የባሌ ተራሮች እና የጌዴኦ ባህላዊ የተፈጥሮ ቅርሶች
ሐሙስ፣ መስከረም 24 2016
ኢትዮጵያ መልክዓ ምድራዊ የተፈጥሮ አቀማመጧ ፣ እንደሀገር የምትታወቅባቸው እና መልካም ስም ያተረፈችባቸው ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ቅርሶቿ ፣ ህዝቦቿ ለዘመናት የቀመሯቸው የባህላዊ እሴቶቻቸው ድምር በአፍሪቃ ቀዳሚ የሚዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት አድርገዋታል። በእርግጥ ነው ኢትዮጵያ ከባሕር ጠለል በታች 125 ሜትር ዝቅ ብሎ ከሚገኘው የዳሎል ወይም ደንከል ዝቅተኛ መልክዓ ምድር ጀምሮ ከባሕር ጠለል በላይ 4,550 ሜትር እስከሚረዝመው የዳሸን ተራራ ባለቤት ናት ። ዓለም አውቆ ከመዘገበላት ታሪካዊ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ቅርሶች ባሻገር ዛሬም አስደማሚ እና ከሀገራዊ ቅርስነት ባሻገር ዓለም አቀፋዊ እውቅና ሊያገኙ የሚገባቸው የበርካታ ቅርሶች ምድርም ናት። የዘመን አቆጣጠር ስሌቷ ፤ የራሷ ፊደል ያላት ፣ በክርስትናም ሆነ የእስልምና ሃይማኖት መጻሕፍት የተጠቀሰች ምድር ኢትዮጵያ ፤ ምንም እንኳ በግጭት ጦርነት ፣ ስደት መፈናቀል ስሟ በተደጋጋሚ ቢነሳም ፣ ድርቅ ፣ በሽታ እና ረሃብ ዛሬም ፈተናዋ እንደሆነ ቢዘልቅም ይህቺው ምድር በብዙ የውጣ ውረድ ውስጥ ሆና ዘንድሮ ሁለት ተፈጥሯዊ እና ባህላዊ የሚዳሰሱ ቅርሶችን ለዓለም እንካችሁ ብላለች ። ባህላዊ ሕግ "ሂር ሂሴ" በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስነት እንዲመዘገብ የሚደረገው ጥረት
ዓለም አቀፉ የቅርስ ኮሚቴ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እና በጌዴኦ ዞን የሚገኘው የጌዴኦ ባሕላዊ መልክዓ- ምድርን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገቡ ወስኗል። ይህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የባህል ፣ ታሪክ እና የተፈጥሮ መስህብ የቅርስ መዝገብ ውስጥ ያሰፈረቻቸውን ቅርሶች ብዛት 11 በማድረስ ከአፍሪቃ ቀዳሚ እንድትሆን አስችሏታል። ይህ ለኢትዮጵያውያን ይዞ የሚመጣውን የጭስ አልባ ኢንዱስትሪ ገጸ በረከት ሲታሰብ ደግሞ ትልቅ የዕድል በር እንደሚከፍት ይገመታል።
አቶ ነጋ ወዳጆ የኦሮሚያ ክልል የቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ናቸው ። በቅርቡ ኦስሎ ኖርዌይ ውስጥ በተካሄደ የቱሪዝም አውደ ርዕይ ላይ ተሳትፈው ሲመለሱ ወደ ቦን ጀርመን ጎራ ብለው በዶይቼ ቬለ ዋናው የስርጭት ማዕከል ስቱዲዮ አነጋግረናቸው ነበር። በቅርቡ በዓለም የተፈጥሮ ቅርስ መዝገብ ውስጥ የሰፈረው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ረዥም ዓመታትን የወሰደ እና እጅግ አድካሚ ሂደት ማለፉን ይናገራሉ።
በ45ኛው የዓለም የቅርስ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ ካስመዘገበቻቸው ሁለት ቅርሶች አንደኛው የነበረው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እንደ ፓርክ የተቋቋመው በ1962 ዓ.ም ነው ። ፓርኩ 2,150 ካሬ ኪሎ ሜትር ቦታን የሚሸፍን ሲሆን በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ እንስሳት እና እጽዋትን በውስጡ አቅፏል። የባሌ ተራሮች ከባሕር ጠለል በላይ ከ1,500 እስከ 4, 377 ሜትር የሚደርስ ሲሆን÷ በኢትዮጵያ ሁለተኛው ትልቁ ተራራ ቱሉ ዲምቱ መገኛም ጭምር ነው፡፡
በብሔራዊ ፓርኩ ውስጥ በጥናት ከተለዩት 1,660 የእጽዋት ዝርያዎች ውስጥ 40 በመቶ የመድሃኒትነት ፋይዳ ያላቸው ስለመሆናቸው ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡
በሻሸመኔ አዳባ አድርገው የሰብስቤ ዋሻ አቀበትን ሲያያዙት የሚጀምረው የባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በተለይ ዲንሾ ሲደርሱ የሚቀበልዎት ቀዝቃዛ አየር፤ በአካባቢው የሚመረተውን የገብስ ቆሎ እየቆረጠሙ፣ ኩልል ብሎ የሚወርደውን የምንጭ ዉኃ እየተጎነጩ በተራሮች ስር የተነጠፉ ከሚመስሉ አረንጓዴ መስኮችን ሳር ሲግጡ እና ትንንሽ እንስሳት ሲያድኑ የሚታዩ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ እንስሳት እንደ ኒያላ እና ቀይ ቀበሮዎች ይታያሉ። ታሪካዊው የሸህ ሆጀሌ ችሎት አዳራሽ ዕድሜ ጠገብ ሆነው ሽበት ያበቀሉ እና በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ እንደ የኮሶ ዛፍ አይነት እና በሌሎች በርካታ ዕጽዋት የበለጸገው ፓርኩ አሁንም በኢትዮጵያ ብቻ በሚገኙ የአዕዋፋት ዝማሬ የተሞላውን የተፈጥሮ ገጸ በረከቶችን ሲመለከቱ ምነው ዩኔስኮ ዘገየ ያስብላል።ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊ እና ታሪካዊ ስፍራዎችን በምናብ በማስጎብኘት የሚታወቀው እና ተጓዡ ጋዜጠኛ የሚል ቅጽል ስም ያተረፈው ጋዜጠኛ ሄኒክ ስዩም እንደሚለው ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ያስመዘገበቻቸውን ሁለቱን ተፈጥሯዊ እና ባህላዊ ቅርሶች በተደጋጋሚ ጎብኝቷል። የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ካለው ድንቅ የተፈጥሮ መስህብነት አንጻር እስከ ዛሬም ድረስ በዩኔስኮ አለመመዝገቡ ያስቆጫል ባይ ነው።
የጌዴኦ መልክዓ ምድር በአብዛኛው ተራራማና ወጣ ገባ፣ በተወሰነ ደረጃ ደግሞ ሜዳማ የሆነ ገጽታ ያለው ተፈጥሯዊ አካባቢ ስለመሆኑ ይነገርለታል። የጌዴኦ ማኅበረሰብ በዚህ ወጣ ገባ የበዛበትን መልክዓ ምድር ለዘመናት የአፈር ደህንነቱን በጠበቀ መልኩ ጥምር እርሻ በማካሄድ ተፈጥሮን ተንከባክቦ ማቆየቱ ይነገርለታል። ለጌዴኦ ቡና፣ እንሰት እና ደን የሕይወቱ ቁርኝት ናቸው። ይህ ብቻም አይደለም። የጌዶዎች ለየት ያለ የእርሻ ልማዳቸው ፤ ጥንታዊ የቱቱ-ፈላ ትክል ድንጋዮች እና የድንጋይ ላይ ጥንታዊ ሥዕሎች ለቅርስ ምዝገባው ተመራጭ እንዳደረጓቸው የዩኔስኮ መረጃ ያመለክታል።ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ስለ ጌዴኦ ተናግሮ መጨረስ አይሆንለትም ። የጌዴኦ ማኅበረሰብ ባህላዊ ስረዓት አበጅተው የተፈጥሮ አካባቢያቸውን መጠበቃቸው እና ተምሳሌታዊነታቸውንም እንዲህ ይገልጸዋል።
እነዚሁ ባህላዊ እና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ከዚህ በኋላ የዓለም ቅርሶች ናቸው። ነገር ግን እንደሀገር ብሎም ለየአካባቢው ማኅበረሰብ የሚያመጧቸው ገጸ በረከቶች መዘንጋት እንደሌለባቸው ይነገራል።
አቶ ነጋ ወዳጆ እንደሚሉት የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በዓለም ቅርስነት መመዝገብ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ፣ ክልሉ ኦሮሚያ ብሎም ለባሌ አካባቢ ነዋሪ የሚያስገኘው ጥቅም በቀላሉ የሚታይ አይደለም ።
ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በበኩሉ የጌዴኦ ባህላዊ መልካዓ ምድር ለሀገርም ይሁን ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሚያመጣውን ትሩፋት ይገልጻል። ቅርስን መጠበቅ ማንነትን መጠበቅ
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የቅርስ መዝገብ ያስመዘገበቻቸው የሚዳሰሱ ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ ቅርሶቿን 11 በማድረስ በአፍሪቃ ቀዳሚ ሀገር ሆናለች ። ቀደም ሲል የላሊበላ ውቅር አብያተ ቤተክርስትያናት ፣ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ፣የፋሲል ግቢና ሌሎች የጎንደር ሐውልቶች፣ የአክሱም ሐውልቶች፣ የታችኛው አዋሽ ሸለቆ፣ የጢያ ትክል ድንጋይ፣ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ የአርኪኦሎጂ/የስነምድር/ ስፍራ፣ የሐረር ጀጎል ጥአሳሳቢው የቅርስ ምዝበራና የድረገጽ ላይ ሽያጭንታዊ ከተማ፣ የኮንሶ መልከዓ ምድር ፣ በዚህ ዓመት ደግሞ የጌዴኦ ባሕላዊ መልክዓ- ምድር እና የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በመዝገቡ ውስጥ የሰፈሩ ናቸው። በእንግሊዞች ተዘርፈው የነበሩ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ቅርሶች ተመለሱ
ኢትዮጵያ ያሏት ባህላዊ ፣ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ የሚዳሰሱ ቅርሶች እነዚህ ብቻም አይደሉም ። ሌሎች በርካታ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች ያሏት ቅርሶቹ ከሀገር አልፎ የዓለም እንዲሆን በርካታ ጥረቶች እና ሙከራዎች መቀጠላቸውን ሰምተናል። የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነጋ ወዳጆ እንደሚሉት በክልላቸው ብቻ በርካታ ቅርሶችን በዓለም አቀፉ መዝገብ ለማስፈር ጥረት እያደረጉ ነው።
ኢትዮጵያ የበርካታ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት እንደመሆኗ ፣ ቅርሶቹን በዓለም አቀፉ መዝገብ ለማስመዝገብ እና እውቅና ለመውሰድ የሚደረገውን ያህል ጥረት ጥበቃው እና እንክብካቤውም በዚያው ልክ ትኩረት እንደሚሻ ጋዜጠኛ ሄኖክ ተናግሯል።
ታምራት ዲንሳ
ሸዋዬ ለገሠ