተላላፊ  እና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ክትትል እና የህክምና ጣልቃገብነት ላይ ተመሰርቶ ባወጣው መረጃ በኢትዮጵያ  በጤና አገልግሎት አሰጣጥ ረገድ አጠቃላይ እድገት ቢታይም ፤ የጤና አገልግሎት ሽፋን ግን አሁንም ከ50 በመቶ በታች ነው።በመሆኑም የሀገሪቱን የጤና አገልግሎት ስርዓትን ለማዘመንና ሽፋኑን  ለማሳደግ ቴክኖሎጅ የሚጫወተው ሚና ቀላል አይደለም እና ጤናዎን የመሳሰሉ አጋዥ የዲጀታል ቴክኖሎጅዎች ሀገሪቱ በእጅጉ የሚያስፈልጋታል።
 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው እንዲያደመጡ እንጋበዛለነ።

 

ፀሀይ ጫኔ
ነጋሽ መሀመድ