1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምክር ቤት አባላቱ የደሞዝና ጥያቄና ሕገ ወጥ የማዳበሪያ ንግድ መፍትሔ እንዲያገኝ ጠየቁ

ሐሙስ፣ የካቲት 21 2016

ደሞዝ ባለመከፈሉ የትምህርትና የጤና ሥራዎች ተስተጓጉለዋል ያሉት የምክር ቤት አባላቱ« የመንግሥት ሠራተኞችን ደሞዝ የሚያሳጣ መዋቅር መኖር የለበትም። ማዳበሪያን በተመለከተ አሁን ላይ በመንግሥትና በማህበራት እጅ 4ሺህ ብር የነበረው አንድ ኬሻ ማዳበሪያ በነጋዴዎች እስከ 20 ሺህ ብር እየተሸጠ ይገኛል ይህ ለምን ይሆናል? በማለት ጠይቀዋል ፡፡

https://p.dw.com/p/4d1Nb
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ እንደሻው ጣሰው
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ እንደሻው ጣሰው ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥያቄዎች

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ምን ጣለ ምን አነሳ ?

በወልቂጤ ከተማ ለሁለት ቀናት የተካሄደው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 6ኛ ዙር 1ኛ መደበኛ ጉባዔ  የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በርዕሰ መስተዳድሩ የቀረበውን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ክንውን አዳምጧል ፡፡ የሥራ ክንውን ሪፖርቱን ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ናቸው ፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ መንግሥታቸው በግብርና ፣ በጤና ፣ በትምህርት እና በሥራ ዕድል ፈጠራ አከናውኗል ያሏቸውን ተግባራት ለምክር ቤቱ በንባብ አሰምተዋል ፡፡

የርዕሰ መስተዳድሩ ሪፖርት

በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት በግብርናው ዘርፍ እስከ 3ሺ ለሚደርሱ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩን በሪፖርታቸው የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው “ ግንባታቸው የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በትኩረት እየሠራን እንገኛለን ፡፡የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ ምርታማነትን ለማሳደግና የሰንበት ገበያዎችን ለማስፋፋት እየሞከረን ነው ፤ አንዳንድ አካላት በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት በማስፋፋት ክልሉ ተረጋግቶ ሥራ እንዳይጀምር መጠነ ሰፊ ዘመቻ ከፍተው ነበር። ነገር ግን የክልሉ መንግስት በተሟላ መንገድ ወደ ስራ በመግባቱ በሁሉም ዘርፍ ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል “ ብለዋል ፡፡የፍትህ ተደራሽነት ጥያቄ በደቡብ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች

የሠራተኞች ደሞዝ እና የገበሬዎች የአፈር ማዳበሪያ ጥያቄ

የምክር ቤቱ አባላት የርዕሰ መስተዳድሩን ሪፖርት ተከትሎ በክልሉ አሳሳቢ ያሏቸውን ጉዳዮች በጥያቄና በአስተያየት አንስተዋል ፡፡ በተለይም የሠራተኞች ደሞዝ በወቅቱ አለመከፈል እና ህገ ወጥ የአፈር ማዳበሪያ ንግድ መስፋፋት አሁንም በክልሉ ያልተፈቱ ችግሮች መሆናቸውን ነው አባላቱ የጠቀሱት ፡፡ ደሞዝ ባለመከፈሉ የትምህርት እና  የጤና ሥራዎች እየተስተጓጎሉ ይገኛሉ ያሉት የምክር ቤት አባላቱ “ የመንግሥት ሠራተኞችን በደሞዝ ጥያቄ ምክንያት ሥራ ሊያቆሙ አይገባም ፡፡ ደሞዛቸዉን በፈረቃ የሚቀበሎት ዜጎች አቤቱታደሞዝ የሚያሳጣ መዋቅር መኖር የለበትም ፡፡ ማዳበሪያን በተመለከተ አሁን ላይ በመንግሥት እና በማህበራት እጅ 4ሺህ ብር የነበረው አንድ ኬሻ ማዳበሪያ አሁን ላይ በነጋዴዎች እስከ 20 ሺህ ብር እየተሸጠ ይገኛል ፡፡ ይህ ለምን ይሆናል “ በማለት ጠይቀዋል ፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ምስል Central Ethiopia Regional state Communications office

በብድር እየተሸፈነ የሚገኘው የሠራተኞች ደሞዝ

ከምክር ቤት አባላት በቀረበው የሠራተኞች የደሞዝ ጥያቄ ዙሪያ ምላሽ የሰጡት የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ዘይቱና ኢብራሂም የደሞዝ መዘግየት መንስዔና እየተደረገ ይገኛል ያሉትን ጥረት ለምክር ቤቱ አብራርተዋል ፡፡ ችግሩ ከረጅም ጊዜ አንስቶ ሲንከባለል የመጣ ከግበዓትና ከጥሬ ገንዘብ ብድር ጋር የተያያዘ መሆኑን የጠቀሱት ወይዘሮ ዘይቱና “ በዚህ ዓመት ብቻ የፌዴራል መንግሥት ከክልሉ በጀት ላይ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ቆርጦ ያስቀረበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ አሁን ላይ ከሀምሌ አንድ ጀምሮ ያልተከፈለ ደሞዝ ያለባቸውን ተቋማት በመለየት ክልሉ ለደሞዝ ብቻ በወር እስከ 130 ሚሊየን ብር በብድር እየከፈለ ይገኛል ፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ወረዳዎችና ዞኖች የውስጥ ገቢ አሰባሰብ አቅማቸውን በማሳደግ ክፍተቱን ለመሸፈን ይሠራል “ ብለዋል።

 የወልቂጤ ከተማ፦ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት መቀመጫ
የወልቂጤ ከተማ፦ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት መቀመጫ ምስል Shewangzaw Wegayehu/DW

የደላላ ሲሳይ የሆነው የአፈር ማዳበሪያ

የአፈር ማዳበሪያን በተመለከተ አሁንም በደላሎች አማካኝነት ሕገ ወጥ ሥራዎች መኖራቸውን የጠቀሱት የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር እና የክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አንዳሻው ጣሰው ለዚህም መንግስታቸው የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወስድ ተናግረዋል ፡፡ በአሁኑወቅት በክልሉ ለዓመቱ ከታቀደው 804 ሺህ  ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ መካከል 386 ሺህ ኩንታል ወደ ክልሉ መግባቱን የጠቀሱት ሃላፊዎቹ “ ግበዓቱን ወደ ደላላ ለማስተላለፍ ሰፊ ዘመቻ እየተካሄደ ይገኛል ፡፡  በዛሬ ቀን ነጋዴዎች ገበያ ላይ ማዳበሪያ እየሸጡ እንደሚገኙ እናውቃለን ፡፡ በእኛ በኩል እንዴት ይወጣል በማን ያወጣዋል የሚለውን እየተከታተልን አንገኛለን  ፡፡ ሙሉ ሰንሰለቱን ስንደርስበት ለህግ የምናቀርብ ይሆናል ፡፡ በዚህ ላይ ጥብቅ አቋም አለን  “ ብለዋል ፡፡

የሃድያ ዞን መምህራን እና ሐኪሞች የደሞዝ ጥያቄ ከምን ደረሰ?በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ላይ በአዲስ መልክ በተዋቀረው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሠራተኞች ደሞዝ ፤ ገበሬዎች ደግሞ የማዳበሪያ አቅርቦት ጥያቄን በተደጋጋሚ ሲያነሱ መቆየታቸው ይታወቃል ፡፡ የክልሉ መንግሥት በበኩሉ በበጀት እጥረት እና ባልተከፈለ የማዳበሪያ ዕዳ የተነሳ የደሞዝ ክፍያውም ሆነ የማዳበሪያ አቅርቦቱን በሚፈለገው  ደረጃ ለማከናወን  እንደተቸገር ሲገልፅ ቆይቷል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ