1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዝደንት መፈታት ያስከተለው ቅሬታ

ሰኞ፣ መጋቢት 23 2016

መንግስት የሶማሌ ክልል የቀድሞ ርእሰ መስተዳድር አብዲ መሀመድ ዑመር ወይም በተለምዶ አብዲ ኢሌ በምሕረት ከእስር እንዲፈቱ ያሳለፈው ውሳኔ በደል የደረሰባቸውን ሰዎች ስሜት የጎዳ እና ፍትህ ያሳጣ ነው በሚል ቅሬታ ቀረበ።

https://p.dw.com/p/4eJn8
የሶማሌ ክልል የቀድሞ ርእሰ መስተዳድር አብዲ መሀመድ ዑመር መፈታት ቅሬታ አቅራቢ
መንግስት የሶማሌ ክልል የቀድሞ ርእሰ መስተዳድር አብዲ መሀመድ ዑመር ወይም በተለምዶ አብዲ ኢሌ በምሕረት ከእስር እንዲፈቱ ያሳለፈው ውሳኔ በደል የደረሰባቸውን ሰዎች ስሜት የጎዳ እና ፍትህ ያሳጣ ነው በሚል ቅሬታ ቀረበ።ምስል Messay Teklu/DW

የተበዳዮች ቅሬታ

በተለይ ምሕረቱ የተሰጠበትን ምክንያት «ለህዝብ ጥቅም» በሚል መገለፁ አግባብ አለመሆኑን የጠቀሱት አስተያየት ሰጭዎች ዳግም ፍትህን ማረጋገጥ እና የተለያየ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች መካስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በቀድሞው ርእሰ መስተዳድር አመራርነት ወቅት በጅግጅጋ ከተማ በነዋሪዎች ላይ በተፈፀመ ጥቃት አካላዊ ጉዳት እና ንብረት መዘረፋቸውን የሚገልፁት አስተያየት ሰጭ የግለሰቡ መፈታት ለተጎጅዎች ትክክለኛ ፍትህ አለመሆኑን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ መልኩ በከተማዋ በተፈፀመ ጥቃት «ጠዋሪ ልጄን አጥቻለሁ» ያሉ አስተያየት ሰጭ በወቅቱ ተፈፅመዋል ያሏቸውን ሌሎች ጥፋቶች በማንሳት በውሳኔው ላይ ያላቸውን ቅሬታ ገልጸዋል።

ከቅሬታ አቅራቢዎች አንዱ የሆኑት አቶ ማስሬ ኢብራሂም በበኩላቸው ስርዓቱ «በውሸት በተቀነባበረ ወንጀል የሞት ፍርድ እንዲፈረድብኝ አድርጓል» በዚህም ለ11 ዓመታት  ያህል በዝዋይ በእስር ቆይተው ስርዓቱ ሲቀየር መፈታታቸውን ተናግረዋል። 

በእሳቸው እና በሌሎች ላይ አስከፊ ሥራ ሰርተዋል ያሏቸው የቀድሞ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር «ለህዝብ ጥቅም ሲባል ተፈቱ የሚለውን መስማት እኛን በጣም ያሳምመናል» በማለት መንግሥት ሊወስዳቸው ይገባል ያሏቸውን ጉዳዮች አንስተዋል።

 Ehemalige Opferfamilien verurteilen Freilassung des ehemaligen somalischen Präsidenten
ምስል Messay Teklu/DW

በተመሳሳይ በቀድሞ  የሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳድር አብዲ ኢሌ ለደርሰባቸው በደል ፍትህ ሲጠብቁ እንደነበር የሚናገሩት አቶ አብዱላሂ ሀሰን አብዲ «ፍርድ ስንጠብቅ ግለሰቡ መፈታታቸውን ስሰማ የተሰማኝን ስሜት አሁን መግለፅ አልችልም» ብለዋል። በመንግሥት አካሄድ ግራ መጋባታቸውን በማንሳት።

 በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለማግኘት የእጅ ስልካቸው ላይ የደወልንላቸው የፍትህ ሚንስቴር የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ስልክ ብንደውልም ባለመነሳቱ ምላሽ ማካተት አልተቻለም።

ሂውማን ራይትስ ዎች የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳድር አብዲ መሀመድ ዑመር (አብዲ ኢሌ) ክስ እንዲቋረጥ መደረጉ የወንጀል ተግባርን  እንደማበረታታት እና እውቅና እንደ መስጠት የሚቆጠር ነው ሲል መተቸቱ ይታወሳል።

መሳይ ተክሉ

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ