1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትአፍሪቃ

«ፈተና የተፈተነው መስኮት በጥይት እየተመታ ነው» የጎንደር ከተማ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ

ልደት አበበ
ሰኞ፣ ነሐሴ 8 2015

በቅርቡ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ተቋማት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ተሰጥቷል። ትምህርት ሚኒስቴር ይፋ እንዳደረገው በጎንደር ዩንቨርስቲ 3 ካምፓሶች ግን ይፈተኑ የነበሩ 16 ሺህ ተማሪዎች በከተማዋ በነበረ ውጊያ ፈተናውን ሳይወስዱ ቀርተዋል። በዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ይህንን ፈተና በአራት ተቋማት የወሰዱ ተማሪዎችን አነጋግረናል።

https://p.dw.com/p/4V1ne
Äthiopien | Hauptcampus der Universität Addis Abeba
ፎቶ ከማህደር፤ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ካምፓስ ምስል Solomon Muchi/DW

«ፈተና የተፈተነው መስኮት በጥይት እየተመታ ነው» የጎንደር ከተማ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ

ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በሚል ከወሰዳቸው ርምጃዎች አንዱ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በከፍተኛ ተቋማት እንዲሰጥ ማድረጉ ነው።   በዚህም መሠረት ተማሪዎች ወደ ተመደቡበት እና በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ከፍተኛ ተቋም በመሄድ ፈተናዎቻቸውን ይወስዳሉ። እነዚህ ተማሪዎች በሚመደቡበት ተቋም እስከ ስድስት ቀናት ያህል መቆየትም ግድ ይላቸዋል።  ለዛሬ ተሞክሯቸውን ያካፈሉን አራት ተፈታኞች ሲሆኑ ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን ቀይረንዋል።
መቅደስ  የተፈጥሮ ሳይንስ ፈተና ለመውሰድ የአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ከሐምሌ 23 እስከ 28 ቀን እንደቆየች ነግራናለች።  የምትማርበት የግል ትምህርት ቤት አስቀድሞ ስለ ፈተና አሰጣጡ ገለፃ ሰጥቷቸው የነበረ ቢሆንም ቦታው ላይ ስትደርስ ብዙ ግራ የሚያጋቡ ነገሮች ገጥመዋታል።  በተለይ ወደ ግቢ ይዘው እንዲገቡ የሚፈቀድላቸው ነገር እንደፈታሹ ይለያይ ነበር ትላለች።« መጀመሪያ ከትምህርት ቤታችን አንድ የመንግሥት ትምህርት ቤት ሄደን ተፈተሽን። ከዛ ድጋሚ አስቱ ለሁለተኛ ጊዜ ተፈተሽን» ።

የትምህርት ሚንስትር ፕ/ሮ ብርሃኑ ነጋ
የትምህርት ሚንስትር ፕ/ሮ ብርሃኑ ነጋምስል Shewangizaw Wegyayehu/DW

መቅደስ ኩረጃን ለመከላከል በሚል የተወሰዱት አንዳንድ ፍተሻዎች ክብርን የሚነኩ ሆና አግኝታቸዋለች። ለዚህም ወደ ግቢ ስትገባ እና በፈተና ወቅት የነበረውን እንደ ምሳሌ ትጠቅሳለች፤ 
« ፍተሻው የሚሰቀጥጥ ነበር። ልብሳችን ብቻ ሳይሆን እኛንም ጭምር ስንፈተሽ አንዳንድ የግል ቦታዎችን ይነካካሉ። » በማለት የገጠማትን ታስረዳለች። መቅደስ የምትናፈጥበት ሶፍት ይዛም ወደ ፈተና ቦታ መግባት እንዳልተፈቀደላት ነግራናለች። 
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተና ውጤት አንድምታ

ሌላው ተፈታኝ  ናትናኤል  በአንጻሩ ጥሩ ተሞክሮ ነበረው።  የቢሺፍቱ ከተማ ነዋሪ በመሆኑ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናውን የወሰደው እዛው ቢሾፍቱ ወይም ደብረ ዘይት ከተማ ነበር።     
« ደብረዘይት የሚገኝ የእንስሳት ህክምና ኮሌጅ ነው ለመፈተን የገባነው። አቀባበሉ ጥሩ ነበር። ትምህርት ቤት ስንሄድ ወደ ምንፈተንበት ተቋም የሚወስደን መኪና ተዘጋጅቶልን ነበር» ይላል።
እንደ ናትናኤል ጥሩ አቀባበል ያልገጠማት ሌላኛዋ ተፈታኝ ሜሮን ናት። የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነችው ሜሮን እንድትፈተን የተመደበችው አዲስ አበባ የሚገኘው 6 ኪሎ ዩንቨርሲቲ ነው።
« እሁድ ማታ ካምፓስ ገባን። ማታ ላይ መብራት ጠፋ። ከሌሊቱ 8 ሰዓት አካባቢ አንድ ወንድ ክፈቱ እያለ በራችንን በዱላ ያንኳኳ ነበር » ትላለች። እነሱም በሩን ሳይከፍቱ ቀርተዋል።
 በእንደዚህ አይነት ሁኔታ የዩንቨርሲቲ ቆይታቸው እንደጀመረ የገለጸችልን ሜሮን ቀጣዮቹም ቀናት አስፈሪ እና ለፈተና የማይመቹ ሆና አግኝታቸዋለች። አንድ ክፍል ውስጥ ስምንት ተማሪዎች የተመደቡ ሲሆን አምስቱ የሚተዋወቁ እና ከአንድ ትምህርት ቤት ነበሩ። ሜሮን ከእነዚህ የክፍል ባልደረባዋ አንዷ ላይ ግቢ በገቡ ማግሥት የደረሰባትን ስትናገር ማታ ላይ ወደ መፀዳቻ ቤት ሄዳ ስትመለስ ልጅቱ ተገርፋለች። « ድምፅ ሰምተን ስንወጣ እጇን ተመታለች። » የምትለው ሜሮን ወደ መጸዳቻ ቤት እንኳን መነፃነት ለመሄድ እንደተነፈጉ ለዶይቸ ቬለ ገልፃለች።

ሌላው አበበ ብላችሁ ጥሩኝ ያለን ተፈታኝ እንደውም በዚህ የፈተና ወቅት ለህይወቱ የሚያሰጋ ሁኔታ ገጥሞት እንደነበር ይናገራል። ወጣቱ የጎንደር ከተማ ነዋሪ ነው ።  በተመደበበት ፋሲል ካምፓስ የነበረው ይዞታ ላይ ምንም ቅሬታ የለውም።  « ፈተናውን ማክሰኞ ዕለት ጀመርን። ካምፓስ ከገባን ጀምሮ ረብሻ ሊፈጠር እንደሚችል ሰምተን ነበር። ከዛ አራት ፈተና ተፈትነን የኬሚስትሪ ፈተና የምንፈተን ቀን ጠዋት ላይ ይተኮስ ነበር። ፈተና ልንፈተን ወረቀታችንን ተቀብለን እንደተቀመጥን መስኮቱ በጥይት እየተመታ ነው የተፈተነው።  80ያውንም ጥያቄ የመለስንም አይመስለኝ» ይላል።


የአማራ ክልል ፀጥታና ኢንተርኔት
አበበ እንደገለፀልን በነበረው ውጊያ ምክንያት የባዮሎጂ እና ፊዚክስ ፈተና ሳይፈተኑ ቀርተዋል። ትምህርት ሚኒስቴር የፈተናዎቹ ቀናት እንደተጠናቀቁ ይፋ ባደረገው መግለጫ በጎንደር ዩንቨርስቲ ሶስት ካምፓሶች 16 ሺ የሚሆኑ ተማሪዎች ፈተናውን ሳይወስዱ መቅረታቸውን አስታውቋል። በአጠቃላይ 840 ሺ 859 የማህበራዊ ሳይንስ እና የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች በ2 ሺ 785 የፈተና ጣቢያዎች ተፈትነዋል ያለው ሚኒስቴሩ «ፈተናው ከስርቆት እና ከኩረጃ ነፃ ሆኖ ተጠናቋልም» ብሏል። መቅደስ ግን በተፈተነችበት ተቋም ኩረጃ አልነበረም ለማለት ይከብዳታል። 
« የተቀመጥንበት አቀማመጥ ትምህርት ቤት እንኳን እንዲህ ተቀራርበን አንቀመጥም። ከደርባዬ የነበረው ልጅ እየተደጋገመ ነበር መልስ አምጪ እያለ የሚጠይቀኝ። ፈታኞቹም ጠንካራ ርምጃ አይወስዱም ነበር።  ክፍል ውስጥም ወሬ ስለነበር ፈተናዬ ላይ አተኩሬ መስራት አልቻልኩም። » መቅደስ ሰዓት ይዞ ወደ ፈተና ክፍል መግባት አይቻልም የሚል መረጃ ስለነበራት ሰዓት ይዛ አልገባችም። በተፈተኑበትም ክፍል የጋራ የሆነ ሰዓት አለመኖሩ ሰዓት እንደልቧ አይታና አብቃቅታ ፈተናዋን እንዳትሰራ እንቅፋት ሆኖባታል። ፈታኛቸውም ስንት ሰዓት እንደሆነ ሊነግራቸው ፍቃደኛ እንዳልነበረ ትናገራለች። 

የጎንደር ከተማ
በጎንደር ዩንቨርስቲ ሶስት ካምፓሶች 16 ሺ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና አልተፈተኑምምስል Alemnew Mekonnen/DW


የተከለከሉ እና የተፈቀዱ ነገሮችን በሚመለከት የ ናትናኤልስ ተሞክሮ ምን ይመስላል?


የአማራ ክልል ከተሞች ሰላማዊ ውሎ፣ የአውሮጳ ኅብረት የአሜሪካና አጋሮቿ መግለጫ« እስክርቢቶ ይዘን እንድንገባ አልተፈቀደልንም። ሁሉም ነገር በትክክል ተፈትሾ ነበር የሚገባው።» እነናትናኤል ሰዓት ይዘው ወደ ተቋሙ መግባት ተፈቅዶላቸዋል። « ነገር ግን ወደ ፈተና ክፍል ሰዓት ይዞ መግባት አልተፈቀደልንም። ፈታኞቻችን በየጊዜው ይነግሩን ነበር ይላል። የመኮራረጅ ሁኔታ አልነበረም ማለት ይቻላል የሚለው ናትናኤል በጥሩ አያያዝ ፈተናውን መውሰድ በመቻሉ ደስተኛ ነው። መቅደስ እና ሜሮን የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የተወሰደውን ርምጃ  ባይቃወሙም አተገባበሩ ላይ በደንብ መሰራት እንዳለበት ያሳስባሉ። « እንደዚህ አይነት ችግር ካጋጠመ የሚወድቅ ተማሪ ይበዛል» የምትለው ሜሮን « እኛ ላይ የደረሰው ነገር ሌሎች ላይ እንዲደርስ አልፈልግም። እኔም የሚቀጥለው ዓመት የምትፈተን ታናሽ እህት አለችን። ይኼ ፈተና በዩኒቨርስቲ የሚሰጥ ከሆነ አሰጣጡ በስርዓቱ መንገድ ቢሰጥልን» ትላለች ።
በተለይ ንፅህና የጎደላቸው ማደሪያ  ክፍሎች እና መጸዳቻ ቤቶች  ሊስተካከሉ፣ ተማሪዎች በፈተና ወቅት በነፃ እንኳን መመገብ ባይችሉ እንደልባቸው ምግብ ገዝተው መመገብ እንዲችሉ የተማሪዎቹን ቁጥር ያገናዘበ አቅርቦት እንደሚያስፈልግ መቅደስ የገጠማትን በምሳሌነት በመግለጽ እንዲሻሻል ትመክራለች።


ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ