1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኑሮ ውድነት በአማራ ክልል

ማክሰኞ፣ መጋቢት 5 2015

የምግብ ዋጋ በመጨመርና የአቅርቦት እጥረት የከተማ ነዋሪዎችን ኑሮ ፈታኝ እዳደረገው ሸማቾች ተናገሩ፣ አርሶ አደሮች ምርት የማናወጣው የግብርና ግብዓቶች ዋጋ በመጨመሩ ነው ይላሉ፣ የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ በበኩሉ ችግሩ ሰው ሰራሽ ነው ይላል፣ በምግብ እህል ዘርፍ ፈቃድ የተሰጣቸው ደላሎችም ፈቃዳቸው እንደሚሰረዝ ቢሮው አመልክቷል፡፡

https://p.dw.com/p/4OfLt
Ätiopien | Markt in Bahir Dar
ምስል Alemenew Mekonnen/DW

የኑሮ ውድነት በአማራ ክልል

የምግብ ዋጋ በመጨመርና የአቅርቦት እጥረት የከተማ ነዋሪዎችን ኑሮ ፈታኝ እዳደረገው ሸማቾች ተናገሩ፣ አርሶ አደሮች ምርት የማናወጣው የግብርና ግብዓቶች ዋጋ በመጨመሩ ነው ይላሉ፣ የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ በበኩሉ ችግሩ ሰው ሰራሽ ነው ይላል፣ በምግብ እህል ዘርፍ ፈቃድ የተሰጣቸው ደላሎችም ፈቃዳቸው እንደሚሰረዝ ቢሮው አመልክቷል፡፡ 
ወ/ሮ ህይወት አበበ እንደሚሉት ከቅርብጊዜ ወዲህ የምግብ እህል ዋጋ በማይታመን ሁኔታ ጨምሯል፣ ለመንግስት ሰራተኛውና ለዝቅተኛ ነዋሪው ኑሮ ፈተና ሆኖበታል ነው ያሉት፣ ለዋጋው መጨመር ዋናው ምክንት የምርት እጥረት እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ 
“ጤፍ በኩንታል 5000 ብር እንገዛ የነበረው አሁን ከ7500 እስከ 8000 ብር ይባላል፣ ከ3000 ብር እስከ 4000 ብር እንገዛ የነበረው ወደ 6000 ብር አድጓል፣ ምክንቱ ደግሞ ጤፍ ከቦታው (ከገበሬው) አይመጣም ነው፣ ኑሮ ለመንግስት ሰራተኛውና ለዝቅተኛ ነዋሪው ከብዷል፣ ፓስታና መኮሮኒ 40ና 50 ብር በኪሎ ነበር፣ አሁን 70 እና 80 ብረ በኪሎ ሆኗል ” 
በአማራ ክልል የምዕራብ ጎጃም አንድ አርሶ አደር ለዶይቼ ቬሌ እንደተናገሩት መንግስት የግብርና ምርቶችንና የሸቀጦችን ዋጋ ስለጨመረብን እህል ወደ ገበያ ለማውጣት ፍላጎት የላቸውም፡፡ 
“… ማዳበሪያ ይፈታ (ዋጋው ይቀንስ) የሱቅ እቃም … የእኛ እህል እየተሸጠ የነሱ (የመንግስት አቅርቦት) ዋጋው እያሻቀበ ነው፣ እና እናቁም ነው አዎ በዚያ ነው እህል ወደ ገበያ የማይወጣው፡፡” 
በጤፍ ንግድ የተሰማሩ አንድ ነጋዴ በበኩላቸው ምርት ከቦታ ቦታ እንዳይዘዋወር ንግድ ቢሮ ክልከላ በማድረጉ የእህል ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ 
በአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የገበያ ጥናት ባለሙያ ወ/ሮ ጤና ደጉ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የምግብ እህል ዋጋ እየጨመረ እንደሆነ ዘርዝረዋል፡፡ 
“አንደኛ ደረጃ ጤፍ በኩንታል 5000 ብር የነበረው 7500 ብር፣ ሰርገኛ ጤፍ 4300 የነበረው 6500 ነው፣ ዳጉሳ በኪሎ 30 ብር የነበረው 42 ብር ገብቷል፣ ማሽላ ከ29 ብር 32 ብር፣ ነጪ ሽንኩርት ከ100 ብር 180 ብር ደርሷል፡፡” ብለዋል፡፡ 
የአማራ ክልል ገበያ ልማት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አቢታ ገበያው ዓለማ አቀፋዊ የምርት እጥረት፣ የምርት ምርት በህገወጥ ነጋዴው መደበቅ፣ ህገወጥ ንግድ መበራከት፣ የህገወጥ ደላላ ሥራና የፖለቲካል ኢኮኖሚ የገበያ ሻጥር ገበያውን ረብሾታል ብለዋል፣ ችግሩ እንዲፈታ ደግሞ እየተሰራ እንደሆነ አብራርተዋል፡፤ 
“የቁጥጥር ሥራውን ከታች እስከላይ ያለው ጥምር ግብረ ኃይል ህገወጥ ንግድና ቁጥጥር ፀረ ኮንትሮባንድና ግብረ ኃይል በማጠናከር እንደገና የተቋሙን ቁጥጥር ደግሞ ቀን ከቀን እየፈተሸ አስፈላጊው እርምጃ እየተወሰደ ነው፣ በርካታ ክስ የተመሰረተባቸው፣ በህግ እርምጃ የተወሰደባቸው፣ ፈቃዳቸው የተወሰደባቸው፣ ማስጠንቀቂያ የመስጠት፣የማሸግ ሥራ የተሰራባቸው አሉ፡፡” 
በምግብ ሸቀጦች ዙሪያ ፈቃድ የተሰጣቸው ደላሎች ፈቃዳቸውን ባግባቡ ተጠቅመው ባለምስራታቸው፣ ፈቃዳቸው የሚሰረዝ እንደሚሆን አቶ አቢታ አመልክተዋል፡፡ 
“በምግብ ምርቶች ላይ ደላላ የሚባል ፈቃድ መስጠት እንዲቆም ስምምነት ላይ ተደርሷል፣ ደላላ አምራችና ነጋዴው፣ ሻጪና ገዥ እንዳይገናኝ እያደረገ፣ ያለ አግባብም እየበለፀገ ነው፣ መስራት ከፈለገ በሌላ የስራ መስክ ይሰማራል፣ አምራችና ነጋዴ፣ አምራችና ገዥ በቀጥታ መገናኘት አለባቸው፣ ያለፈቃድ ሲሸጥ፣ ምርት ሲያዘዋውር የተገኘ ማንኛውም አካል እርምጃ የሚወሰድበት ይሆናል” ነው ያሉት፡፡ ቢሮው ገዥና ሻጪን ማገናኘት ዓላመው ሆኖ ሳለ ያልተጨበጠ አሉባልታ የሚያወሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፣ ምርት ወደየትኛውም የአገሪቱ ክፍል እንዳይዘዋወር ያለው ነገር ለም፣ ቢሮው ምርት ወደ ገበያ እንዳይወጣ አድርጓል የሚለው ስሞታ ከእውነት የራቀ ነው ብለዋል፣ ይህን አሉባልታ የሚያስወሩትም ጥቅማቸው የተጓደለባቸው ናቸው ይላሉ፡፡ 
“ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምርት እንዳይወጣ እያደረገ ነው በማለት አሉባልታ የሚያስወራው ሳይሰራ ቁጭ ብሎ የሚበላው ደላሎች፣ ህገወጥ ነጋዴዎችና የፖለቲካል ኢኮኖሚው አሻጥረኞች ናቸው” 
ያለውን የምርት እጥረትና የዋጋ መጨመር ለመከላከል የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት ምርቶችን ለተጠቃሚው እንዲያቀርቡም ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ኃላፊው ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡ 

Ätiopien | Markt in Bahir Dar
የአማራ ብሔራዊ ክልላዎ መንግሥት ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምስል Alemenew Mekonnen/DW
Ätiopien | Markt in Bahir Dar
ገበያ በባህርዳር ገበያምስል Alemenew Mekonnen/DW


ዓለምነው መኮንን 


ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
አዜብ ታደሰ