1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሸቀጦች ዋጋ ማሻቀብ በአማራ ክልል

ሐሙስ፣ የካቲት 21 2016

አንድ ኩንታል ጤፍ እስከ 15 ሺህ ብር መድረሱን የነገሩን ነዋሪ ዘይትም 5ቱ ሊትር ከአንድ ሺህ ብር በላይ መድረሱን፣ጤፍ በኩንታል 11 ሺህ የነበረው አሁን 14 ሺህ፣ 15 ሺህ መድረሱን፣ ስኳር አንዱ ኪሎ አሁን 130 ብር እንደሚሸጥ፣ ዘይት 5 ሊትር ወደ 850 ብር የነበረው ዛሬ ላይ እስከ 900 ብር፣ እስከ 1 ሺህ ብር ደርሷል ብለዋል።

https://p.dw.com/p/4d2JZ
Ätiopien | Markt in Bahir Dar
ምስል Alemenew Mekonnen/DW

የአንድ ኩንታል ጤፍ ዋጋ እስከ 15 ሺህ ብር ደርሷል

በአማራ ክልል የሸቀጦች ዋጋ አሻቅቧል

የመንገዶች መዘጋጋትና በክልሉ ያለው ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ ምርት ወደ ገበያ እንዲደርስ ማድረግ ባለመቻሉ በከተሞች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ነዋሪዎችና ለመንግስት ሰራተኛው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት እንዲፈጠርበት ምክንት መሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ፣ ካለው የፀጥታ ሁኔታ አኳያ አርሶ አደሩ ምርት ወደ ገበያ ማውጣት እንዳልቻለም ነዋሪዎች ይገልፃሉ።  የኑሮ ውድነቱ በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን እየተፈታተነ እንደሆነ ነው ነዋሪዎቹ የሚገልፁት።

የኑሮ ውድነት በአማራ ክልል

በሰሜን ሸዋ ዞን የሸዋሮቢት ከተማ ነዋሪ ለዶይቼ ቬሌ እንደተናገሩት ባለፈው የካቲት 16/2016 ዓ ም የማዕከላዊ ሸዋ እዝ ጣቢያ (Command Post) ከደብረብርሀን ወደ ደሴና ከደሴ ወደ ደብረብርሀን የሚወስደው መስመር ለተሸከርካሪ ዝግ መሆኑን ካሳወቀ በኋላ አሁንም መንገዱ አልተከፈተም፡፡  ይህም የገበያውን ሁኔታ አንሮታል ብለዋል፡፡በከተማዋ ያሉ ባንኮችም ዛሬ አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ እኚሁ ነዋሪ አመልክተዋል፡፡

“... ግማሹ ቆሎ፣ ግማሹ ንፍሮ፣ ግማሹ ድንች ሸጦ ነው የሚኖረው፣ ይህ መንገድ ሲዘጋ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እየሆነ ነው ያለው፣ ለማነኛውም መንግስት የሚችለውን ሁሉ አድርጎ መንገዱን ሰላም  ማድረግ (መክፈት) አለበት፣ አለዚያ ብዙ ማህበረሰብ ይጎዳል ብየ አስባለሁ፣ ባንኮቹ አሁንም ዝግ ናቸው፣ የኑሮ ውድነቱ በተለይ መንገድ ሲዘጋጋ የዘይቱ፣ የስኳሩ፣ የጨው ዋጋ ሁሉ ይንራል፣ ዘይት አሁን ከ800 ብር ወደ 1ሺህ 100 ብር ደርሷል፡፡” ብለዋል፡፡

አትክልትና ፍራፍሬ በባህር ዳር ገበያ
አትክልትና ፍራፍሬ በባህር ዳር ገበያምስል Alemenew Mekonnen/DW

በምስራቅ ጎጃም ዞን የቢቸና ከተማ ነዋሪ “ትዕዛዙ” ከየት እንደመጣ ባያውቁም፣ ካለፉት 3 ቀናት ጀምሮ ከከተማዋ የሚወጣም ሆነ ወደ የሚገባ ተሸከርካሪ የለም ነው ያሉት፣ በዚህም ምክንት የእለት ኑሯቸውን በተለያዩ መንገዶች ተሯርጠው የሚመሩ ሰዎች ለችግር መዳረጋቸውን ገልጠዋል፡፡

“እታች ያሉ የቀን ሰራተኞች የኑሮ ውድነቱ ብቻ ሳይሆን ሥራ የለም፣ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ስላልገባ እታች ላይ ያሉ ማህበረሰቦች ከእነርሱ ላይ ጉዳት አለ፡፡” ሲሉ ገልፀዋል፡፡

የአንድ ኩንታል ጤፍ ዋጋ እስከ 15 ሺህ ብር ደርሷል

 

አንድ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪም፣ የምርቶች ዋጋ በማይታመን ሁኔታ ማሻቀቡን ነው የገለፁት፣ የአንድ ኩንታል ጤፍ ዋጋ እስከ 15 ሺህ ብር መድረሱን የነገሩን እኚሁ ነዋሪ ዘይትም 5ቱ ሊትር ከአንድ ሺህ ብር በላይ መድረሱን አስረድተዋል፡፡ነዋሪዋ አያይዘውም፣ “ጤፍ በፊት በኩንታል 11 ሺህ ይባል የነበረው አሁን 14 ሺህ፣ 15 ሺህ ነው የሚባለው፣ ስኳር አንዱ ኪሎ 130 ብር ነው አሁን የሚሸጠው፣ ዘይት 5 ሊትር ወደ 850 ብር የነበረው ዛሬ ላይ እስከ  900 ብር፣ እስከ 1 ሺህ ብር ደርሷል፣ የቀን ስራ ከእጅ ወደ አፍ ነው፣ በዚህ ላይ የቤት ኪራይ ይከፍላሉ፣ እነሱ ናቸው (የቀን ሰራተኞች) በጣም እየተጎዱ ያሉት፣ ገበያው ጫና እያደረገ ያለው በቀን ሰራተኛውና በዝቅተኛ የገቢ ምንጭ ባላቸው ወገኖች ላይ ነው፡፡”ማኅበረሰቡን የፈተነዉ የኑሮ ዉድነት

የጥራጥሬዎች ገበያ በባህር ዳር
የጥራጥሬዎች ገበያ በባህር ዳርምስል Alemenew Mekonnen/DW

በምዕራብ ጎጃም ዞን የፈረስ ቤት ከተማ ነዋሪም መንገድ ከተዘጋ 3 ቀናት መሆኑን ጠቁመው ምርት ገበያ ላይ ባለመኖሩ ህዝቡ ተቸግሯል ነው ያሉት፡፡“ህዝቡ ተቸግሯል፣ መንገድ የተዘጋ ሰሞኑን ነው ዛሬ 3ኛ ቀኑ ነው፣ ማን እንደዘጋው አላውቅም የጊዜ ገደብ ካለው ሊከፈት ይችላል፣ ግን ኤታወቅም፣ ለምግብ ፍጆታ የሚውሉ ሸቀጦች በውድም ቢሆን ቢገዙ ጥሩ ነበር ግን ገበያ ላይ ማግኘት አይቻልም” በሰሜን ጎጃም ዞን የመረዓዊ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው ባለው የመንገዶች መዘጋጋትና  የሰላም እጦት ምክንያት የመንግስት ሰራተኛውና  በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደረው ህዝብ ኑሮውን ለመምራት ፈተና ሆኖበታል ብለዋል፡፡

“ጤፍ 9ሺህ ብር የነበረው  አሁን 13 ሺህ ብር ገብቷል፣ ቦቆሎ ከ2ሺህ800 ብር ወደ 3ሺህ 200 ብር ከፍ ብሏል፣ የከተማዋ ነዋሪ አሁን ከባድ ፈተና ውስጥ ገብቷል፣ ዝቅተኛ ነዋሪውም የመንግስት ሰራተኛውም በኑሮ ወድነቱ ተጎድቷል፣  ህዝቡ በጣም እየተሰቃየ ነው፡፡” ሲሉ ነው አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬሌ የተናገሩት፡፡

በአማራ ክልል በመንግስት የፀጥታ ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተጀመረውና 7ኛ ወሩን እያገባደደ የሚገኘው ግጭትና ጦርነት የብዙዎችን ህይወት ቀጥፎና በርካቶችን የአካል ጉዳተኛ አድርጎ አሁንም መቋጫ አላገኘም፡፡ በተከሰተው የፀጥታ መደፍረስ ምክንያት  የአማራ ክልል ከሐምሌ 2015 ጀምሮ ለ6 ወራት በአስቸኳ ጊዜ አዋጅ ስር ቆየ ሲሆን የጊዜ ገደቡ ከተጠናቀቀ በኋላ ለሌላ የ4 ወራት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር እንዲቆይ ተወስኗል፡፡

ዓለምነው መኮንን

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ