1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በትግራይ ለተከሰተዉ ረሃብ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ተጠየቀ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 29 2016

በትግራይ የሚንቀሳቀሱ 72 ሲቪል ተቋማት የፌደራል መንግስት በትግራይ ለተከሰተዉ ረሃብ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ሁኔታውን በማጣጣል ተግባር ላይ ተጠምዷል ሲሉ ወቀሱ። የዓለምአቀፍ ማሕበረሰቡ እና የኢትዮጵያ መንግስት አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጡ ተቋማቱ ጠይቀዋል። በትግራይ እና አማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች አብዛኛው ማሕበረሰብ ለረሃብ አደጋ ተጋልጧል።

https://p.dw.com/p/4azD8
በትግራይ የሚንቀሳቀሱ 72 ሲቪል ተቋማት መግለጫ በመቀለ
በትግራይ የሚንቀሳቀሱ 72 ሲቪል ተቋማት መግለጫ በመቀለምስል Million Hailesilassie/DW

አስከፊ የረሃብ አደሃ በትግራይ እና አማራ ክልሎች

በትግራይ የሚንቀሳቀሱ 72 ሲቪል ተቋማት የፌደራል መንግስት በትግራይ ላለው ረሃብ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ሁኔታው የማጣጣል ተግባር ላይ ተጠምዷል በማለት ወቀሱ። የዓለምአቀፍ ማሕበረሰቡ እና የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ያለው አስከፊ ረሃብ በመገንዘብ አስቸኳይ ምላሽ ሊሰጡ ይገባል ሲሉም ሲቪል ተቋማቱ ጥሪ አቅርበዋል። 

ያለፈው የክረምት ወቅት በትግራይ እና አማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የዝናብ ሽፋኑ አነስተኛ መሆኑ ተከትሎ፥ ዝናብ ላይ ጥገኛ የሆነው አብዛኛው ማሕበረሰብ ለረሃብ አደጋ ተጋልጦ ይገኛል። እንደ የፌደራሉ መንግስት አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን መረጃ በትግራይ 2 ነጥብ 2 ሚልዮን ዜጎች በድርቅ ምክንያት ለረሃብ አደጋ ተጋልጠው ያለ ሲሆን፥ በአማራ ክልል ደግሞ እንዲሁ በ23 ቀበሌዎች የሚገኙ 2 ነጥብ 4 ሚልዮን ዜጎች እርዳታ ፈላጊ መሆናቸው ይገልፃል።

ፌድራል መንግሥት የኮምዩንኬሽን አገልግሎት የሰጠውን መግለጫ እንዲያርም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጠየቀ

የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በትግራይ ድርቅ የፈጠረው ረሃብ በክልሉ ከፍተኛ አደጋ ደቅኖ ያለ መሆኑ የሚገልፅ ሲሆን እስካሁን ካስከተለው ጥፋት በዘለለ፥ አስቸኳይ ምላሽ ካላገኘ በታሪክ ከሚታወቁ የድርቅና ረሃብ ክስተቶች ሁሉ የከፋ ስብአዊ ቀውስ በትግራይ የሚከሰትበት አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችል ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ 72 ሲቪል ማሕበራት በትግራይ ላለው ረሃብ የወለደው ሰብአዊ ቀውስ ተገቢው ምላሽ እየሰጠ አይደለም በማለት የፌደራል መንግስቱ ወቅሰዋል። የሴቶች እና ወጣቶች ነፃ ማሕበራት ጨምሮ የተለያዩ የሙያ ማሕበራት እና ሌሎች በአጠቃላይ 72 ሲቪል ማሕበራት ያቀፈው የትግራይ ሲቪል ማሕበረሰብ ተቋማት ሕብረት እንደገለፀው፥ በጦርነት እና በሙሉ መዘጋት የነበረው የትግራይ ህዝብ አሁን ደግሞ ለድርቅ ተጋልጦ፣ በየዕለቱ በርካቶች በረሃብ ምክንያት እየሞቱ ነው ይላል።

የትግራይ ክልል ብድር ጠየቀ፣ ደሞዝ መክፍል ተስኖታል

በትግራይ በየወረዳው ከአንድ መቶ በላይ ሰዎች የሚሞቱበት አጋጣሚ እየታየ ነው የሚሉት የትግራይ ሲቪል ማሕበራት ሕብረት ስራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ በርሃ፥ ይህ ሆኖ እያለ በአንዳንዶች ዘንድ ችላ ማለት እና የሰዎች ሕልፈት እንደተራ ነገር አድርጎ የማቅረብ አዝማሚያ መታየቱ አሳሳቢ ነው ይላሉ። አቶ ያሬድ "በትግራይ ያለው የድርቅ ሁኔታ በአግባቡ አለመረዳት፣ የሚረዱ ቢኖሩ እንኳን መጠራጠር ወይም ደግሞ ሆን ብሎ በሚፈለገው መጠን ችግሩ እንዳይወጣ በሚመስል መንገድ ማጣጣል እየታየ ነው" ብለዋል።

ሲቪል ማሕበራቱ፥ በትግራይ ያለው አስከፊ ሰብአዊ ሁኔታ ትክክለኛ መልኩ እንዳይታወቅ በማድረግ ደግሞ የፌደራል መንግስቱ ባለስልጣናት ወቅሰዋል። የትግራይ ሲቪል ማሕበራት ሕብረት ስራአስኪያጅ አቶ ያሬድ በርሃ "በኢትዮጵያ መንግስት አንዳንድ ባለስልጣናት ጨምሮ በተለያዩ ሌሎች አካላት፥ በትግራይ ተከስቶ ያለው ረሃብ የተለየ ትኩረት የማያስፈልገው አስመስሎ ለህዝብና ለዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ መግለፅ፥ መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር የማይሄድ በመሆኑ በፍጥነት መታረም አለበት" ይላሉ።

በትግራይ የረሃብ አደጋ
በትግራይ የረሃብ አደጋ ምስል Million Haileselassie Brhane/DW

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከዚህ ቀደም በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ በትግራይ የሚገኙ ዜጎችም ቢሆን በአሁኑ ወቅት በትግራይ ባለው ሁኔታ ምክንያት በመኖር እና አለመኖር ፈተና ላይ መሆናቸው ተገልጿል። በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን፥ የመቐለ ልደታ ማርያም ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ቆሞስ አባ ጥዑም በርሃ በትግራይ የሚገኙ ተፈናቃዮች በዘላቂነት ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ጥረት መደረግ አለበት ሲሉ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን እስከዛው ግን በሕይወት የሚቆዩበት ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

 ሥራ አጥነት በትግራይ

አባ ጥዑም በርሃ "በድርቅ የተጎዱ ወረዳዎች ጣብያዎች ብቻ ሳይሆን፣ ከዚህ ቀደም ሰርተው ይበሉ የነበሩ ይሁንና በጦርነቱ ምክንያት ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎችም አሁን ላይ ከፍተኛ አደጋ ላይ ናቸው። መፍትሔ ተገኝቶ ተፈናቃዮቹ እስኪመለሱ ድረስ በሕይወት ሊቆዩበት የሚያስችል ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል" ሲሉ ገልፀዋል። 

በዚህ የሲቪል ማሕበራቱ መግለጫ እና የሌሎች የማሕበረሰብ ተወካዮች ጥሪ ዙርያ ከፌደራል መንግስቱ የመንግስት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ባለፈው ሳምንት በትግራይ ስላለው ሰብአዊ ሁኔታ ተናግረው የነበሩት የመንግስት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ፥ የኢትዮጵያ መንግስት ለትግራይ "በበቂ መጠን" ሰብአዊ ድጋፍ እያቀረበ ነው ብለው ነበር። እንደ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር መረጃ ከመስከረም ወር ወዲህ ባለው ግዜ በትግራይ 900 ሰዎች በረሃብ ምክንያት ሞተዋል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ