1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ ተወላጅ የመከላከያ አባላት እንዲፈቱ ተጠየቀ

ረቡዕ፣ መጋቢት 4 2016

በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች በእስር ላይ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች የሆኑ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ከእስር እንዲለቀቁ ቤተሰቦቻቸው እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጠየቁ ።

https://p.dw.com/p/4dTAp
Äthiopien, Mek'ele | Verwaltungsgebäude der Region Tigray
ምስል Million Haileselassie/DW

የታሳሪዎቹ ቤተሰቦች ችግር ላይ ወደቀናል ብለዋል

በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች በእስር ላይ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች የሆኑ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ከእስር እንዲለቀቁ ቤተሰቦቻቸው እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጠየቁ ። በጦርነቱ ወቅት የታሰሩት እነዚህ የትግራይ ተወላጆች የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት፥ ከሰላም ስምምነቱ በኋላም ከእስር አለመፈታታቸውን ቤተሰቦቻቸው ይናገራሉ ። 

ከሰላሳ ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የቆዩት ሌተናንት ኮለኔል ገብረኪዳን ወልደማርያም፥ ከትግራዩ ጦርነት ጋር ተያይዞ ከሥራ ቦታቸው ተይዘው ከታሰሩት የትግራይ ተወላጅ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት መካከል መሆናቸውን ቤተሰቦቻቸው ይገልፃሉ። የሌተናል ኮለኔል ገብረኪዳን ልጅ ፍረሕይወት ገብረኪዳን፥ አባትዋ እስከታሰሩበት ቀን ድረስ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ደቡብ ዕዝ ይሰሩ እንደነበር ገልጻለች ።  ታስረው ከተፈረደባቸው በኋላ መላ ቤተሰብ ያሉበትን ሁኔታ እንደማያውቅም ነግራናለች።

ታሳሪዎቹ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?

«ደቡብ እዝ አርባምንጭ ነበር ይሠራ የነበረው። በ2013 ዓመተምህረት ሥራችሁን አቋርጡ፤ ትጥቃችሁን ፍቱ ተብለው እዛ ታስሮ እንደነበረ ነው የምናውቀው» የምትለው የኮለኔሉ ልጅ፥ መጀመርያ ላይ አባታቸው ይደውሉላቸው እንደነበረ ተናግራለች ።  ነሐሴ 28 ቀን፣ 2013 ዓመተምህረት የ18 ዓመት እስር ተፈረደባቸው ከተባለ በኋላ ግን ስለአባታቸው የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ትገልፃለች።

የቤተሰብ አስተዳደር የሆነ አባታቸው ሌተናል ኮለኔል ገብረኪዳን ከታሰሩ በኋላ ቤተሰባቸው ለከፋ ሕይወት ተጋልጦ እንደሚገኝ ልጁ ፍረሕይወት ጨምራ ትናገራለች። «2013 ነሐሴ ላይ ከተፈረደበት በኋላ ወድያውኑ ደሞዝ ተቋረጠ፣ ለመከላከያ ቤተሰብ ከተሰጠው ቤት አስወጡን፣ በችግር ላይ ነን ያለነው» ትላለች።

የተጠቀሱት ኮለኔን የመሰሉ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ የትግራይ ተወላጅ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት፥ ገሚሶች ያሉበት ሁኔታ ሳይታወቅ፥ ሌሎች ደግሞ ከትግራዩ ጦርነት ጋር በተያያዘ ተከሰው፥ በወታደራዊ ፍርድቤት ተፈርዶባቸው፥ በእስር ላይ መሆናቸውን ቤተሰቦቻቸው ይገልፃሉ

ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የነገሩን ሌላው ያነጋገርናቸው የአንድ ታሳሪ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባል ወንድም፥ ሰላሳ ዓመት ገደማ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በተለያዩ የኃላፊነት ዘርፍ ያገለገሉ ኮለኔል ወንድማቸው እና ሌሎች ዒላማ ተደርገው ተለይተው የታሰሩት «በብሄራቸው» ምክንያት መሆኑን ይገልፃል።

የትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቐለ
የትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቐለምስል Million Haileselassie/DW

እኝህ የታሳሪ ቤተሰብ በተለይም ከሰላም ስምምነቱ በኋላ እነዚህ በጦርነቱ ወቅት የታሰሩ የትግራይ ተወላጅ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ይፈታሉ ብሎ ቤተሰብ ይጠብቅ እንደነበረ የሚገልፅ ሲሆን፥ ይሁንና አሁንም ወንድማቸውን ጨምሮ በርካቶች በተለያዩ የሀገሪቱ እስርቤት እየማቀቁ ነው ይላሉ።

የታሳሪዎቹ ቤተሰቦች ችግር ላይ ወደቀናል ብለዋል

«የእኔ ወንድም የታሰረው ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ሕዳር 12 ቀን፣ 2013 ዓመተምህረት ነው። መጀመርያ የፌደራል ወንጀል ምርመራ ሜክሲኮ አከባቢ ያለው አሰሯቸው» የሚሉት እኝህ ያነጋገርናቸው የታሳሪ ቤተሰብ፥ ከወንድማቸው መታሰር በኋላ ቤተሰባቸውም የመከላከያ ቤተሰብ ከሚኖርበት ቤት እንዲወጡ መደረጋቸውን ጨምረው ገልፀዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር  በእስር ላይ ያሉ የትግራይ ተወላጅ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት እንዲፈቱ በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ቆይቷል። በጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ፕሬዝደንት ሌተናንት ጀነራል ታደሰ ወረዳ ፊርማ፥ በቅርቡ ለኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር መላኩ የተነገረው ደብዳቤ፥ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ተፈርዶባቸው፣ በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች እስር ላይ እንደሚገኙ በማንሳት፣ ለሕዝብ ጥቅም ተብሎ በይቅርታ ወይ በሌላ መንገድ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ይጠይቃል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴሩ ዶክተር አብርሃም በላይ
የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴሩ ዶክተር አብርሃም በላይ። ፎቶ፦ ከክምችት ማኅደርምስል DW/G. Tedla Haile Giorgis

በዚህ ጉዳይ ዙርያ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ምላሽ ለማግኘት በተደጋጋሚ ወደ ሕዝብ ግንኙነት ክፍሉ ብንደውልም አልተሳካም። በዚሁ እና ሌሎች ጉዳዮች ዙርያ በቅርቡ ለመንግስታዊው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተናግረው የነበሩ የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴሩ ዶክተር አብርሃም በላይ፦ ታስረው ያሉ የትግራይ ተወላጅ የመከላከያ ሰራዊት አባላት መኖራቸው አረጋግጠዋል። የታጠቀ ብቻ አይደለም፣ ሁሉም ትግራዋይ በጥርጣሬ የሚታይበት ሁኔታ ነበረ ብለው የሚገልፁት ሚኒስቴሩ፥ ከጦርነቱ ጅማሮ በኃላ "ካምፕ" ባሉት ቦታ እንዲቆዩ የተደረጉ የትግራይ ተወላጅ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት እንደነበሩ፣ በኋላ ላይ ግን በርካቶች ከነበሩበት ወጥተው ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ መደረጉን ተናግረዋል። የቀሩ በነበረው ሁኔታ ምክንያት የታሰሩ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት የሆኑ የትግራይ ተወላጆች ለይቶ ለመፍታትም ሥራዎች እየተከወኑ ነው ሲሉ ገልፀው።

መከላከያ ሚኒስቴሩ አብርሃም በላይ «ከፕሪቶርያው ውል ጋር የተያያዘ፥ ሰላም ስለፈጠርን፥ ሌላ ወንጀል እስካልሰሩ ድረስ ይቅርታ የሚሰጣቸው አካላት እየተለዩ ነው። እነዚህ በስርዓቱ፥ በይቅርታ ይለቀቃሉ» ብለዋል። የታሳሪ ቤተሰቦች «አለአግባብ ታስረዋል» ያሏቸው የመከላከያ አባላት በፍጥነት እንዲፈቱ፥ ይህ እስኪሆን ደግሞ የተሻለ አያያዝ እንዲኖር ይጠይቃሉ።

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ-እግዚአብሔር