የቀድሞው የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም «ፀደይ ባንክ» ሆኖ ተመሰረተ
ቅዳሜ፣ መስከረም 7 2015
የቀድሞው የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም (አብቁተ) ስያሜውን ፀደይ ባንክ በሚል ወደ ባንክ ማደጉን አስታወቀ፣ የባንኩ አካል የሆነውን ዘመናዊ የመረጃ ማዕክል ዛሬ አስመርቋል፡፡ በስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የኢፌድሪ ኢንፎርሜሽን ደህንነትአስተዳደር ምክትል ዳይሬክተር ትዕግስት አህመድ ፀደይ ባንክ ደህንነቱ የተጠበቀ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ባለቤት ሆኗል ብለዋል፡፡
የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም፣ የዛሬው ፀደይ ባንክ በ1988 ዓ ም “የገጠር ብድር አገልግሎት” በሚል በአማራ ክልል 6 ወረዳዎች ከ40 በማይበልጡ ሰራተኞችና ከ3 ሚሊዮን ብር በማይበልጥ ካፒታል ነው ስራውን የጀመረው፣ ተቋሙ ዛሬ ፅህፈት ቤቶቹን ወደ 500 ያሳደገ ሲሆን ሰራተኞቹም 13 ሺህ ተጠግተዋል፡፡ ጠቅላላ ሀብቱም ቢሆን ከ40 ቢሊዮን በላይ መሆኑን የባንኩ ኃላፊዎች ይናገራሉ፡፡
ተቋሙ የደረሰበትን እድገትና መስፈርት ተመልክቶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥር 20/2014 ዓ ም አብቁተን ወደ ባንክነት እንዲሸጋገር መፍቀዱን ለባንኩ የተሰጠው የምስክር ወረቀት ያሳያል፡፡
የተቋሙን ወደ ባንክነት መሸጋገሩን ከሚያመለክቱ ሥራዎች መካከል የፀደይ ባንክ የመረጃ ማዕከል ዛሬ በባሕር ዳር ተመርቋል፡፡
ግንባታውን በአማካሪነት ሲከታተል የነበረው የኢፌድሪ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ምክትል ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት አህመድ ባንኩ ደህንነቱን ማስጠበቅ የሚችል የቴክኖሎጂ ባለቤት ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
የፀደይ ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መኮንን የለውም ወሰን የመረጃ ማዕከሉ ከ370 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት አስረድተዋል፡፡
የፀደይ ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ፀደይ ባንክ በ11. 3 ቢሊዮን ብር ካፒታል ስራ መጀመሩን በስነስርዓቱ ላይ ተናግረዋል፡፡ ጠቅላላ የባንኩ ሀብት 40 ቢሊዮን ብር መድረሱንና 1.5 ሚሊዮን ደንበኞች እንዳሉት ነው አቶ ገዱ ያመለከቱት፡፡
“ … 11.3 ቢሊዮን ብር፣ ይዞ ወደ ገበያው የሚገባ ነው፣ የተጣራ ካፒታል፣ ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ ጠቅላላ ሀብት፣ 24 ቢሊዮን አሁን ያለ ቁጠባ እና 28.8 ቢሊዮን ብር በደንበኞች ላይ ያለ ብድር ይዞ ነው ወደ ባንክነት እየተሸጋገረ ያለው”
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ የባንክ ዘርፍ እጅግ እያደገ በመምጣቱ ፀደይ ባንክ ቀደም ሲል ያዳበረውን የስራ ልምድ ተጠቅሞ በገበያው ዘልቆ መታየት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ተቋሙ ስራውን ሲጀምር ሳንቲሞችን በቁጠባ እያሰባሰበ ጭምር እንደነበር የተናገሩት የፀደይ ባንክ ምክትል ስራ አስፈፃሚና ዋና የመረጃ ባለሙያ አቶ ተመስገን ገብረእግዚብሔር ሰራተኛውና ደንቦች የባንኩ እድገት አስደስቷአዋል ነው ያሉት፡፡
ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ በመልዕክታቸው ቀደም ሲል የነበሩ የአነስተኛና ብድር ተቋማት አገልግሎታቸውን ሳቋርጡ ለአርሶ አደሩና ለከተማ ነዋሪው እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ታምራት ዲንሳ