1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በምስራቅ ቦረና፤ ጎሮዶላ የተማሪዎች ተቃውሞና እስር

ዓርብ፣ ግንቦት 16 2016

ተማሪዎች እና የተማሪ ቤተሰብ ዓመቱን ሙሉ በቂ ትምህርት ለተማሪዎቹ አልተሰጠም በሚል ተማሪዎች ፈተና ላይ እንዳይቀመጡ ሲወተውቱ የወረዳው የመንግስት አካላት ለፈተናው መቀመጥ አለባቸው ይላሉ።በቅርቡ በዚህ ለመፈተን ፎርም እንድትሞሉ በሚል ትልቅ ሁከት ተፈጥሮ በርካቶች ታስረዋል፡፡ አሁን ከተማሪ ባሻገር የተማሪዎች ቤተሰብን ማስፈራራቱ ይስተዋላል፡፡

https://p.dw.com/p/4gErY
Äthiopien West Guji Zone
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በምስራቅ ቦረና፤ ጎሮዶላ የተማሪዎች ተቃውሞ

ከዚህ ቀደም በጉጂ ዞን ስር ትተዳደር በነበረችውና አሁን ላይ በአዲስ መልክ በተዋቀረው ምስራቅ ቦረና ዞን ስር በምትተዳደረው ጎሮዶላ ወረዳ ውዝግቡ አሁንም እንደ ቀጠለ ነው፡፡ ከትናት በስቲያ እሮብ ግንቦት 14 ቀን 2016 ኣ.ም. በወረዳው ዋና ከተማ ሀርቀሎ ተከሰተ ያሉትን ለዶቼ ቬለ የገለጹት አንድ የከተማው ነዋሪ፡ “ከዚህ በፊት የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ላይ ተማሪዎች እንዲቀመጡ መዝግበው ነበር፡፡ ተማሪዎች እና የተማሪ ቤተሰብ ዓመቱን ሙሉ በቂ ትምህርት ለተማሪዎቹ አልተሰጠም በሚል ተማሪዎች ፈተና ላይ እንዳይቀመጡ ሲወተውቱ የወረዳው የመንግስት አካላት ለፈተናው መቀመጥ አለባቸው ይላሉ፡፡ አሁን በቀደም በዚህ ፈተና ላይ ለመቀመጥ ፎርም እንድትሞሉ በሚል ትልቅ ሁከት ተፈጥሮ በርካቶች ታስረዋል፡፡ አሁን ከተማሪ ባሻገር የተማሪዎች ቤተሰብን ማስፈራራቱ ይስተዋላል፡፡ ተማሪዎች እና ወላጆች የሚገኙበት ከትናንት በስቲያ የታሰሩ 12 ሰዎች እስከ ዛሬ አልተፈቱም” ብለዋል፡፡በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ቦረና ዞን የተማሪዎች ጥያቄ

የተማሪዎቹ ተቃውሞ መሰረት


በጎሮዶላ ሀርቀሎ ከተማ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ የሆነው አስተያየት ሰጪ እሮብ በትምህርት ቤቱ ተከሰተ ያለውን ሲያስረዳ፡ “እሮብ እኛ ጋ የተከሰተው ለአንድ ዓመት ገደማ ትምህርት ባልተሰጠበት ፈተና ላይ እንድትቀመጡ ፎርም ሙሉ የሚል ነገር ነበር፡፡ ከዚህ በፊት በመሃል ትምህርት እጅግ ዘግይቶ እንዲጀመር ተብሎ ለተወሰነ ጊዜ እኛም ወደ ክፍል ስንገባ ነበር፡፡ ነገር ግን በቂ ቁጥር ያለው ተማሪ ወደ ትምህርት ስለማይመታ ያም በጥሩ ሁኔታ ባለመቀጠሉ ውስን ጊዜ ነው በትምህርት ላይ የቆየነው፡፡ ይህ ባልሆነበት ነው እንግዲህ ለስምንተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ትቀመጣላችሁ በሚል ፎርም ሊያስሞሉን ሲሉ ሁከት የተነሳው፡፡ ከትምህርት ባሻገር ትልቁ ክፍተት የፈጠረው መጀመሪያ ላይ የጉጂ ዞን በሚል ስም ትምህርት ብንጀምር የፈተናው ፎርም የመጣው ምስራቅ ቦረና በሚል መዋቅር በመሆኑ ከዚህ በፊትም ተማሪዎች ይህን ስቃወሙ የነበረ እንደመሆኑ የጠብ መንስኤ ሆኗል፡፡ በዚህ የተጫረው ጠብ ምክንያን በርካቶች ተደብድበዋል የሸሹም አሉ የታሰሩም ወደ 13 ሰዎች ናቸው፡፡ በዚህ አከባቢ እየሆነ ያለው ባጠቃላይም አሳዛኝ ነው” ይላል፡፡

የጉጂ ከተማ ኦሮምያ
የጉጂ ከተማ ኦሮምያ ምስል Private

ተማሪዎችን እንዲፈተኑ የማድረግ ጫና 


ተማሪዎች ፈተናው ላይ እንዲቀመጡ የሃይል ጫና ይደረጋል የሚለው ተማሪው በዓመቱ የተሰጠው ትምህርት እጅግ ውስን መሆኑ የተማሪውን ዝግጅት አነስተኛ በማድረጉ ሂደቱ ተቃውሞ ገጥሞታልም ይላል፡፡ “እንደ መንግስት እቅድ የስምንተኛ ክፍል የሞዴል ፈተና የፊታችን ሰኞ ነው መሰጠት የሚጀምረው፡፡ የስድስተኛ ክፍል ደግሞ እሮብ ነበር መሰጠት የጀመረው፡፡ አሁን ይህን የስድስተኛ ክፍል ፈተና ያቋረጡም ሆነ የስምንተኛ ክፍል ፈተና ላይ አልቀመጥም ያሉትን ተማሪዎች ነው ያሰሩት፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት ከአንድ ኣመት ወዲህ ትምህርት ባለመኖሩ ነው” ብሏል፡፡
በወረዳው ተከሰተ ስለተባለው የትምህርት ሂደቱ መስተጓጎልና እሮብ እለት ተስተውሏል ስለተባለው አለመረጋጋት ላይ ተጨማሪ መረጃዎችን ለመጠየቅ ለወረዳው አስተዳዳሪ በሪሶ ሳፋይ ብንደውልም ስብሳባ ላይ በመሆናቸው አስተያየቱን ሊሰጡን እንደማችሉ ገልጸዋል፡፡ የወረዳው ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሴ ዋቆ ከዚህ በፊት ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት በዚህ ዓመት በወረዳው በቂ ዝግጅት ባልተደረገበት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ለብሔራዊ ፈተና የማቅረብ ውጥን ባይኖርም የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች ግን ለብሔራዊ ፈተናዎቹ ይቀመጣሉ ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ጉዳዩን የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ምን ያህል ያውቀዋል የሚለውንም አክለን ለመጠየቅ ለክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች በመደወል አስተያየታቸውን ለማካተት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልሰመረም፡፡የኦሮሚያ ክልል ከአንድ ዓመት በፊት ሚያዚያ 15 ቀን 2015 ኣ.ም. አዲስ መዋቅሩን ሲያስተዋውቅ ምስራቅ ቦረና ብሎ ከጉጂ፣ ቦረና እና ባሌ ዞኖች የተወሰኑትን ወረዳዎች አንድ ላይ በማምጣት የመሰረተው አዲስ ዞን ክፉኛ ተቃውሞ ማስተናገዱ ይታወሳል፡፡ በተለይም ከጎጂ ዞን ወደ ምስራቅ ቦረና በተዋቀረው ጎሮዶላ ወረዳ ዓመቱን በሙሉ በነበረው ተቃውሞ ትምህርትን ጨምሮ በርካታ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ስራቸው ላይ እክል ማጋጠሙም ተደጋግሞ ተዘግቧል፡፡  

ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ