1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታሳሪዎች የረሃብ አድማ

ሰኞ፣ መስከረም 21 2016

የረሃብ አድማ ለማድረግ ምክንያት ብለው ያስቀመጡትን ጉዳይም ጠበቃው ሲያብራሩ «በታሰሩበት ቦታ ስለሚደርስባቸው የመብት ጥሰት እና በአማራ ማኅበረሰብ ላይ ተደቅኗል ስላሉት አደጋ ድምፅ ለመሆን» መሆኑን ጠቅሰዋል።

https://p.dw.com/p/4X3ML
መታሰርን የሚወክል ምስል
ምስል Fotolia/axentevlad

የረሃብ አድማ በእስርቤት

የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር እና አባል የነበሩት አቶ ዮሐንስ ቧያሌው እና ዶክተር ካሣ ተሻገር እንዲሁም የተቃዋሚ የፓለቲካ ፓርቲ አመራር እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ክርስትያን ታደለ ከዛሬ ጀምሮየረሃብ አድማ ላይ ስለመሆናቸው በማኅበራዊ መገናኛዎች ከትናንት ጀምሮ እየተነገረ ነው። ይህ ምን ያህል እውነተኛና ተጨባጭ መረጃ ነው ስንል የጠየቅናቸው የአቶ ክርስቲያን ታደለ ባለቤት ወይዘሮ ናርዶስ አዲሴ «እንዲህ ያለውን ነገር ያደርጉታል የሚል እምነት አለኝ» ብለዋል። 
የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር እና የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል የነበሩት የአቶ ዮሐንስ ቧያሌው ባለቤት ወይዘሮ ሄዘር ሙሰማ «እርግጠኛ ባልሆንም የእነሱ ይመስለኛል» ሲሉ በእጃቸው ተጽፎ ወጣ የተባለው ጽሐፍ የታሳሪዎቹ ሊሆን እንደሚችን ገልጸዋል። 
ኢሰመኮ በአማራ ክልል የተደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተከትሎ የምክር ቤት አባላትን ጨምሮ 53 እስረኞች አዋሽ አርባ ውስጥ በሚገኝ ጊዜያዊ ማቆያ የሆነ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ እንደሚገኙ በአካል አመራሮቹ ተገኝተው መመልከታቸውን ከዚህ በፊት አረጋግጦ ነበር። ኮሚሽኑ ከዚህ በኋላ ግን ለክትትል ወደዚህ ስፍራ አለመሄዱን ለዶቼ ቬለ አረጋግጧል። የታሳሪዎቹን ጠበቃ አቶ ሰለሞን ገዛኸኝንም ስለጉዳዩ  ጠይቀናቸዋል። ታሳሪዎቹ የረሃብ አድማ ለማድረግ ምክንያት ብለው ያስቀመጡትን ጉዳይም ጠበቃው ሲያብራሩ «በታሰሩበት ቦታ ስለሚደርስባቸውየመብት ጥሰት እና በአማራ ማኅበረሰብ ላይ ተደቅኗል ስላሉት አደጋ ድምፅ ለመሆን» መሆኑን ጠቅሰዋል። 
ከአቶ ክርስትያን ታደለ እና ከዶክተር ካሣ ተሻገር ጠበቆች አንዱ ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ እሥሩ ሕገ - ወጥ ነው በሚል በፍርድ ቤት ጀምረውት የነበረው አካልን ነፃ የማውጣት ክስ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ድንጋጌ የሚሻር በመሆኑ ክሱን ለማቋረጥ መገደዳቸውን ገልፀዋል። 
ሰሎሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሔር
ሽዋዬ ለገሠ