1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኅዳር 5 ቀን 2017 ዓ.ም. የዓለም ዜና

Hirut Melesseሐሙስ፣ ኅዳር 5 2017

የኅዳር 5 ቀን 2017 ዓ.ም. አርዕስተ ዜና ባለፈው ማክሰኞ የክስ ጭብጣቸው በዐቃቤ ሕግ ተሻሽሎ ከቀረበው በሽብር ወንጀል ከተከሰሱ 51 ሰዎች መካከል በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉት ዛሬ ሐሙስ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ። በእነ ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ በሽብር ወንጀል ክስ ከቀረበባቸው 51 ተከሳሾች መካከል አራት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ይገኙበታል። የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት፣ የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት እንዲወጣ በይፋ አለመጠየቁ አሳሳቢ ነው የዓሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አስታወቀ። ቱርክ ብሪክስ በተባለው ቡድን የአጋርነት ደረጃ ተሰጣት።

https://p.dw.com/p/4mzuH

አዲስ አበባ     በሽብር ወንጀል የተከሰሱት 51 ሰዎች የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ

 

ባለፈው ማክሰኞ  የክስ ጭብጣቸው በዐቃቤ ሕግ ተሻሽሎ ከቀረበው በሽብር ወንጀል ከተከሰሱ 51 ሰዎች መካከል በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉት ዛሬ ሐሙስ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ። በእነ ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ በሽብር ወንጀል ክስ ከቀረበባቸውና የክስ ጭብጣቸው ከተሻሻላቸው  51 ተከሳሾች መካከል አራት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ይገኙበታል።

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የተሰየመው ችሎት ዛሬ የቀረቡ ተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል አዳምጧል፤ ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን የወንጀል ክስ አለመፈፀማቸውንም ለችሎቱ ተናግረዋል ሲሉ ከተከሳሽ ጠበቆች አንደኛው ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

በዛሬው ችሎት የተከሳሽ ጠበቆች የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓትን ጠቅሰው ተከሳሾች የሚናገሩት የእምነት ክህደት ቃል በሙሉ፣ በመቅረፀ ድምፅ እንዲቀዳ በመጠየቃቸው የተከሳሾች ቃል ተቀድቷል ተብሏል። ዐቃቤ ሕግ በሰጠው አስተያየት ተከሳሾቹ የተከሰሱበትን ወንጀል ክደው የተከራከሩ በመሆኑ ማስረጃዎችን ለማቅረብ ከ ታህሳስ 7 እስከ ታህሳስ 18 ቀን ቀጠሮ ተሰጥቷል።

በሌላ በኩል በተለያዩ ጭብጦች ክስ የቀረበባት ጋዜጠኛ መስከረም አበራ ከተከሰሰችባቸው ጉዳዮች በአንዱ ሕዳር ሦስት የጥፋተኝነት ብይን የተሰጠባት ቢሆንም በወቅቱ ዳኞች ባለመሟላታቸው ብይኑ ሳይነበብ ቀርቷል።

ይህም በመሆኑ ብይን ለማንበብ ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረው ችሎት ዛሬም ዳኞች ባለመሟላታቸው የቅጣት ውሳኔውን ለማንበብ ለሕዳር 11 ተቀጥሯል ሲሉ ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ መግለፃቸውን ሰሎሞን ሙጬ ከአዲስ አበባ ዘግቧል።

 

መቀሌ       የተቃዋሚው «አሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ» ወቀሳ

የትግራዩ ጦርነት ካበቃ ከሁለት ዓመት በኃላም የኤርትራ ጦር ከአዋሳኝ አካባቢዎች ባለመውጣቱ  ህዝብ አደጋ ላይ ነው ሲል ዓሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አስታወቀ። ኢትዮጵያ እና ኤርትራን በሚያዋስኑ አካባቢዎች የሚገኙ ዛላንበሳ፣ ባድመ፣ ሰበያና እገላን ጨምሮ ሌሎች በርካታ አካባቢዎች በኤርትራ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ሆነው መቀጠላቸውን ፓርቲው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት፣ የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት እንዲወጣ በይፋ አለመጠየቁ ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ እንዳደረገው  የዓሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ዶሪ አስገዶምተናግረዋል።  

የፕሪቶርያውን የሰላም ስምምነት ያፈራረሙ አካላትም የኤርትራ ጦር በወረራ ከያዛቸው አካባቢዎች እንዲወጣ ጫና አልፈጠሩም ሲሉም ወቅሰዋል።

የኤርትራ ጦር እና በምዕራብ ትግራይ ያሉ የአማራ ታጣቂዎች ያላቸውንም ከአካባቢው እንዲያስለቅቅ ዓሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ጥሪ አቅርቧል። ከዚህ በተጨማሪ ፓርቲው በትግራይ የፀጥታ ችግሮች መባባሳቸውንም የገለፀ ሲሆን በዚህም በሴቶች ላይ የሚደርስ ፆታዊ ጥቃት፣ ግድያ፣ ዝርፍያ እና ሌሎች ወንጀሎችም መበራከታቸውን ማስታወቁን የመቀሌው ወኪላችን ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ ዘግቧል።

 

አንካራ    ቱርክ የብሪክስ አጋር አባል ሆነች

 

ቱርክ ብሪክስ በተባለው ቡድን የአጋርነት ደረጃ ተሰጣት።የሀገሪቱ የንግድ ሚኒስቴር ኦማር ቦላት ሀገራቸው በብሪክስ የአጋር አባልነት ደረጃ ተሰጥቷታል ሲሉ ዛሬ ለአንድ የግል ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃለ ምልልስ አስታውቀዋል።  ሚኒስትሩ  ሀገሪቱ ያገኘችው ይህ ደረጃ በብሪክስ ድርጅታዊ መዋቅር የሽግግር  ሂደት ነው ብለዋል። አንካራ ብሪክስን ከምዕራባውያን ጋር ከሚያስተሳስረው ከሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ ይልቅ ከአባል ሀገራት ጋር ለተጨማሪ የኤኮኖሚ ትብብር እድል የሚሰጥ አድርጋ እንደምታየው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጠይብ ሬሴፕ ኤርዶሀን ተናግረዋል። የኔቶ አባል ቱርክ ከቅርብ ወራት ወዲህ የብሪክስ አባል የመሆን ፍላጎት ስታሳይ ነበር። ብሪክስ  በአሁኑ ጊዜ  ብራዚል ፣ሩስያ፣ ህንድ ፣ቻይና ፣ደቡብ አፍሪቃ ፣ኢትዮጵያ ኢራን ግብጽ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶችን በአባልነት አቅፏል።

 

በርሊን    የጀርመን ወግ አጥባቂ ፓርቲዎች የህዝብ ድጋፍ ጨምሯል

በጀርመን ወቅቱን ያልጠበቀ ምርጫ ሊካሄድ ሦስት ወራት በቀሩበት በአሁኑ ጊዜ የተካሄደ የህዝብ አስተያየት መመዘኛ ፣ ለተቃዋሚዎቹ ወግ አጥባቂ ፓርቲዎች ህዝቡ የሚሰጠው ድጋፍ ከፍ ማለቱን አመልክቷል። በጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ የሚመራው ሦስት ፓርቲዎች የተጣመሩበት መንግሥት ከአንድ ሳምንት በፊት ከፈረሰ በኋላ ለመጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም. ምርጫ ተጠርቷል። በምዘናው  ተቃዋሚዎቹ እህትማማቾቹ  የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረትና የክርስቲያን ኅብረት ፓርቲዎች ህዝብ የሚሰጣቸው ድጋፍ ጨምሯል። በጥናቱ መሠረት  በምዘናው የተሳተፉ 33 በመቶ መራጮች በፍሬድሪሽ ሜርዝ የሚመራውን የመሀል ግራውን የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ እንደሚደግፉ አስታውቀዋል። መደበኛው የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ በመጪው ዓመት መስከረም ነበር የሚካሄደው ሆኖም ሾልዝ የጥምሩ መንግሥት አካል ከሆነው የነፃ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ መሪና የፋይናንስ ሚኒስትራቸው ክርስቲያን ሊንድነር ጋር ለወራት ሲያሟግታቸው በቆየው በጎርጎሮሳዊው 2025 ዓም የሀገሪቱ በጀት ላይ መስማማት ባለመቻላቸው ሾልዝ ያባረሯቸው ሊንድነር ከጥምሩ መንግሥት ሲወጡ መንግሥቱ ፈርሶ  ወቅቱን ያልጠበቀ ምርጫ እንዲጠራ ምክንያት ሆኗል ።በመመዘኛው መሰረት የሾልዝ ፓርቲ 15 በመቶ የጥምሩ መengeሥት አካል የነበረው የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ደግሞ 11 በመቶ ድጋፍ ነው ያገኙት ።

 

ለንደን    ዘ ጋርዲያን ቲውተርን መጠቀም አቆመ።

ዘ ጋርዲያን ጽሁፎቹን በቀድሞው ቲውተር በአሁኑ መጠርያው  X ማውጣት እንደሚያቆም አስታወቀ። የብሪታንያ ዕለታዊ ጋዜጣ ዘ ጋርዲያን  የXን ባለቤት ኤሎን ማስክን "ፖለቲካ ለመቅረጽ" የሚጠቀሙበት "መርዛማ" መድረክ ነው ሲል ተናግሯል ። ጋዜጣው ስለ ውሳኔው በሰጠው ማብራሪያ "በኤክስ ላይ መገኘት ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች ይልቅ ከአሉታዊ ጎኖቹ የበለጠ እና ሀብቶቻችንን ጋዜጠኝነትን በሌላ ቦታ ለማስተዋወቅ ይጠቅማል ብለን እናስባለን ብሏል። ዘ ጋርዲያን “የቀኝ ዘመም የሴራ ንድፈ ሃሳቦችን እና ዘረኝነትን ጨምሮ በመድረኩ ላይ የሚንፀባረቀው  ይዘት የሚረብሽ  እና አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል ብሏል። ይህም በተለይ የ X ባለቤት ኤሎን ማስክ ዶናልድ ትራምፕ ወደ ኋይት ሀውስ እንዲመለሱ ግፊት ካደረጉ ወዲህ  በቅርብ ወራት ውስጥ የበለጠ እየጨመረ ነው ሲልም አስታውቋል። "ለዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዘመቻ ያገለገለው X መርዛማ የመገናኛ ብዙሃን መድረክ መሆኑን እና  ኤሎን ማስክ የፖለቲካ ንግግሮችን ለመቅረጽ ተጽኖውን ሊጠቀሙበት ችለዋልም ብሏል ዘጋርዲያን።

 

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ

 

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ስለዚህ ዝግጅት

ስለዚህ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።