1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደሞዛቸዉን በፈረቃ የሚቀበሎት ዜጎች አቤቱታ

ዓርብ፣ የካቲት 15 2016

የደሞዝ ክፍያው መዘግየት በኑሯቸው ላይ ከፍተኛ ተፅኖ እንዳሳደረባቸው የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ ልጆቻቸውን ለመመገብና ለማሳከም ልመና እስከመውጣት ደርሰዋል፡፡ በሠራተኞቹ ቅሬታ ዙሪያ ተጨማሪ ምላሽ ለማግኘት የሥልጤ ዞንንም ሆነ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፋይናንስ ሃላፊዎች ስብሰባ ላይ በመሆናቸዉ ዝርዝር መልስ ማግኘት አልተቻለም።

https://p.dw.com/p/4cnnP
የደሞዝ ክፍያ በፈረቃ የሚቀበሉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቅሬታ
የደሞዝ ክፍያ በፈረቃ የሚቀበሉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቅሬታምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ቅሬታ አቅራቢዎቱ የመንግሥት ሠራተኞች ወርሃዊ የደሞዝ ክፍያቸው ከአንድ እስከ ሁለት ወራት ይዘገይባቸዋል

ያልተመለሰው የደሞዝ ጥያቄ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል

አቶ ከማል አብዱራዝቅ እና አቶ ሚፍታህ ጀማል በሥልጤ ዞን ሥልጤ ወረዳ በመንግሥት ሠራተኝነት በማገልገል ላይ እንደሚገኙ ይናገራሉ ፡፡ ከማል እና ሚፍታህ እንደሚሉት ካለፈው የህዳር ወር ጀምሮ  የእነሱን ጨምሮ በተለያዩ የሥልጤ ዞን ወረዳዎች የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ወርሃዊ የደሞዝ ክፍያቸው ከአንድ እስከ ሁለት ወራት ይዘገይባቸዋል ፡፡

ደሞዝ በፈረቃ

የደሞዝ ክፍያው መዘግየት በኑሯቸው ላይ ከፍተኛ ተፅኖ እንዳሳደረባቸው የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ  “ በተለይም አንዳንድ ሠራተኞች ልጆቻቸውን ለመመገብና ለማሳከም ልመና እስከመውጣት ደርሰዋል  ፡፡ደሞዛችንን በወቅቱ ለማግኘት ያልቻልነው ክፍያው በፈረቃ በመፈጸሙ የተነሳ ነው ፡፡ ለምሳሌ በያዝነው የየካቲት ወር መከፈል የነበረበትን የጥር ወር ደሞዝ ያገኙት በ16 መሥሪያቤቶች ውስጥ የሚገኙ ሠራተኞች ናቸው ፡፡ ቀሪዎቹ የ9 መስሪያቤት ሠራተኞች ደግም በቀጣዩ ወር የሚከፈላቸው ነው የሚሆነው  ፡፡ በአጭሩ ክፍያው እንደ መብራትና ውሃ በፈረቃ ነው የሚፈጸመው “ ብለዋል ፡፡

የመዋቅር መስፋት ያስከተለው የበጀት እጥረት

“ ደሞዝ በወቅቱ እየተከፈለን አይደለም “  በሚል ከሠራተኞቹ የቀረበው ቅሬታ ትክክል መሆኑን የሥልጤ ወረዳ ፋይናንስ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ሸምሲያ ቃሲም ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል ፡፡ሃላፊዋ የደሞዝ መዝገየት ያጋጠመው ተጨማሪ የአስተዳደር መዋቅር መደራጀታቸውን ተከትሎ የበጀት እጥረት በማጋጠሙ ነው ይላሉ  ፡፡

ቀደምሲል በሥልጤ ዞን የሚገኘው የሥልጤ ወረዳ አሁን ላይ ምስራቅ ሥልጤ ፤ የቅበት ከተማ አስተዳደር እና ራሱ ሥልጤ ወረዳ በመሆን አሁን ሦስት መዋቅር ሆኖ መውጣቱን የጠቀሱት ወይዘሮ ሸምሲያ “ የአዳዲስ መዋቅሮች መደራጀት ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ የሰጡ ቢሆንምበበጀት አቅርቦት ላይ ግን የራሳቸውን ተፅኖ እያሳደሩ ይገኛሉ ፡፡ በእኛ በኩል ችግሩን  ለማቃላል በሙሉ አቅማችን እየጣርን እንገኛለን ፡፡ በተለይም የገቢ አሰባሰብ አቅምን ለመጨመር ትኩረት ሰጥተን እየሠራን እንገኛለን “ ብለዋል ፡፡

የርዕሰ መስተዳድሩ ማሳሰቢያ

ዶቼ ቬለ በሠራተኞቹ ቅሬታ ዙሪያ ተጨማሪ ምላሽ ለማግኘት የሥልጤ ዞንንም ሆነ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፋይናንስ ሃላፊዎችን ለማነጋገር ጥረት አድርጓል ፡፡ ይሁንእንጂ ሃላፊዎቹ ስብሰባ ላይ መሆናቸውን የሚገልፅ በአጭር የጹሁፍ መልዕክት ከመመለስ በስተቀር እነሱን አግኝቶ አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም ፡፡ ያም ሆኖ ባለፈው ወር መደበኛ ጉባዔውን ባካሄደው የክልሉ ምክር ቤት ጉባዔ ላይ  ይሄው የደሞዝ ጥያቄው ከምክር ቤቱ አባላት ለርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው ተነስቶላቸው  ነበር ፡፡ “ በክልሉ የደሞዝ ጥያቄ አጀንዳ እንዲሆን አንፈልግልም “ ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ “ በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደር መዋቅሮች የራሳቸውን ገቢ ሰብስበውና የድጎማ በጀታቸውን ጨምረው ለጥያቄው መፍትሄ መስጠት ይኖርባቸዋል ፡፡ ሁሉም መዋቅሮች ሌሎች ፕሮጀክቶችን ከመፈጸማቸው በፊት የሠራተኞቻቸውን ደሞዝ መክፈል መቻል አለባቸው ፡፡ ይህንን ሁላችሁም ሃላፊዎች በጥንቃቄ እንድትመሩት አሳስባለሁ  “ ብለው ነበር ፡፡

የደሞዝ ክፍያ በፈረቃ የሚቀበሉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቅሬታ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤትምስል Central Ethiopia Regional state Communications office

የፊርማ ስብሰባ

ሠራተኞቹ አሁን ላይ ኮሚቴ በማቋቋምና ፊርማቸውን በማሰባሰብ በክልሉ ይመለከታቸዋል ላሏቸው ተቋማት አቤቱታቸውን እያቀረቡ እንደሚገኙ ሠራተኞቹ ተናግረዋል ፡፡ እስከአሁንም በስልጤ ዞን እና በማዕከላዊ ኢትዮጲያ ክልል ለሚገኙ የፋይናንስ ፤ የሰው ሀብት አስተዳደር ቢሮዎች እና ለርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ጥያቄያቻቸውን በጽሁፍ  በማስገባት ምላሽ እየጠበቁ እንደሚገኙ ገልጸዋል ፡፡ የነባሩ የደቡብ ብሄር ፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል አካል ሆኖ የቀጠለውና በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ላይ በአዲስ መልክ የተዋቀረው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሠራተኞች የደሞዝ አልተከፈለንም ቅሬታ ሲያቀርቡ መስማት የተለመደ ነው ፡፡ የክልሉ መንግሥት በበኩሉ በበጀት እጥረት እና ባልተከፈለ የማዳበሪያ ዕዳ የተነሳ ክፍያውን በወቅቱ ለማከናወን እንደተቸገር በተደጋጋሚ ሲገልፅ ቆይቷል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

አዜብ ታደሰ 

ኂሩት መለሰ