የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት የአፍሪካ አገራትን ገንዘብ ማዳከም ጀምሯል ።
ሐሙስ፣ መጋቢት 24 2018
የአፍሪካ ሕብረት፣የአፍሪካ ልማት ባንክ፣የተባበሩት መንግስታት ደርጅት የልማት ፕሮግራምና የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን፣የመካከለኛው ምስራቅ ግጭት በአፍሪካ ኢኮኖሚ ላይ ያደረሰውን ተጽዕኖና የመፍትሔ ሐሳቦችን ያካተተ ሰነድ ዛሬ ይፋ አድረገዋል ።
እየተካሄደ ካለው አመታዊው የአህጉሪቱ የኢኮኖሚ ሚኒስትሮች ስብሰባ ጎን ለጎን ይፋ የተደረገው ሰነድ፣ የበርካታ የአህጉሪቱ አገራት የገንዘብ የምንዛሪ መጠን ቅናሽ ማሳየቱን አመልክቷል። የበለጠ ተጋላጭ የሆኑት ነዳጅ አምራች ያልሆኑ አገራት መሆናቸውን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረዳት ዋና ፀሃፊና የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም የአፍሪካ ቢሮ ዳይሬክተር አሁና ኢዚያኮንዋ ለዶይቼ ቨለ አስረድተዋል።
በመካከለኛው ምስራቅ በቀጠለው ጦርነት ምክንያት፣የ29 የአፍሪካ አገራት የገንዘብ ምንዛሪ መጠን መቀነሱን የአፍሪካ ሕብረት ከሌሎች ተቋማት ጋር በመኾን ይፋ ያደረገው መረጃ ያመለክታል።ይህ ደግሞ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ዋጋ እንዲያሻቅብ እና የውጭ እዳ መጠን እንዲጨምር ማድረጉን ጠቅሷል።
የመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት ተጽዕኖ ያሳደረበት የአፍሪካ የገንዘብ ምንዛሪ
ዛሬ መጋቢት 24 ቀን 2018 ዓ/ም በሞሮኮ ይፋ የተደረገው ሰነድ፣ጦርነቱ በአህጉሪቱ ኢኮነሚ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳትና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አመላክቷል ። በአፍሪካ ሕብረት፣በአፍሪካ ልማት ባንክ፣በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽንና በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም የተዘጋጀው ሰነድ ከጠቀሳቸው ነጦቦች መካከል በግጭቱ ምክንያት የ29 የአፍሪካ አገራት የገንዘብ ምንዛሪ መጠን መቀነሱ ይገኝበታል። ከሞሮኮ በስልክ ያነጋገርኳቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረዳት ዋና ፀሃፊና የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም የአፍሪካ ቢሮ ዳይሬክተር አሁና ኢዚያኮንዋ ይህንኑ አብራርተዋል።
" አሁን ሪፖርት የተደረገው በዋነኛነት ከዩናይትድ ስቴትስ ዶላር አንጻር ነው።የምንዛሪ መጠኑ የተሰላው ነዳጅ ዘይትና ማዳበሪያ ለማስገባት ዋነኛው መገበያያ ከኾነው ከዶላር አንጻር ነው።የነዳጅ ግብይት በአሁኑ ጊዜ በአብዛኛው የዶላር ግብይት ኾኗል።በአለምአቀፍ ንግድ ወስጥ ለውጭ ተቋማት የሚከፈለውን ገንዘብ የሚወሰነውም ይሄ ነው።እናም የምንዛሪ መጠኑ የተሰላው ከዶላር አንጻር ነው" ብለዋል። የበለጠ ተጽእኖ እያሳደረ ያለውም ነዳጅ አምራች ባልሆኑ አገራት ላይ መኾኑን ረዳት ዋና ፀሃፊዋ ምስራቅ አፍሪካን በምሳሌነት በመጥቀስ ለዶይቼ ቨለ አስረድተዋል።
"በምስራቅ አፍሪካና በአፍሪካ ቀንድ የገንዘብ ምንዛሪ መጠን መቀነሰ ያጋጠማቸው የተወሰኑት አገራት፣ ኬኒያ፣ኢትዮጵያ፣ዩጋንዳ፣ታንዛኒያ፣ሶማሊያ ጂቡቲና ደቡብ ሱዳን ናቸው።እነዚህ ኢኮኖሚዎች ይበልጥ የተጋለጡት ከውጭ በሚገባ የነዳጅና የምግብ ግዥ ላይ በጣም ጥገኛ በመኾናቸው ይመስለኛል።እነዚህ ነዳጅ አምራች አገራት አለመኾናቸውን መመልከት ትችላለህ" በማለት አስረድተዋል።
በሰነዱ የተካተቱ የመፍትሔ ሐሰቦች
የአፍሪካ ልማት ባንክ በሳምንቱ መጀመሪያ ይፋ ያደረገው ሪፖርት እንደሚያሳየው፣የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነትከመጀመሩ በፊትም የአህጉሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት መቀነስ ጀምሮ ነበር።ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ መንግስታት ከአበዳሪዎች የወሰዱት የገንዘብ መጠን ከፍተኛ መኾን፣የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እየቀነሰ መምጣትና ከውጭ የሚገኝ የልማት እርዳታ መጠን መቀነስ መኾናቸውን አብራርቷል። ረዳት ዋና ፀሃፊዋ እንዳሉት፣ በሰነዱ የተካተቱ ምክረ ሐሳቦችም ከወቅታዊው የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት አሻግረው የሚመለከቱ ናቸው።
"የመካከለኛውን ምስራቅ ግጭት እንደ ጊዚያዊ መስተጓጐል እየቆጠርነው አይደለም።በአፍሪካ የንግድ፣የኃይልና የገንዘብ ስርአት ውስጥ የማሻሻያ እርምጀ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የሚያሳይ የማስጠንቀቂያ ምልክት አድርገን ነው የምናየው " ብለዋል። እናም ሰነዱ የአጭር ገዜ፣የመካከለኛ እና የረዥም ገዜ የመፍትሔ ሐሳቦችን ያካተተ መኾኑን ገልፀዋል ።
ውሳኔዎችን የመተግበር አስፈላጊነት
ሰነዱ ይፋ የተደረገው አመታዊ የአህጉሪቱ የኢኮኖሚ ሚኒስትሮች ስብሰባ በሞሮኮ እየተካሄደ ባለበት ወቅት ነው።በእንግሊዝኛው ምህጻረ ቃል አይ.ኤስ.ኤስ. በመባል በሚታወቀው የጸጥታ ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ የኾኑት ሞዝስ ኦኬሎ ለ ዶይቼ ቬለ እንዳሉት፣ውሳኔዎችን የመተግበር አስፈላጊነት በሚኒስትሮቹ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።"ከሞሮኮው ስብሰባ መውጣት ያለበትና እጅግ ከሁሉም የበለጠ አስፈላጊ የሆነው ነገር ይሄ ይመስለኛል ።ሕብረቱ የሚደርስበትን ውሳኔ መንግስታቱ እንዲያከብሩ የሚያስችል ስልት ሚኒስትሮቹ ማውጣት አለባቸው።ምክንያቱም ከውጭ አካላት ጋር አብሮ መስራት የሚችሉት አንድነት ሲፈጥሩና አንድ ድምፅ ሲኖራቸው ነው" በማለት አስረድተዋል ።
እስክንድር ፍሪው
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ