1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ ተፈናቃዮች መመለስ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 23 2016

በአማራ ክልል በኩል ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች የተመሰረቱ ሕገወጥ አስተዳደሮቹ ፈርሰው ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው የሚመለሱበት ምቹ ሁኔታ ሊፈጠር፣ አዳዲስ ሰፋሪዎች ከያዙት ቦታ ሊወጡ ከፌደራሉ መንግስት ጋር በነበረ ውይይት መግባባት ላይ መደረሱ ጀነራል ታደሰ ወረደ ተናግሯል።

https://p.dw.com/p/4fOsk
Äthiopien Tigray Mekelle | PK Vizepräsident der Übergangsregierung General Tadese Werede
ምስል Million Haileslassie/DW

የትግራይ ተፈናቃዮች መመለስ

አስከ ሰኔ 30 ባለው፥ በአማራ ክልል በኩል ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች የተመሰረቱ ሕገወጥ አስተዳደሮች ሊፈርሱ፣ ተፈናቃዮች ወደቀዬአቸው ሊመለሱ ከፌደራሉ መንግስት ጋር መግባባት መደረሱ የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር አስታወቀ። የግዚያዊ አስተዳደሩ ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ ዛሬ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ በሰጡት ማብራሪያ የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ለመተግበር ሁለቱ ተደራዳሪ አካላት እየሰሩ ነው ብለዋል።

ዛሬ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ለመንግስት መገናኛ ብዙሐን መግለጫ የሰጡት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት በየምዕራፉ ለመተግበርከኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ጋር እየተሰራ መሆኑአንስተዋል። በተለይም በጦርነቱ ምክንያት ከምዕራብ ትግራይ ዞን፣ ከደቡብ ትግራይ የተለያዩ ወረዳዎች እንዲሁም ከፀለምቲ የተፈናቀሉ እና እስካሁን ወደቀዬአቸው ያልተመለሱ ተፈናቃዮች ለመመለስ ዝርዝር የአፈፃፀም እቅድ መውጣቱ ያነሱ ሲሆን በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ተፈናቃዮች የመመለስተግባር ለመከወን መግባባት መደረሱ አንስተዋል።

በአማራ ክልል በኩል ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች የተመሰረቱ ሕገወጥ አስተዳደሮቹ ሊፈርሱ፣ ተፈናቃዮች ወደቀዬአቸው የሚመለሱበት ምቹ ሁኔታ ሊፈጠር፣ አዳዲስ ሰፋሪዎች ከያዙት ቦታ ሊወጡ ከፌደራሉ መንግስት ጋር በነበረ ውይይት መግባባት ላይ መደረሱ ያነሱት ጀነራል ታደሰ ወረደ ተፈናቃዮች ከተመለሱ በኃላ ባለው ግዜ ደግሞ በጣብያ እና ወረዳ ደረጃ አዲስ አስተዳደር እንደሚመሰረት ተናግረዋል። ጀነራል ታደሰ "የተቀመጠው ግዜ፥ ራያ እና ፀለምቲ እስከ ግንቦት 30 ሊጠናቀቅ፣ ምዕራብ ትግራይ ደግሞ እስከ ሰኔ 30 ባለው ልናጠናቅቅ የሚል ነው። ይህ ሙሉ መግባባት የተደረሰበት ነው። በእኛ በኩል በተቀመጠው ሐሳብ እና አፈፃፀም ተግባብተን ጨርሰናል" ብለዋል።

Symbolbild I Äthiopien - Humanitäre Lage
ምስል Ed Ram/Getty Images

እነዚህ አካባቢዎች በማን ስር ይቆያሉ የሚለው ጉዳይ ግን ገና መቋጫ ያላገኘ አጀንዳ መሆኑ ጨምረው የተናገሩት ጀነራል ታደሰ የትግራይ ሐይሎችም የያዝዋቸው አካባቢዎች እንደሚለቁ ጠቁመዋል። ከዚህ በተጨማሪ በትግራይ በኩል የሰላም ስምምነቱ በሙሉእነት የመተግበር እንጂ ወደጦርነት የመግባት ፍላጎት ፈፅሞ የለም ሲሉም በአፅንኦት ተናግረዋል።

ጀነራል ታደሰ "ጦርነት የሚፈልግ ሐይል አለ፣ ሰላም የማይሻ አለ የሚል ሆን ተብሎ የሚፈጠር ትርክት ስህተት ነው። ስህተት መሆኑም በተደጋጋሚ ገልፀናል። ይህ ለነሱም ገልፀንላቸዋል። ይህ ታስቦበት አልያም በስህተት የሚሰራጭ ትርክት መሬት ላይ የሌለ ነው። እንደ ትግራይ አንድ ሆነን ይህ ተግባራዊ ለማድረግ ነው እየሄድን ያለነው። በሌላ ገፅ ደግሞ ይህ ትርክት ለመጠቀም የሚሞክር አካላም በሌለ ነገር ነው ለመጠቀም ሙከራ እያደረገ ያለው። በሁለታችን ተደራዳሪዎች በኩል ግን እንደ ቁምነገር መታየት ያለበት ሳይሆን ስምምነቱ ለመተግበር በሚደረግ እንቅስቃሴ የሚያጋጥም ችግር ተደርጎ መታየት ያለበት ነው" ሲሉ ገልፀዋል።

ከጦርነቱ መቆም 18 ወራት በኃላም ቢሆን በጦርነቱ ምክንያት ከምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብ እንዲሁም ደቡብ ትግራይ ዞኖች በሐይል የተፈናቀሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አሁንም በየመጠልያው የከፋ ሕይወት እየገፉ ነው።

ሚልዮን ሃይለላሴ

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር