1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሶማልያው ፕረዚደንት ወቀሳ

እሑድ፣ የካቲት 10 2016

የጉባኤው አስተናጋጅ ኢትዮጵያ ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት ለቀረበባት ወቀሳ በሰጠችው ምላሽ፣ ለአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ለሚመጡ የሀገራት መሪዎች እንደሚደረገው ሁሉ ለሶማሊያው ፕሬዝዳንትም "በሙሉ ክብር ደማቅ አቀባበል" እንደተደረገላቸው ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/4cYDL
የሶማልያው ፕረዚደንት ሐሰን ሸኽ ማሕሙድ
የሶማልያው ፕረዚደንት ሐሰን ሸኽ ማሕሙድምስል MICHELE SPATARI/AFP

የአፍሪቃ መሪዎች ውይይትና የሶማልልያው ፕረዚደንት ወቀሳ

የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የጉባኤው ግኝቶችን እና የወደፊት አቅጣጫዎችን በተመለከተ የሕብረቱ መሪዎች ዛሬ ሌሊቱን በሚሰጡት መግለጫ ይጠናቀቃል።
የትምህርትን ጉዳይ ዐቢይ የውይይት አጀንዳ ያደረገው 37 ኛው የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤበአሕጉሩ ከዓመት ዓመት ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሰ ነው የተባለውን የፀጥታ እና የደህንነት ጉዳይም ውይይት እያደረገበት እንደሆነ ተገልጿል።
በሌላ በኩል ለሕብረቱ ጉባኤ አዲስ አበባ  የገቡት የሚሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼሕ ሞሐሙድ የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ውይይቱ ወደ ሚካሄድበት ሥፍራ “እንዳልገባ ተከለከልኩ"  በሚል ትናንት ያሰሙት ክስ የተሳሳተ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል።

የፖለቲካ አለመረጋጋት ፣ ድርቅና ድህነት ብሎም የፀጥታ ችግር አሁንም አፍሪካን አላራምድ ያለ ችግርመሆኑ በትናንቱ የጉባኤው የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገለፀበት የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በዝግ የቀጠለ ሲሆን በአሕጉሩ አልቀረፍ ባለው ኢ - ሕገ መንግሥታዊ የመንግሥት ለውጦች እና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ እየመከረ ነው። ከዚህ ባለፈ መሪዎቹ በዝርዝር ስለተወያዩባቸው ጉዳዮች እስካሁን መግለጫዎች ይፋ ባለመሆናቸው የታወቀ ነገር የለም። 

የአፍሪቃ ኅብረት ስብሰባ በከፊል
የአፍሪቃ ኅብረት ስብሰባ በከፊልምስል MICHELE SPATARI/AFP

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የጉባኤው አስተናጋጅ ኢትዮጵያ ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት ለቀረበባት ወቀሳ በሰጠችው ምላሽ፣ ለአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ለሚመጡ የሀገራት መሪዎች እንደሚደረገው ሁሉ ለሶማሊያው ፕሬዝዳንትም "በሙሉ ክብር ደማቅ አቀባበል" እንደተደረገላቸው ገልጻለች።

ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼሕ ሞሐሙድ ትናንት በአፍሪካ ሕብረት ግቢ ውስጥ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረሙትን የመግባቢያ ስምምነት ተቃውመው ድርጊቱን ኮንነዋል። አያይዘውም  የመሪዎች ጉባኤ ወደ ሚካሄድበት ስፍራ እንዳይገቡ በኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ክልከላ ለማድረግ ሙከራ እንደተደረገባቸው ገልፀዋል።

የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድርጊቱ የዲፕሎማሲ እና ዓለም አቀፍ ደንብን የሚጥስ እና የአፍሪካ ሕብረትን ነባር ባሕል የሚቃረን መሆኑንም ገልጾ ክስተቱ ምርመራ እንዲደረግበት ጠይቋል።
"ዛሬ ጥዋት ከሆቴል መጥቼ በጉባኤው ዝግ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ስዘጋጅ የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይላት መንገዴን ዘግተውብኛል። ከሆቴል ወጥቼ በመኪናዬ ወደ ስብሰባው ለመምጣት አልቻልኩም። እዚያው በመቆየት ብዙ ጊዜ ፈጅቶብኛል። መጨረሻ ላይ የሌላ ፕሬዝዳንት መኪና ይዤ መጥቻለሁ። እንደገና የጅቡቲ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት እና እኔ ወደ የአፍሪካ ህብረት ዋና መሥሪያ ዋና ጽሕፈት ቤት ስንደርስ እንዳንገባ ተከለከልን።"
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች መንገድ ዘግተው ካረፉበት ሆቴል እንዳልወጣ አድርገዋል፣ ጠመንጃ የታጠቁ ወታደሮች ወደ ሕብረቱ ግቢ እንዳልገባ አግደውን ነበር ቢሉም የኢትዮጵያ መንግሥት ክሱ ትክክል እንዳልሆነ ገልጿል። ኢትዮጵያ አስተናጋጅ ሀገር እንደመሆኗ ለእንግዶቹ ደኅንነት ግዴታ ያለበት መሆኑንም መንግሥት አስታውቋል።

የሶማሊያ ተወካዮች በመንግሥት የተመደበላቸውን የፀጥታ ሰራተኞች አንቀበልም ማለታቸውንና ጠባቂዎቻቸው የጦር መሣሪያ እንደታጠቁ ወደ ሕብረት ቅጥር ለመግባት ሞክረው በተቋሙ የፀጥታ ኃይላት መከልከላቸውን እና የኢትዮጵያ መንግሥት የተባለውን ክልከላ አለማድረጉንም ገልጿል።
በዝግ የቀጠለው 37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ከጥቂት ሠዓታት በኋል የሕብረቱ የፖለቲካ ፣ የሠላም እና ደኅንነት ኮሚሽን ስለ አህጉሩ አጠቃላይ የሰላምና ደህንነት ሁኔታ እንዲሁም እኩለ ሌሊት ገደማ አዲስ ተመራጩ የሕብረቱ ሊቀመንበር እና የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር አጠቃላይ በጉባኤው ስለተገኘው ውጤት እና የወደፊት አቅጣጫ በሚሰጡት መግለጫ ይጠናቀቃል።
ሰሎሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር