1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዲሱ የዲጅታል መታወቂያ ተስፋ እና ስጋቶች

ረቡዕ፣ መጋቢት 27 2015

ከጎርጎሪያኑ 2021 ዓ/ም ጀምሮ በኢትዮጵያ የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎትን ስራ ላይ ለማዋል በብሄራዊ የመታወቂያ መርሃ ግብር አማካኝነት ሙከራ ሲደረግ ቆይቷል።ያለፈው ሳምንት ደግሞ የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሀገሪቱን የዲጂታል መታወቂያ አዋጅ አፅድቋል።

https://p.dw.com/p/4Phri
NUR für das Investigativ-Team Digitaler Ausweis
ምስል Sven Simon/picture-alliance/dpa

አዲሱ የዲጅታል መታወቂያ


ከጎርጎሪያኑ 2021 ዓ/ም ጀምሮ በኢትዮጵያ  የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎትን ስራ ላይ ለማዋል በብሄራዊ  የመታወቂያ መርሃ ግብር  አማካኝነት ሙከራ ሲደረግ ቆይቷል።ያለፈው ሳምንት  ደግሞ የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  የሀገሪቱን የዲጂታል መታወቂያ አዋጅ አፅድቋል።የዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅት  በዲጂታል መታወቂያ ጥቅሞች፣ ስጋቶች እና ተግዳሮቶች ላይ ያተኮረ ነው።
የዲጅታል መታወቂያ አገልግሎት በዓለም ላይ የበይነመረብ መምጣትን ተከትሎ ከ1960 ዎቹ ጀምሮ በተለያዩ ሀገራት በሙሉ ወይም በከፊል እየተሰራበት ይገኛል።በአሁኑ ወቅት ከዓለም ህዝብ 3.2 ቢሊዮን ያህሉ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ የዲጅታል ማንነት ወይም መታወቂያ ተጠቃሚ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።በኢትዮጵያም ከጎርጎሪያኑ 2021 ዓ/ም ጀምሮ በብሄራዊ  የመታወቂያ መርሃ ግብር አማካኝነት በዓለም ባንክ ድጋፍ በድጂታል መታወቂያ አገልግሎት ላይ የሙከራ ስራ ሲሰራ ቆይቷል።በዚህም እስካሁን 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሰዎች ለመታወቂያው መመዝገባቸውን  የብሔራዊ መታወቂያ መርሃ ግብር መረጃ ያሳያል።
ያለፈው ሳምንት መጋቢት 21 ቀን 2015 ዓ/ም ደግሞ የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው  6ኛው  የሁለተኛ ዓመት የስራ ዘመን 12ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ ረቂቅ አዋጅን  በአብላጫ ድምጽ አፅድቋል።

Äthiopien, Addis Abeba | Äthiopisches Parlament
ምስል Solomon Muchie/DW

ይህ አዋጅ ነዋሪዎች በተለያዩ አገልግሎቶች ውስጥ የዲጂታል መታወቂያዎችን ለመጠቀም ህጋዊ መሰረት የሚሰጥ ሲሆን፤የሀገሪቱን የመለያ ስርዓት ለማዘመን ትልቅ ርምጃ መሆኑንም ምክር ቤቱ ገልጿል።የዲጂታል መታወቂው በዋናነት በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ የሚዘጋጅ ሲሆን፤ ለሌሎች ቋንቋዎችም ዝግ አለመሆኑን በምክር ቤቱ ተገልጿል።በምክር ቤቱ የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እፀገነት መንግስቱ በውይይቱ ገልጸዋል። 
በዝቅተኛው የመንግስት አስተዳደር ደረጃ የሚሰጠው የቀበሌ መታወቂያ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ በብዛት ጥቅም ላይ የዋለው የመለያ ዘዴ ነው። ይህ መታወቂያ በርካታ ድክመቶች ያሉት ሲሆን፤ከነዚህም ውስጥ  የማዕከላዊ መዝገብ አለመኖሩ፣ ሙስና፣ ለአንድ ሰው የተለያዩ ማንነቶችን የያዙ የተለያዩ መታወቂያዎችን ማደል   እና ረዘም ላለ ጊዜ መቆየት አለመቻል ይጠቀሳሉ።
ዲጅታል መታወቂያው ይህንን በማስቀረት  በመንግስት እና በሌሎች ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶች ላይ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት እና ፈጣን የአገልግሎት አሰጣጥ  እንዲኖር ለማድረግ አመቺ ሁኔታዎችን ይፈጥራል ተብሏል። የኢትዮጵያ  የመብቶች እና የዲሞክራሲ ማሻሻያ ማዕከል ዋና ስራ አስኪያጅ የሆነው በፈቃዱ ሀይሉ በጠቀሜታው ላይ ይስማማል። 

Digitaler Fingerabdruck
ምስል AP

ጉድ ዴይ ኦንላይን  የተባለው ጀማሪ የቴክኖሎጅ ኩባንያ ተባባሪ መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ትግስት አፈወርቅ በፅሁፍ በሰጡን አስተያየት የተማከለ ዲጅታል የመታወቂያ ስርዓት ባለመኖሩ ስራ እና ሰራተኛ ለማገናኘት በሚሰራው ጉዳይኦን በተባለው መተግበሪያቸው ብዙ ችግር ገጥሟቸዋል። እናም ዲጅታል የማንነት መለያው እምነት የሚጣልበት  ሰራተኛ ለማግኘት የሚያጠፉትን ጊዜ እና ገንዘብ የሚያስቀር ይሆናል። አዲሱ የዲጅታል መታወቂያ  እንደ ወይዘሮ ትግስት ላሉ  መረጃ ላይ ለተመሰረቱ የዲጅታል አገልግሎት ሰጭዎች ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገር አስተማማኝ የበይነመረብ ግብይቶችን ለመፈፀምም አስፈላጊ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም መታወቂያው ወንጀልን ለመከላከል፣የጤና አጠባበቅ፣ የባንክ አገልግሎት እና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶችን ተደራሽነት ለማሻሻል  ይረዳል። ነገር ግን ይህ ዲጅታል  መታወቂያ የተጠቃሚ ስሞችን፣ ፆታን፣የልደት ቀንን፣ የመኖሪያ አድራሻ የማህበራዊ ዋስትና ቁጥርን እና ሌሎች  ግላዊ መረጃዎችን አጠቃሎ የሚይዝ በመሆኑ ፤ ይህ የተከማቸ የግለሰቦች ውሂብ እንደ በፈቃዱ ገለፃ  አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል።

Sicherheitsschwachstelle Log4J
ምስል Alexander Limbach/Zoonar/picture alliance

ከዚህ አኳያ ችግሩን ለመከላከል ከዲጅታል ማንነት መለያ አዋጅ በፊት የግለሰቦች የውሂብ ጥበቃ አዋጅ ሊቀድም ይገባል ይላል።ከአዋጁ በተጨማሪም የግለሰቦች መረጃ እንዳይሰረቅ እና አላግባብ ጥቅም ላይ እንዳይውል በሀገሪቱ የውሂብ ጥበቃ የሚያደርግ ጠንካራ ተቋም አስፈላጊ መሆኑንም ይገልፃል።ያ ካልሆነ ግን በግለሰብም ሆነ በሀገር ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን አስምሮበታል።
እንደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዲጂታል መታወቂያ ማግኘት የሁሉም ሰዉ ሰብዓዊ መብት ነው።ከዚህ በመነሳት  የአፍሪቃ ሕብረትም እስከ ጎርጎሪያኑ 2030 ዓ/ም ድረስ የአህጉሪቱ ህዝብ የዚህ መታወቂያ ባለቤት እንዲሆን አቅዷል።ሰሞኑን አዋጁን ያጸደቀችው ኢትዮጵያም በጎርጎሪያኑ  2025 ዓ/ም መጨረሻ ድረስ  ፋይዳ የተሰኘውን ዲጂታል መታወቂያ ለነዋሪዎቿ የማደል ዕቅድ ይዛለች።ያም ሆኖ የበይነመረብ አገልግሎት ዝቅተኛ እና ውድ መሆን ፣ያልዳበረ የቴሌኮም መሰረተ ልማት፣ ለቴክኖሎጅ አጠቃቀም የህግ እና የቁጥጥር ማዕቀፍ አለመኖር ተግዳሮቶች  ናቸው።ከምንም በላይ ግን መታወቂያው ማንነት ላይ ላተኮረ ጥቃት ዜጎችን እንዳያጋልጥ የሚያሳስቡም አሉ። 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ