1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችኢትዮጵያ

የምሥራቅ ቦረና ዞን ውዝግብ ትምህርታቸውን እንዳስተጓጎለ ተማሪዎች ተናገሩ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 14 2016

በኦሮሚያ ክልል የተመሠረተው የምሥራቅ ቦረና ዞን ውዝግብ የአካባቢውን ወጣቶች ከትምህርት አስተጓጉሏል። በዞኑ ጎሮ ዶላ ወረዳ የሚገኙ 81 ትምህርት ቤቶች በ2016 በወጉ ትምህርት እንዳልሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ። በጉጂ ዞን ሥር የነበሩት ጎሮ ዶላ እና ሊበን ወረዳዎች በ2015 ወደተመሰረተ አዲስ ዞን መዛወራቸው ተቃውሞ ገጥሞታል።

https://p.dw.com/p/4jgYJ
Äthiopien Oromia Schule
ምስል S. Getu/DW

የምሥራቅ ቦረና ዞን ውዝግብ ትምህርታቸውን እንዳስተጓጎለ ተማሪዎች ተናገሩ

ዋቆ በሪሶ በቅርቡ ሚያዚያ ወር 2015 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በአዲስ መልክ በተመሰረተው ምስራቅ ቦረና ዞን በጎሮ ዶላ ወረዳ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ ዋቆን ጨምሮ በርካታ የወረዳው ተማሪዎች ማህበረሰቡ ክፉኛ የተቃወመውን የዞን መዋቅሩን ተከትሎ በ2016 ዓ.ም. ከትምህርታቸው ተስተጓጉለዋል፡፡ በወረዳው ያጋጠመውን የህዝብ ተቃውሞ ተከትሎ በዓመቱ ትምህርትን ጨምሮ በርካታ ማህበራዊ አገልግሎቶች በተገቢው ሳይሰጡ መክረሙንም አመልክተዋል፡፡

“ይህ የዞን መዋቅሩ ተግባራዊ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ ምንም ትምህርት የለም፡፡ እኔ አሁን ባለፈው 2016 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ፡፡ ግን ስላልተማርኩ ፈተና ላይ መቀመጥ አልቻልኩም፡፡ ይህም የሆነው በወረዳው የተሰጠ ትምህርት ባለመኖሩ ነው፡፡ ከወረዳው በምንሰማው መረጃ ከ52ሺህ በላይ ተማሪዎች በዚህ ወረዳ ብቻ በትምህርት ገበታቸው ላይ አለመሆናቸውን ነው፡፡ ታውቃለህ አሁንም ህዝቡ እንዳኮረፈ ነው፡፡ በቀጣይ 2017ም ትምህርት ይጀመራል የሚባል ምንም ተስፋ አይታየንም” ሲል ተስፋ በመቁረጥ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

የጸጥታው ስጋትና ትምህርት

ሌላው የ12ኛ ክፍል ተማሪ የነበረና ከትምህርት ገበታው ውጪ መሆኑን የሚገልጸው ኖቴ ሶርሳ የተባለ የሀርቀሎ ከተማ ተማሪ በዞኑ በተለይም ከጉጂ ዞን ወደ ምስራቅ ቦረና መዋቅር በተቀየጡ ጎሮዶላ እና ሊበን ወረዳዎች ከ80 በላይ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ከ60 ሺህ ላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ውጪ ሆነው መቆየታቸው መረጃ መኖሩን ያስረዳል፡፡

በኦሮሚያ በዞን መዋቅር የተነሳው ውዝግብ ቀጥሏል

“በጎሮዶላ አጠቃላይ ወረዳ እና በሊባን ወረዳ በከፊል ቀበሌያት ከ60 ሺህ በላይ የሚሆኑ በ80 ገደማ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ውጪ መሆናቸውን እንሰማለን፡፡ በ2016 ዓ.ም. የትምህርት ዘመኑን ምንም ሳንማር ነው ያሳለፍነው፡፡ ከዚሁ የተነሳ ለብሔራዊ ፈተናም አልተቀመጥንም፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ አሁን ለ2017 ዓ.ም. የትምህርት ዘመንም እስካሁን ምዝገባ መጀመር የነበረበት ቢሆንም ምንም ዝግጅትና እንቅስቃሴ አይታይም፡፡

INFOGRAFIK Äthiopien: Konfliktreiche Grenzregion -DE

መንግስት ወርዶ እዚህ ያለውን እውነታ ያውቃል ወይ የሚለው ሁሌም ጥያቄ ሆንብናል፡፡ ቁጥሩ የማይናቅ በርካታ ህዝብ ነው እዚህ ማህበራዊ ፍትህ እየተነፈገ ያለው፡፡ በሊበን 18 ቀበሌዎች እና በጎሮዶላ ወረዳ ደግሞ በ31ዱም ቀበሌያት ትምህርት እየተሰጠ አለመሆኑን ወርዶ የተመለከተና ትክክለኛውን ነገር የተረዳ መኖሩን
እጠራጠራለሁ፡፡ ስለዚህ ችግር ስታወራ ከጸጥታ ጉዳይ ጋር ነው የሚያያይዙብህ፡፡ የት ሂደን እንማር፤ ሁሉም ትምህርት ቤት ዘድግ ነው” ብለዋል፡፡

የተማሪዎች የትምህርት ጉጉት

ችግሩ ከተማሪም አልፎ ሲከማች እንደማህበረሰብም ብዙ ችግር የሚፈጥር ነው የሚሉት ተማሪዎች አላስፈላጊ ስነልቦና ሊያስከትል እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡ ተማሪዎቹ በቀጣይም ህብረተሰቡ በዞን መዋቅሩ ላይ ጥያቄው የቀጠለ እንደመሆኑ ትምህርት የመቀጠል እድሉ አናሳ ነው እያሉም ይገኛሉ፡፡

በምስራቅ ቦረና፤ ጎሮዶላ የተማሪዎች ተቃውሞ እስር

የስድስተኛ ክፍል ተማሪና ባለፈው ዓመት የተሰጠው ትምህርት እጅግ አናሳ በመሆኑ ፈተናዋን ለማቋረጥ መገደዷን የምትገልጸው ታዳጊ ቢፍቱ ጎሮም፤ “የስድስተኛ ከፍል ፈተና በግድ ግቡና ተፈተኑ ስሉን ነበር እኔ ጀምረው አቋርጨው የሄድኩት፡፡ ያልተማርኩበት ዓመት ስለሆነ ያልተማርኩትን እንዴት ልመልስ ብዬ ነው ጀምረው ፈተናውን አቋርጬ የተውኩት፡፡ የተወሰኑ ተማሪዎች ፈተናው ላይ ስቀመጡ እኔ ግን ያልተማርኩትን ብፈተን ለነገም አይጠቅመኝም ብዬ ትቸዋለሁ፡፡ ለምቀጥለው ዓመት አሁን ተመዝገቡ የሚል ነገር ብኖርም የተማሪው ዝግጁነት ግን ምን ላይ እንዳለ አላውቅም፡፡ እንደ እኔ ፍላጎት ትምህርት ቤቱ ብከፈትልን፤ የህዝባችንም ጥያቄ ብመለስ ብዬ ለትምህርቴ እጓጓለሁ፡፡ ግን ስጋት አለኝ” ብላለች፡፡

የትምህርት ቁሳቁስ
አንዲት የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ባለፈው ዓመት የተሰጠው ትምህርት እጅግ አናሳ በመሆኑ ፈተናዋን ለማቋረጥ መገደዷን ለዶይቼ ቬለ ተናግራለችምስል Pond5 Images/imago images

የወላጆች ጭንቀት

ወደ ትምህርት ቤት የላኳቸው ሶስት ልጆች እንዳሏቸው የሚገልጹት አረቢዩ ኡታራ የተባሉ የተማሪዎች ወላጅም በአስተያየታቸው ባለፈው ዓመት ያለ ትምህርት የከረሙ ልጆቻቸው እጅጉን ያሳስባቸዋል፡፡

“አንድ ዓመት በሙሉ ልጆቻችን ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነው እንዴት ነው የማያሳስበን፡፡ ለዚህ ችግር መንስኤው የዞን መዋቅሩ ነው፡፡ ከዚያ በመነሳት ነበር የጉጂ ህዝብ መዋቅሩን በመቃወም ልጆቼን ወደ ትምህርት ቤት አልክም ያለው እንጂ ችግሩማ እንዴት አያሳስበንም፡፡ በጎሮዶላ ብቻ 81 ትምህርት ቤቶች ብኖሩም በ2016 ዓ.ም. በወጉ በተሟላ ሁኔታ ትምህርት የሰጠ ትምህርት ቤት የለም፡፡ ልጆቼን ጨምሮ በትንሽ ግምት ከ52 ሺኅ በላይ ተማሪዎች በባለፈው የትምህርት ዘመን ትምህርት አምልጦአቸዋል፡፡ ይህ ነገር ብያሳስበንም አሁንም በጉጂ ካልሆነ በምስራቅ ቦረና መዋቅር ስር ልጆቻችንን አናስተምርም ያሉ በመዋቅሩ ቅሬታ ያላቸው ቤተሰቦች በርካታ በመሆናቸው በቀጣይ ዓመትም ትምህርት ጀመራል ወይ የሚለው አሳሳቢ ነው” ብለዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ቦረና ዞን የተማሪዎች ጥያቄ

በዞኑ ችግሩ በስፋት ይስተዋልበታል በተባለው ጎሮዶላ ወረዳ የትምህርት መምሪያ ኃላፊ ለሆኑት ለአቶ ንጉሴ ዋቆ ደውለን ስለ ችግሩና ስለቀጣይ ዓመትም እቅዳቸው እንዲያስረዱ ብንጠይቃቸውም ከአምስት ደቂቃ በኋላ ደውሉ ብለው በተደጋጋሚ መልሰን ብንደውልላቸውም ምላሻቸውን ማግኘት አልተቻለም፡፡ ቀደም ሲል በጉጂ ዞን ስር ይተዳደር የነበሩት የጎሮዶላ እና ሊበን ወረዳዎች በ2015 ዓ.ም. ወደ ምስራቅ ቦረና ዞን ተጠቃለው በተመሰረተው አዲስ ዞን ስር እንዲተዳደሩ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ውሳኔ ብተላለፍም ውሳኔው ብርቱ ተቃውሞ ማስተናገዱ አይዘነጋም፡፡

ሥዩም ጌቱ 
እሸቴ በቀለ
ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር