1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በተባለው ቀን እንመለስ ይሆን?

ሐሙስ፣ ግንቦት 22 2016

መቐለ በሚገኘው 70 ካሬ የተፈናቃዮች መጠልያ ያነጋገርናቸው ተፈናቃይ አቶ ገብረመድህን ጨርቆስ ተፈናቃዮች ከክረምት በፊት ለመመለስ የተገባው ቃል እየተፈፀመ አይደለም ሲሉ ይናገራሉ።

https://p.dw.com/p/4gSqn
ከትግራይ ተፈናቃዮች መካከል
ከትግራይ ተፈናቃዮች መካከልምስል Million Hailesillassie/DW

በተባለው ቀን እንመለስ ይሁን?

በትግራይ የሚገኙ የጦርነቱ ተፈናቃዮች እስካሁን ወደቀዬአቸው አለመመለሳቸው ተከትሎ ለከፋ ሁኔታ ተዳርገው እንደሚገኙ ገለጹ። መንግስት ከክረምቱ በፊት ወደቀዬአቸው እንዲመልሳቸው ተፈናቃዮቹ ጥሪ አቅርበዋል። የክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር ተፈናቃዮቹ እስከ ሰኔ 30 ድረስ ለመመለስ ከፌደራል መንግስቱ ጋር መግባባት መደረሱ እና ስራዎች እየተከናወኑ ነው ቢልም ተፈናቃዮች ተስፋ ሰጪ ሁኔታ የለም ባዮች ናቸው።

የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በቅርቡ የጦርነቱ ተፈናቃዮች እስከ ሰኔ 30 ድረስ ሙሉበሙሉ ለመመለስ ከኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ጋር መግባባት መደረሱ፣ ይህ ለማስፈፀም እና አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር ደግሞ እየተሰራ መሆኑ ሲገልፅ ቆይቷል። ከትግራይ ደቡባዊ እና ሰሜን ምዕራብ ዞኖች የተፈናቀሉ እሰከ ግንቦት 30፣ ከትግራይ ምዕራባዊ ዞን የተፈናቀሉ ደግሞ እስከ ሰኔ 30 ድረስ ይመለሳሉ ተብሎ በግዚያዊ አስተዳደሩ ምክትል ፕሬዝደንት ተገልፆ ነበር። ይሁንና በትግራይ የተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ተፈናቃዮች እንደሚሉት እስካሁን በተባለው ግዜ መመለስ የሚያስችል እንቅስቃሴ እየታየ አለመሆኑ ተከትሎ ሌላ የክረምት ወቅት በመጠልያ እንዳያሳልፉ ስጋት ላይ ናቸው። ከፀገዴ፥ መንደር አውሮራ ከተባለ አካባቢ ተፈናቅለው አሁን በዓድዋ በሚገኝ መጠልያ ያሉ አቶ ገብረእግዚአብሔር ወልዱ ተፈናቃይ ለመመለስ ምዝባ እየተካሄደ መሆኑ የሚናገሩ ሲሆን ይሁንና ስራው አሁንም አዝጋሚ መሆኑ ይገልፃሉ።

የትግራይ ተፈናቃዮች ወደ ቀያችን መልሱን በማለት ቀደም ሲል ያደረጉት ሰልፍ በከፊል
የትግራይ ተፈናቃዮች ወደ ቀያችን መልሱን በማለት ቀደም ሲል ያደረጉት ሰልፍ በከፊልምስል Million Haileselassie/DW

ሌላ መቐለ ከሚገኘው 70 ካሬ የተፈናቃዮች መጠልያ ያነጋገርናቸው ተፈናቃይ አቶ ገብረመድህን ጨርቆስ በበኩላቸው ተፈናቃዮች ከክረምት በፊት ለመመለስ የተገባው ቃል እየተፈፀመ አይደለም ሲሉ ይናገራሉ።

አቶ ገብረመድህን "የእርዳታ ጉዳይ በተወሰነ ደረጃ የተሻሻለ ይመስላል። ግን እሱ አይደለም ተስፋችን። ለማኝ ሆኖ መኖር አይቻልም። በተባለው መሰረት እስከ ሰኔ 30 ድረስ ልንመለስ ይገባል። ህዝቡ በተስፋ ነው እየጠበቀ ያለው" ይላሉ።

ያነጋገርናቸው ተፈናቃዮችበእርዳታ አቅርቦት ረገድ የተወሰነ መሻሻል ቢኖርም፥ ከዚህ ባለፈ ከእርዳታ ተላቀው ወደ መደበኛ ሕይወታቸው የሚመለሱበት ሁኔታ እንዲፈጠር ጥሪ ያቀርባሉ።

የጦርነቱ ተፈናቃዮች መመለስ የአስተዳደሩ ቀዳሚ ተግባር ነው የሚለው የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር በወጣው አቅድ መሰረት ከፌዴራሉ መንግስት ጋር በመተባበር ከክረምት በፊት ተፈናቃዮች ለመመለስ እየሰራ መሆኑ ገልጿል። በዚህ ጉዳይ  ከፌዴራሉ መንግስት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ሚልዮን ሃይለስላሴ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
እሸቴ በቀለ