1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የርዋንዳ የዘር ማጥፋት ሰላሳኛ ዓመት ሲዘከር

ቅዳሜ፣ መጋቢት 28 2016

እሁድ መጋቢት 29 ቀን 2016 ዓ/ም በጎርጎርሳውያን የቀን ቀመር ኤፕሪል 7 ቀን ርዋንዳውያን በታሪካቸው የጨለማውን ጊዜ ይዘክራሉ ። አብዛኞቹ አናሳ የቱትሲ ጎሳ አባላት የሆኑ እና ከ1 ሚሊዮን በላይ ርዋንዳዊያን በማንነታቸው ብቻ እየተለዩ የዘር ጭፍጨፋ የተፈጸመባቸው ቀን ነው።

https://p.dw.com/p/4eUvC
Reclaiming History - Völkermord in Ruanda 1994
ርዋንዳ ሰላሳኛውን ዓመት የጅምላ ጭፍጨፋ እየዘከረች ነው ምስል Sayyid Azim/AP Photo/picture alliance

በርዋንዳ የጅምላ ጭፍጨፋ ሰላሳኛ ዓመት ይዘከራል

ነገ እሁድ መጋቢት 29 ቀን 2016 ዓ/ም በጎርጎርሳውያን የቀን ቀመር ኤፕሪል 7 ቀን ርዋንዳውያን በታሪካቸው የጨለማውን ጊዜ ይዘክራሉ። አብዛኞቹ አናሳ የቱትሲ ጎሳ አባላት የሆኑ  እና ከ1 ሚሊዮን በላይ ርዋንዳዊያን በማንነታቸው ብቻ እየተለዩ የዘር ጭፍጨፋ የተፈጸመባቸው ቀን ፤ እነዚህን ከሞት መልዓክ ለማምለጥ ይሸሹ የነበሩትን ለማስመለጥ አልያም ለማስጠለል የሞከሩ ለዘብተኛ የሁቱ ጎሳ አባላትም ቢሆን ለአናሳዎቹ የመጣባቸው አልቀረላቸውም ፤ እነርሱም ከብዙ በጥቂቱ ልክ እንደእነዚያ ተቆጥረው የጭካኔው በትር ቀማሽ ሆኑ እንጂ።

ይህ ምናልባትም ዓለማችን ካስተናገደቻቸው እና በሰው ልጆች ላይ ከተፈጸሙ የዘር ማጥፋት የጭካኔ ተግባራት አንዱ ተደርጎ የሚወሰደው የርዋንዳው የ100 ቀናት የዘር ማጥፋት ዘመቻ ሲጀመር ነገ እሁድ ድፍን ሰላሳ ዓመት ይሞላዋል። 

ዕለቱ ከርዋንዳውያን ባሻገር በ,ዓለማቀፍ ደረጃ ትልቅ ስፍራ ይሰጠዋል። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም  የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዕለቱን በተለያዩ ስነስረዓቶች ለመዘከር ማቀዱን አ,ስታውቋል። ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ ይህንኑ በተመለከተ ባወጡት መግለጫ «የዘር ማጥፋት ወንጀሉ የተፈጸመባቸውን መቼም አንረሳቸውም፤ ከዚያ የጭካኔ ተግባር በተአምር የተረፉትን ጀግንነት እና ጽናትም እንዲሁ » ብለዋል። 

ከሩዋንዳዉ አስከፊ ታሪክ ምን እንማር?

የቱትሲ ጎሳ አባል የሆነው ፍሬዲ ሙቱንጋ ከጭፍጨፋው በተዓምር ከተረፉቱ አንዱ ነው። 18 ዓመቱ ነበር ከመዲናዋ ኪጋሊ 130 ኪሊ ሜትሮች ርቀት ላይ በምትገኘው ሙሹባቲ በተሰኘች መንደር  ከትምህርት ቤት ለእረፍት  ቤት እያለ ነበር ጭፍጨፋው የተጀመረው። የሁቱ ጽንፈኞች በዋነኛነት የአሁኑ የሀገሪቱ ፕሬዘደንት ፖል ካጋሜ ይመራ የነበረውን የወቅቱ የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር (አር ኤፍ ፒ)  የተባለውን የቱትሲ አማፂ ቡድን አባላት አልያም ይደግፋሉ ያሏቸውን ወጣቶች ያድኑ ነበር ።  

በዘር ጭፍጨፋው ሰላባ ከሆኑ ቤተሰቦች መካከል ጥቂቶቹ
እሁድ መጋቢት 29 ቀን 2016 ዓ/ም በጎርጎርሳውያን የቀን ቀመር ኤፕሪል 7 ቀን ርዋንዳውያን በታሪካቸው የጨለማውን ጊዜ ይዘክራሉ ። አብዛኞቹ አናሳ የቱትሲ ጎሳ አባላት የሆኑ  እና ከ1 ሚሊዮን በላይ ርዋንዳዊያን በማንነታቸው ብቻ እየተለዩ የዘር ጭፍጨፋ የተፈጸመባቸው ቀንምስል Samuel Ishimwe/DW

ከተደቀነበት አስከፊ ሁኔታ ያመልጥ የሙታንጓ እናት ልጃቸው  ሁቱ ከሆነው እና የትምህርት ቤት ጓደኛው ከሆነ ልጅ ቤት እንዲደበቅ መከሩት ። በእርግጥ እናት እንዳሰቡት የልጃቸው ህይወት በቅርብ ርቀት በሚገኙ ለ,ዘብተኛ ሁቱ ቤተሰቦች ተርፎላቸዋል። 

ነገር ግን በቅርብ ርቀት ላይ የነበሩ ቤተሰቦቹ ለሳምንት ያህል ለጽንፈኞቹ ሁቱዎች ገንዘብ እና የአልኮል መጠጦችን እያቀረቡላቸው በህይወት መቆየት ቢችሉም ፤ የነበራቸውን ሰጥተው በመጨረሳቸው ከተደገሰላቸው ሞት ማምለጥ አልቻሉም ፤ እርሱን ያስመለጡት እናቱን ጨምሮ አባቱ እና እህቶቹ ሁሉ የችካኔ እርምጃ ተወሰደባቸው። 
«ወንድሞቼ እና እህቶቼ ያለ ርህራሄ ሲገደሉ የሚያሰሙትን የሰቆቃ ጩኸት እሰማ ነበር፣ ለጥቃት አድራሾች ዳግመኛ ቱትሲ እንደማይሆኑ እና ነፍሳቸውን እንዲያተርፉላቸው ሲማጸኗቸው ነበር ። ይህ ሁሉ ግን በከንቱ ነበር።»

ከሊቢያ ወደሩዋንዳ የተወሰዱ ስደተኞች
ማቲንግዋ ግን እዚያው ጓደኛው ቤት እንደተሸሸገ ነበር ። ከዚያ እንድ እርምጃ ቢራመድ በዙሪያው ካደባው ሞት ሊያስመልጠው የሚችል አንዳችም ኃይል አልነበረም። 
«እህቶቼን በአቅራቢያው ወደሚገኝ ጉድጓድ ውስጥ ጥለው ጥቂት ነብሳቸው ገና በህይወት የነበሩትን ደግሞ በድንጋይ ጨረሷቸው። ታናናሽ እህቶቼ የ4 ፣ 6 ፣ 11 እና 13 ዓመት ዕድሜ ብቻ ነበራቸው ። ወላጆቼም  በገጀራ ተገድለዋል፣ ከተደበቅኩበት ቦታ ብቅ ብል  ለእኔ ግደሉኝ እንደማለት ነው። »ወጣቱ ማቱንጓ በመቶ ቀናቱ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ከቤተሰቦቹ በተጨማሪ ከ80 በላይ ዘመድ አዝማዱን አጥቶበታል። 

ይህ አሰቃቂ የዘር ጭፍጨፋ ከተፈጸመ እነሆ 30 ዓመት ሞላው ፤ ቀናት ለሳምንታት ፤ ሳምንታት ለወራት ብሎም ለዓመታት  እየተቀባበሉ ሶስት አስርት ዓመታት አለፉ ። ነገር ግን ከዚያ አስከፊ የግፍ ጭፍጨፋ በተዓምር  የተረፉቱ ሩዋንዳውያን ከዚያ ሰቆቃ ለማገገም በርግጥ እጅግ አስቸጋሪ ጊዜ አሳልፈዋል። 

ሩዋንዳ ከሰቆቃው በህይወት በተረፉት እና የዘር ማጥፋት ወንጀል በፈጸሙቱ መካከል እርቅ እንዲፈጠር ጥረት ብታደርግም እንደ ሙታንጉሃ እና እህቱ ሮዜት ላሉ ሰዎች  የፈውስ እና የማገገም ጉዞው እጅግ አስቸጋሪ መንገድ ሆኖባቸው ቆይቷል። በተለይ ማቲንጉዋ እንደሚለው ከቤተሰቦቹ ገዳዮች አንዱ የዘር ጭፍጨፋው የተደረገበትን ሂደት አብዛኛውን መረጃ መስጠት አለመፈለጉ ለደረሰበት ጉዳት ህሊናውን እንዳያሳርፍ አድርጎታል። 

የሩዋንዳው የጅምላ ጭፍጨፋ ሰዎች ቅሪተ አካል
ሩዋንዳ ከሰቆቃው በህይወት በተረፉት እና የዘር ማጥፋት ወንጀል በፈጸሙቱ መካከል እርቅ እንዲፈጠር ጥረት ብታደርግም እንደ ሙታንጉሃ እና እህቱ ሮዜት ላሉ ሰዎች  የፈውስ እና የማገገም ጉዞው እጅግ አስቸጋሪ መንገድ ሆኖባቸው ቆይቷል። ምስል SIMON MAINA/AFP

«ወንጀለኞች ብዙውን ጊዜ እውነቱን ስለማይናገሩ እርቅ ለመፍጠር የሚደረጉ ጥረቶችን የሚያደናቅፍ ነው። ይህ ደግሞ በሕይወት የተረፉትን የሚረብሽ ነው»
ርዋንዳ እንደ ሃገር በተጎጂዎች እና ጥፋተኞች መካካል ያደረገችውን ጥረት ልክ እንደ ሙታንጉሃ ሁሉ በለንደን የምስራቅ እና አፍሪካ ጥናት ትምህርት ቤት (SOAS የዓለምአ,ቀፍ ፖለቲካ ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ፊል ክላርክ  ይጋራሉ። በተለይ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት በርዋንዳ የተከናወኑ ጥረቶችን በቅርበት መከታተላቸውን የሚገልጹት ምሁሩ መሻሻሎች እንዳሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። 
« በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የተፈረደባቸው የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈፃሚዎች ዛሬ ተመልሰው ወንጀል በፈጸሙባቸው ማህበረሰቦች ውስጥ ከዘር ማጥፋት የተረፉ ወገኖች ጋር ጎን ለጎን እየኖሩ መሆኑን ስታስብ ሩዋንዳ ከዘር ማጥፋት በኋላ በተደረገው የእርቅ ሂደት ትልቅ እመርታ አሳይታለች።»

በርዋንዳ ከዘር ማጥፋት አስተሳሰብ ለመላቀቅ በመንግስት፣ በሲቪል ማህበረሰብ እና በአጠቃላይ በዜጎች ዕለት ተዕለት በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል ። ነገር ግን ሁሉንም ሰው በንጹህ ልብ ለማቀራረብ የሚያስፈልገውን ለውጥ ለማምጣቱ ያጠራጥራል።

የጅምላ ጭፍጨፋ ሰለባዎች አልባሳት
በርዋንዳ ከዘር ማጥፋት አስተሳሰብ ለመላቀቅ በመንግስት፣ በሲቪል ማህበረሰብ እና በአጠቃላይ በዜጎች ዕለት ተዕለት በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል ። ነገር ግን ሁሉንም ሰው በንጹህ ልብ ለማቀራረብ የሚያስፈልገውን ለውጥ ለማምጣቱ ያጠራጥራል። ምስል DW

 የሩዋንዳ ዘር ጭፍጨፋ 25ኛ ዓመት መታሰቢያ

ሳምንታዊ የውይይት ክበቦች እና በማህበረሰብ ደረጃ የተዋቀሩ ማኅበራት ሰዎች ያለፉትን እና የአሁን ግጭቶችን እየተወያዩ ለሩዋንዳውያን ዘላቂ እርቅ እና የልብ ፈውስ  በአዎንታዊ መልኩ እንዲራመዱ በመርዳት ረገድ በእርግጥ አሁንም እጅጉን  አስፈላጊ ናቸው።
በርዋንዳ ያለው ተጨባች ሁኔታ ከዛሬ አምስት እና አስር አመታት በፊት ከነበረው በእርግጥ በእጅጉ የተሻለ ነው። ይህንን ሩዋንዳውያኑም ሆኑ ዓለማቀፍ ታዛቢዎች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ። 

በአንዲት ጥቁር ቀን መላ ቤተሰቦቹን ያጣው ሙቱንጓ የርዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ በመላው ዓለም እንዲዘከር ፍላጎቱ ነው።  
«ከ30 ዓመታት በፊት በሩዋንዳ የተከሰተውን ነገር ማስታወስ ከዘር ማጥፋት ለተረፉ ቱትሲዎች ጠቃሚ ነገር ሆኖ አይደለም ፤  ነገር ግን ይህ በሰው ልጆች ላይ የተፈፀመ ወንጀል በመሆኑ መላው ዓለም እንዲማርበት እንጂ።»

ታምራት ዲንሳ

እሸቴ በቀለ