1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መንግሥት የኮምዩንኬሽን አገልግሎትን መግለጫ እንዲያርም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጠየቀ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 22 2016

የፌድራል መንግሥት በትግራይ የተከሰተውን ድርቅ እና ረሐብ አስመልክቶ የመንግሥት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት የሰጠውን መግለጫ እንዲያርም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጠየቀ። የአስተዳደሩ የኮምዩንኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ረዳኢ ሓለፎም የመንግሥት አገልግሎት የያዘው “የቁጥር ጨዋታ ኃላፊነት የጎደለው ነው” ሲሉ ተችተዋል

https://p.dw.com/p/4am8n
አቶ ረዳኤ ሓለፎም
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የኮምዩንኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ረዳኢ ሓለፎም የመንግሥት አገልግሎት የያዘው “የቁጥር ጨዋታ ኃላፊነት የጎደለው ነው” ሲሉ ተችተዋልምስል Million Haileslassie/DW

ፌድራል መንግሥት የኮምዩንኬሽን አገልግሎት የሰጠውን መግለጫ እንዲያርም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጠየቀ

የፌደራል መንግስት በትግራይ ባለው ረሃብ ዙርያ የሰጠው መግለጫ እርማት ሊደረግበት የሚገባ ሲል የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ገለፀ። የፌደራል መንግስት ኮምኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር መንግስት "በበቂ መጠን" ለትግራይ እርዳታ እያቀረበ ነው በማለት በክልሉ አስተዳደር የቀረበ የረሃብ አደጋ ጥሪ ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል። የፌደራል መንግስቱ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን በበኩሉ፥ በትግራይ ጨምሮ በሁሉም ክልሎች ለሚገኙ "የቅድሚ ቅድሚያ" የሚሹ ያላቸው ዜጎች እርዳታ እያቀረበ መሆኑ ይገልፃል። 

የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በክልሉ ከሚገኝ አጠቃላይ ህዝብ መካከል 91 በመቶው ለረሃብ መጋለጡ በመግለፅ የኢትዮጵያ መንግስት እና ሌሎች ዓለምአቀፍ ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረቡ ተከትሎ ምላሽ የሰጡት የፌደራል መንግስቱ ኮምኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር ለገሰ ቱሉ የክልሉ አስተዳደር ጥሪ ፖለቲካዊ ፍላጎት የተቀላቀለበት በማለት አጣጥለውታል። ሚኒስቴሩ በመግለጫው የፌደራሉ መንግስት በትግራይ አራት ዞኖች ድርቅ መከሰቱ እንዳረጋገጠ የገለፁ ሲሆን ይሁንና ሁኔታው ከ77 ዓመተምህረት የከፋ ረሃብ ጋር እያመሳሰሉ ማቅረብ በህዝብ ሽፋን የሚቀርብ ፕሮፖጋንዳ በማለት ገልፀውታል። 

በትግራይ ክልል አጽቢ ወረዳ በሶስት ወራት 111 ሰዎች በረሐብ መሞታቸውን ባለሥልጣናት ለዶይቼ ቬለ ገጹ

በዚህ ጉዳይ ዙርያ ማብራርያ የሰጡን የትግራይ ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ፅሕፈት ቤት ሐላፊ አቶ ረዳኢ ሓለፎም፥ የኮምኒኬሽን ሚኒስቴሩ መግለጫ የተዛባ፣ ሐላፊነት የጎደለው እንዲሁም በትግራይ ህዝብ ላይ እንደማፌዝ ተደርጎ የሚወሰድ ሲሉ ኮንነውታል። የፌደራል መንግስቱ ትግራይ ላይ ያለው ሁኔታ ቀርቦ መመልከት እንደሚያስፈልገው የጠቆሙት አቶ ረዳኢ ሓለፎም በፌደራል መንግስት ኮምኒኬሽን አገልግሎት የተሰጠው መግለጫ ግን፥ እርማት ሊደረግበት ይገባል ሲሉ ገልፀውታል።

ለገሠ ቱሉ
ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት አመራር ምክር ቤት በትግራይ ክልል አራት ዞኖች ድርቅ መከሰቱን እንዳረጋገጠ የገለጹት የመንግሥት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሠ ቱሉ “ከ77ቱ ድርቅ እና የረሐብ ቀውስ ጋር ይስተካከላል” የሚል መደምደሚያ ላይ ግን መንግሥታቸው እንዳልደረሰ ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ በሰጡት መግለጫ ተናግረው ነበር። ምስል Seyoum Getu/DW

አቶ ረዳኢ ሓለፎም "በትግራይ ድርቅ በፈጠረው ረሃብ የሰው ሕይወት በየቀኑ እየተቀዘፈ ነው። እስከ ሐምሌ በነበረው መረጃ ከ1300 በላይ ሰው በረሃብ ሞትዋል። ከመስከረም እስካሁን ደግሞ ወደ 900 የሚጠጋ ሰው በረሃብ ምክንያት ሕይወቱ አልፏል። ይህ እስካሁን ያለው ነው። መጪው ግዜ ደግሞ የባሰ ይሆናል። ለምናልባትም በኢትዮጵያ ታሪክም፣ በትግራይ ታሪክም ታይቶ የማይታወቅ መቅዘፍት ከፊትለፊታችን ተደቅንዋል" ሲሉ ተናግረዋል። 

 አረና ትግራይ ለረሐብ አደጋው ሕወሓት ትኩረት አልሰጠም ሲል ወቀሰ

ይህ እንዳለ ሆኖ የኮምኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴሩ "በቁጥር ጨዋታ መጠመዱ" በስቃይ ማፌዝ ተደርጎ እንደሚታይ የገለፁት የትግራይ ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ፅሕፈትቤት ሐላፊው አቶ ረዳኢ ሓለፎም፥ ይህ ትክክል ስላልሆነ "መታረም አለበት" ሲሉ አክለዋል።

የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ስራው በተለያዩ አካላት ፖለቲካዊ መልክ የማስያዝ አዝማሚያ እንደሚታይበት የሚገልፁት ደግሞ በፌደራሉ መንግስቱ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን የኮምኒኬሽን ሐላፊ አቶ አታለለ አቡሀይ ሲሆኑ፥ በቂ ብለው ባይገልፁትም መንግስት በሁሉም ክልሎች ለሚገኙ "የቅድሚያ ቅድሚያ" ተብለው የተለዩ ሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች፥ ድጋፍ እያቀረበ እንዳለ ይናገራሉ።

አቶ ጌታቸው ረዳ
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ ትግራይ አንድ ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ሳይሞቱበት እንዳልቀረ ከሚታመነው የ1977 ድርቅ በኋላ ታይቶ ከማይታወቅ ሰብዓዊ ቀውስ አፋፍ ላይ እንደሚገኝ አስጠንቅቀው ነበር። ምስል Million Haileselassie/DW

ዓለምአቀፍ እርዳታ አቅራቢዎች ድርጅቶች የእርዳታ አቅርቦት ስራ ካቋረጡ ወዲህ ባለው ግዜ በሁለት ዙር የእርዳታ አቅርቦት ለትግራይ መድረሱ ያነሱት የኮምኒኬሽን ሐላፊው፥ ሁለተኛ ዙር ባሉት 111 ሺህ ኩንታል ምግብ ነክ ድጋፍ ወደ ትግራይ መላኩ አንስተዋል። ድርቁ ተከትሎ በትግራይ 2 ሚልዮን ዜጎች እርዳታ ፈላጊ ሆነው እንዳለ የገለፁት ሐላፊው፥ በቀጣይ ሶስተኛ ዙር ከዓለምአቀፉ ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን ሰብአዊ እርዳታ የማዳረስ ስራ እንደሚከወን ለዶቼቬለ ተናግረዋል።

የትግራይ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን እንደሚገልፀው፥ በአሁኑ ወቅት በትግራይ 2 ነጥብ 2 ሚልዮን ዜጎች በድርቁ ምክንያት ለረሃብ አደጋ ተጋልጠው ያሉ ሲሆን፣ በጦርነቱ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉት ዜጎች ጨምሮ በአጠቃላይ ከ5 ነጥብ 2 ሚልዮን በላይ ህዝብ እርዳታ ፈላጊ ሆነው እንዳለ አስታውቋል። 

የትግራይ ክልል ብድር ጠየቀ፣ ደሞዝ መክፍል ተስኖታል

በአሁኑ ወቅት በትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች ከፍተኛ ረሃብ የሚስተዋል ሲሆን፥ በክልሉ አፅቢ ወረዳ በነበረን ቆይታ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎችም በአካባቢያቸው ባለፈው ክረምት ዝናብ አለመዝነቡ ተከትሎ ለከፋ ሁኔታ ተጋልጠው እንደሚገኙ ጠቁመው ነበር። የአፅቢ ነዋሪው የዕድሜ ባለፀጋ አቶ ፍፁም ብርሃን የዘንድሮው ድርቅና ያስከተለው ረሃብ የገለፁት "በሕይወት ዘመኔ አጋጥሞኝ የማያወቅ" ብለው ነው።

በረሃቡ ጉዳይ ያለው ውዝግብ እንዳለ ሆኖ፥ በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት በሰሜን፣ ደቡብ እና ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ፥ የእርዳታ አቅርቦት ካልተፋጠነ እየተባባሰ እንደሚሄድ አስጠንቅቆ እንደነበረ ይታወሳል።

ሚሊዮን ኃይለስላሴ 
እሸቴ በቀለ
ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር