1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ አንድነት ድርጅትና ሕብረት ረጅም ጉዞ

ሰኞ፣ ሐምሌ 4 2014

የቀድሞዉን የአፍሪቃ አንድነት ድርጅትንም ሆነ የኋላዉን የአፍሪቃ ሕብረትን አንዳዶች ከማቀድ ማዉራት ባለፍ ለአሐጉሪቱ ሕዝብ ምንም የማይሰራ የወሬ ሱቅ ይሉታል።ሌሎች የአፍሪቃ መሪዎች መነታረኪያም-መሞጋገሺም መዝናኛም ያደርጉታል።ጥርስ ጥፍር የለሽ ማሕበር ባዮችም ብዙ ናቸዉ።አምባሳደር ተፈራ ሻዉል ግን ወቀሳ፣ትችት ስድቡን ይቃወማሉ።

https://p.dw.com/p/4DyUy
Bildergalerie 50-jähriges Jubiläum der Afrikanischen Union AU
ምስል STR/AFP/Getty Images

የአፍሪቃ አንድነት ድርጅትም ሆነ ሕብረት ከትችት ወቀሳ አልዳነም

 

ለብዙ ምዕተ-ዓመታት የፀና የመንግስት ሥርዓት መስራቺቱ፣ነፃይቱ፣ የራስዋ ፊደል፣ ባሕል፣ ቋንቋ ተጠቃሚይቱ አፍሪቃዊት ሐገር አንድ ነበረች።ኢትዮጵያ።በ1847 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ላይቤሪያ ተጨመረች።በ1957 ጋና ነፃ ወጣች።ሶስት ሆኑ።በስድስተኛዉ ዓመት ሶላሳ-ሁለት ሆኑ።የአፍሪቃ አንድነት ድርጅትንም መሠረቱ።የድርጅቱ ዋና መስራችና የመጀመሪያዉ ሊቀመንበር ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴ፣ንጉሰ ነገስት ዘ ኢትዮጵያ።ግንቦት 25፣ 1963 አዲስ አበባ።

«ይቀን ለአፍሪቃዉያን በመላ ታሪካዊና ታላቅ ቀን ነዉ።» ከ38 ዓመት በኋላ ግንቦት 2001 ከሐምሳ በለጡ።የአፍሪቃ ሕብረት እንዲመሰረት ወሰኑ።ኃምሌ 9፣ 2002 ሕብረቱን መሠረቱ።ባለፈዉ ቅዳሜ 20 ዓመቱ።55 ሆኑም።20ኛ ዓመቱ መነሻ፣ የአንድነትና የሕብረቱ ምስረታ ፈተናና መፍትሔዉ ማጣቃሻ፣ የአፍሪቃ-ተስፋ ቀቢፀ ተስፋ መድረሻችን ነዉ።  

የቀድሞዉን የአፍሪቃ አንድነት ድርጅትንም ሆነ የኋላዉን የአፍሪቃ ሕብረትን አንዳዶች ከማቀድ ማዉራት ባለፍ ለአሐጉሪቱ ሕዝብ ምንም የማይሰራ የወሬ ሱቅ ይሉታል።ሌሎች የአፍሪቃ መሪዎች መነታረኪያም-መሞጋገሺም መዝናኛም ያደርጉታል።ጥርስ ጥፍር የለሽ ማሕበር ባዮችም ብዙ ናቸዉ።አምባሳደር ተፈራ ሻዉል ግን ወቀሳ፣ትችት ስድቡን ይቃወማሉ።

Gründung Afrikanische Union Durban 2002
ምስል picture-alliance/dpa/dpaweb

«ጥርስ የለዉም ተብሎ የአፍሪቃ ሕብረት ሊወቀስ አይገባም።እያንዳዱ ሐገር አፍሪቃ ዉስጥ እንደምታዉቀዉ የዴሞክራሲ ጥማት አለ።በሐገራቸዉ ዴሞክራሲን እያራመዱ አፍሪቃ ዉስጥ እንዳይራመድ የሚፈልጉ አሉ።አምባገኖችን ይደግፋሉ»አምባሳደር ተፈራ በ1963 የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ሲመሠረት እንደ ጋዜጠኛ፣ በ2002 የአፍሪቃ ሕብረት ሲመሰረት ደግሞ እንደ ዲፕሎማት የየምሥረታዉን ሒደትና ሥርዓት ተከታትለዋል።«የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ቻርተር ተፈረመ።ቻርተሩ በነገራችን ላይ ኦሪጂናል ቋንቋዉ አማርኛ ነዉ።አማርኛዉን ከፈለክሕ እልክልሐለሁ»

 

በ19ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ፓዉል ካፊ፣ ዶክተር WEB  ዱቢዮ፣ ማርከስ ሞሲያሕ ጋርቬይ ዩናይትድ ስቴትስና ጃማይካ ላይ የወጠኑት የጥቁሮች አንድነት አዲስ አበባ ላይ ፀና።የአፍሪቃ አንድነት በሰነድ ፀደቀ።1963።ከዚያ ለመድረስ ግን ለያኔዎቹ የአፍሪቃ መሪዎች ጉዞዉ ከባድ፣በክፍፍል፣ በድጥ፣ ማጥ የተሞላ አንሸራታች ነበር።

Gründung Afrikanische Union Durban 2002
ምስል picture-alliance/dpa/dpaweb

ጋርቬይ በ1814 የመሰረቱት የሁለንተናዊ የጥቁሮች እድገት ማሕበርና የአፍሪቃ ማሕበረሰብ ሊግ (UNI-ACL) ለጥቁሮች አንድነት የመጀመሪያዉ ጠንካራ ማሕበር ነበር።የነጋርቬይን የአንድነት መርሕ ከተማሪነታቸዉ ጀምሮ ሲያቀነቅኑ ያደጉት የኋላዎቹ የአፍሪቃ መሪዎችና ልሒቃን አፍሪቃ በአንድነት ካልቆመች የቅኝ ገዢዎችን ጥቃትና ጫና ማምለጥ አትችልም የሚል መርሕ ያራምዱ ያዙ።የዚሕ ሐሳብ ዋና አራማጅ የነበሩት የመጀመሪያዉ የጋና ፕሬዝደንት ክዋሚ ንክሩማ «የጋና ነፃነት ከመላዉ አፍሪቃ ነፃ መዉጣት ጋር ካልተገናኛ ትርጉም የለዉም» ይሉ ብለዉ ነበር።አፍሪቃዉያንም በአሜሪካኖች አምሳያ የተባበረዉ የአፍሪቃ መንግስታት እንዲመሰርቱ ይታገሉ ያዙ።Pan Africanism አምባሳደር ተፈራ ሻዉል «የጋናዉ ዶክተር ንኩሩማ የአፍሪቃ አንድነትን መንፈስ ይዘዉ፣ ከተማሪነታቸዉ ጀምረዉ ስለ ጥቁሮች ሕብረት ይናገሩ ነበር።»

 

የንኩሩማ ሐሳብ የብዙ ወጣት አፍሪቃዉያን ምሑራንና የነፃነት ታጋዮችን ድጋፍ ቢያገኝም፣ በስልጣን ላይ የነበሩት መሪዎችና ፖለቲከኞች ግን  የአፍሪቃ ሐገራት የየራሳቸዉን ልዑላዊነት አፍርሰዉ የተባበሩት የአፍሪቃ መንግስታትን ይመስርቱ የሚለዉን ሐሳብ አልተቀበሉትም።ልዩነቱ የቅኝ ገዢዎች ሴራና ሻጥር ታክሎበት  ነፃ የወጡት 27ቱ የአፍሪቃ መንግስታት መጀመሪያ ሶስት፣ ኋላ ግን የሞንሮቪያና የካዛ ብላንካ የተባሉትን ሁለት ቡድናት መስርተዉ ንትርክ ገጠሙ።

ጥር 1962 በኢትዮጵያ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር በኩል እየቤልዩ ቤተ-መንግስት ቀደም-ከተል ብለዉ የደረሱት ሁለት ደብዳቤዎች ኢትዮጵያ በአፍሪቃዉያን ዘንድ የነበራትን ክብር፣ተወዳጅነትና አለኝታነት መስካሪ፣ ጋዜጠኛዉ እንደታዘበዉ ደግሞ ለአፄ ኃይለ ስላሴና ለዲፕሎማቶቻቸዉ ጥሩ አጋጣሚ ሆኑ።

«ኢትዮጵያ በየጉባኤያቸዉ ላይ እንድትገኝ ሁለቱም ቡድኖች ጥር 1962 የግብዣ ደብዳቤ ላኩ።የካዛ ብላንካዉ ቡድን ካይሮ ላይ፣ የሞንሮቪያዉ ደግሞ ሌጎስ ላይ ጉባኤ ለማድረግ አቅደዋል።የኢትዮጵያ መሪ፣ ንጉስ ነገስት ኃይለ ስላሴ ግብዣዉን ሁለቱን አንጃዎች ለማስታረቅ እንደ ጥሩ አጋጣሚ ተጠቀሙበት።»

ባመቱ ግንቦት የ32ቱ የአፍሪቃ መሪዎች አዲስ አበባ ላይ ጉባኤ ተቀመጡ።የጉባኤዉ ሒደት፣ በተለይ የማሕበሩ ቅርፅና ይዘት ሌላ የዉዝግብ ምክንያት ነበር።ዉዝግብ፣ክርክር፣ኩርፊያ ንትርኩ እስከ ማለዳዉ ቀጠለ።አንጋፋዉ የስፖርት ጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ የአፄ ኃይለስላሴ ብልሐት ለሙያዉ ባለሙያ መመደባቸዉ ነዉ ዓይነት ይላል።«ኢትዮጵያ በምትካፈልባቸዉ ስብሰባዎች ሁሉ አንድ ፈረንሳይኛ፣ አንድ እንግሊዝኛ አንድ አረቢኛ በደንብ የሚያዉቅ መልዕክተኛ ከጃንሆይ ጋር አብሮ ይሄዳል።የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ሲመሰረትም አቶ ከተማ ይፍሩ የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሩ እንግሊዝኛ፣ አቶ ማሞ ታደሰ የገንዘብ ሚንስትሩ ፈረንሳይኛ፣ በአረብኛ ደግሞ አቶ ምናሴ ለማ ነበሩ።ሶስቱን ከፋፍለዉ አፍሪቃን ይይዙታል ከዚያ ንቅንቅ የለም።»

Gründung Afrikanische Union Durban 2002
ምስል ALEXANDER JOE/AFP/Getty Images

                                 

በርግጥም ንቅንቅ አላሉም።የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት መመስረቻን ደንብ ፈረሙ።የተባበሩት የአፍሪቃ መንግስታት አልተመሰረተም።አፍሪቃ ባንድ ለመቆም ግን መሪዎችዋ ተስማሙ።አፄ ኃይለስላሴም ለጉባኤተኞች ባደረጉት ንግግር «የዚሕ ታላቅ የጉባኤ መደረግና የመላዉ ነፃ የአፍሪቃ ሐገራት መሪዎች ተካፋይ መሆን ለአፍሪቃ ለሕዝቧ ላለን አሳቢነት ዓይነተኛ ምስክር ነዉ» በማለት አረጋገጡ።የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት፣ መስራቾቹ እንዳሰቡት ወይም ብዙዎች እንደጠበቁት የአፍሪቃ ሕዝብ ከድሕነት፣ከብዝበዛና ጭቆና ማላቀቅ አልቻለም።የአፍሪቃ ሐገራትን ከዉጪዎቹ ጫና ከግዛት ይገባኛልና ከርስ በርስ ጦርነት ማዳንም አልሆነለትም።

 

አፍሪቃ የኮሚንስት ካፒታሊስቶች ተዘዋዋሪ ጦርነት አስተጋጅ፣ የመፈንቅለ መንግስት መለማመጂያ፣ የአምባገነኖች መፈንጪያም ሆናለች።ድርጅቱ በተመሰረተበት ወቅት በቅኝ አገዛዝ ይማቅቁ የነበሩ አፍሪቃዉያንን ነፃ በማዉጣቱ ትግል ግን ያደረገዉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሊዘነጋ አይገባም።የተዘዋዋሪ ቅኝ ገዢዎች ሴራ፣የምዕራባዉያንና የዘር መድልኦ ስርዓት አራማጆች ሻጥር፣ የምዕራብ ምስራቆች ሽኩቻ፣ የእስራኤል አረቦች ጠብ ከአባል ሐገራት የጥቅም ግጭት ጋር ተዳምረዉ ድርጅቱን ግራ ቀኝ ቢያላትሙትም፣ በሊቀመንበር መንግስቱ ጥረት፣በነ ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ብልሐት ጨርሶ ከመፍረስ ድኗል።

 

ድርጅቱ የ39 ዓመት ጉዞዉን አጠንቅቆ ኃምሌ 2002 ወደ ሕብረትነት ሲቀየርም በአባል ሐገራት መካከል የነበረዉ ዉዝግብ እንደበፊቱ አይሁን እንጂ የተካረረ ነበር።አምባሳደር ተፈራ የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ በተለይ የሕብረቱ ዋና ፅሕፈት ቤት ከአዲስ አበባ እንዳይነሳ «ሽንጣቸዉን ገትረዉ በመከራከራቸዉ ሊመሰገኑ» ይገባል ይላሉ።አቶ መለስ  ከተከራከሩባቸዉ መድርኮች ባንደኛዉ ላይ እንዲሕ ብለዉ ነበር።

Treffen der Afrikanischen Union in Durban
ምስል AP

«ግን ማንም የማይክደዉ አንድ ሐቅ አለ።ኢትዮጵያን የሚገዛዉ መንግስት ምንም ሆነ ምን ኢትዮጵያ ሁል ጊዜ ለአፍሪቃ ነፃነት በፅናት ትቆማለች።ማንዴላን ያሰለጠነዉ ማነዉ?ንጉሰነገስት አፄ ኃይለስላሴ ናቸዉ።አድሐሪዉ (ንጉስ) አብዮታዊዉን ማንዴላ አሰልጥነዋል።ማንዴላ የሰለጠኑት ኢትዮጵያ ዉስጥ ነዉ።ሙጋቤ ከሮዴዚያ አገዛዝ ጋር ሲዋጉ የረዳቸዉ ማነዉ? መንግስቱ።ሐገር ዉስጥ መንግስቱ ገዳይ ነበሩ።የአፍሪቃ ጉዳይ ሲነሳ ግን መንግስቱ ልክ እንደ ኃይለስላሴ ሁሉ ጠጣጣር አቋም ነበራቸዉ።ኢትዮጵያ ለአፍሪቃ ያላት ፅኑ ድጋፍ በመንግስታት መለዋወጥ አልተለወጠም።»

 

የአፍሪቃ ሕብረት ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለማጠናከር፣አምባገነናዊ አገዛዝን በተለይም መፈንቅለ መንግስትን ለመከላከል የሚያስችሉ ጠንካራ ደንቦች አሉት።በተለያዩ የአፍሪቃ ሐገራት የሚጫሩ የርስበርስና የድንበር ዉዝግብና ጦርነቶችን ለማስቆም ከዲፕሎማሲ ሽምግልና ሰላም አስከባሪ እስከ ማዝመት የሚደርስ እርምጃዎችን እየወሰደ ነዉ።በየዓመቱ ሚሊዮኖችን የሚፈጀዉን በሽታ፣ድሕነትና ረሐብን ለመቀነስ፣ ስደትን ለመግታት እየጣረ ነዉ።አብዛኛ ጥረት እቅዶቹ ግን ለዉጤት አልበቁም።ምክንያቱ ብዙ ነዉ።የአፍሪቃዉያን መሪዎች አምባገነናዊነት፣ከሐገርና ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ ለየግል ስልጣንና ጥቅም መራወጥ፣ በሙስና መዘፈቅ፣ ራሳቸዉ ያወጡትን ሕግ እራሳቸዉ እየሻሩ ባሻቸዉ የመግዛት ስስት ጥቂቶቹ ናቸዉ።አጋዜጠኛ ፍቅሩ ኪዳኔ «አፍሪቃ ዉስጥ መፈንቅለ መንግስት ከተጀመረና ወታደራዊ ገዚዎች የቀድሞዎቹን መሪዎች መግደል ከጀመሩ  ወዲሕ ተስፋዉ መነመነ በፊት የነበረዉ ሁሉ ተለወጠ» ይላል።

 

Kofi Annan Afrikanische Union in Durban
ምስል AP

አምባሳደር ተፈራ ሻዉል በበኩላቸዉ ኃያላኑ  መንግስታት «እነሱ ከሚፈልጉና ከሚፈቅዱት ዉጪ» የፍሪቃን ሠላም፤ ልማትና ዕድገትን ስላማይፈልጉ «የአፍሪቃ ድርጅትንም ሆነ ሕብረትን ዓላማ ሥራና አሰራር ያደናቅፋሉ ወይም አደናቃፊዎችን ይረዳሉ።» ባይ ናቸዉ።የአፍሪቃ ማሕበር አንድነትም ሆነ ድርጅት የኃይለ ስላሴ ብልሐት፣ የመንግስቱ ቆራጥነት፣ የመለስ ተሟጋችነት የተመሰከረበት ነዉ።ኢትዮጵያ ግን ዛሬ የጦርነት፣ የዘር ግጭት ጥቃት አብነት ሆናለች።ተፋላሚ ኃይላትን ለማደራደር የአፍሪቃ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ ሰይሟል።ዩናይትድ ስቴትስና ቻይና የአፍሪቃ ሕብረት አደራዳሪን ጥረት በገንዘብም ይሁን በምክክር ከመርዳት ይልቅ የየራሳቸዉን ልዩ መልዕክተኞች መመደቡን ነዉ-የመረጡት።ለኢትዮጵያ ሰላም በጣም አስበዉ ይሆን? ለነገሩ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ለሐገርና ሕዝባቸዉ ሰላም ማሰብና መጨነቅ ካልፈለጉ ሐገራቸዉ የአፍሪቃ ሕብረት ድክመት ማንፀባረቂያ፣የዋሽግተንና ቤጂንግ መሻኮቻ ብትሆን ያስገርም ይሆን?

ነጋሽ መሐመድ 

እሸቴ በቀለ