ሳዑዲ አረቢያ ሁለት ኢትዮጵያውያንን በሞት ቀጣች
ሳዑዲ አረቢያ ሁለት ኢትዮጵያውያንን ትናንት በሞት ቀጣች። የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት (AFP) የሳዑዲ አረቢያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጠቅሶ እንደዘገበው ስማቸው የተገለጸው ሁለቱ የኢትዮጵያ ዜጎች በሞት የተቀጡት አደንዛዥ እጽ በማዘዋወር ተከሰው ነው። በሳዑዲ አረቢያ የዜና አገልግሎት መግለጫ መሠረት ሁለቱም ሀሽሽ የተባለውን አደንዛዥ እጽ በማዘዋወር ጥፋተኛ ተብለው ነበር ። በዘገባው ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤት ክሱን አረጋግጦ በሰዎቹ ላይ የሞት ቅጣት መበየኑም ተጠቅሷል። ሳዑዲ አረቢያ ከዚህ ዓመት ጥር ወር አንስቶ ኢትዮጵያውያን ጨምሮ በሞት የቀጣቻቸው የውጭ ዜጎች ቁጥር ቢያንስ 101 ነው። በጎርጎሮሳዊው 2025 ሀገሪቱ በአጠቃላይ 189 ሰዎችን በሞት ቀጥታለች። ከመካከላቸው 88ቱ ዜጎቿ ናቸው። ባለፈው በጎርጎሮሳዊው 2024 ዓ.ም. ቢያንስ 338 ሰዎች በሞት ተቀጥተዋል። በ2023 ደግሞ በሞት የተቀጡት ቁጥር 170 ነበር። በሳዑዲ አረቢያ የሚፈጸመው የሞት ቅጣት በሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በጥብቅ ተወግዟል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የመካከለኛው ምስራቅ እና የሰሜን አፍሪቃ ቡድን ምክትል ሃላፊ ክሪስቲን ቤከርል በሰጡት አስተያየት የሞት ቅጣቱን “ከከባድ ኢፍትሃዊ የፍርድ ሂደት በኋላ ያለማቋረጥ እና ያለ ርህራሄ ተግባራዊ የሚሆን” ሲሉ ኮንነውታል። የሞት ቅጣት ሊያስፈርዱ በማይገባቸው ወንጀሎች የውጭ ሀገር ዜጎች መገደላቸው በእውነትም አስፈሪ አዝማሚያ እያየን ነው ሲሉም ተናግረዋል። አምነስቲ ግልጽነት ይጎድለዋል በሚለው የሀገሪቱ የፍርድ ስርዓት የውጭ ዜጎች በሳውዲ አረቢያ ፍትሃዊ ፍርድ እንዳያገኙ ተጨማሪ እንቅፋት ሆኗል። የሳዑዲ ባለስልጣናት ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ላይ የሞት ቅጣት መበየንን ለሶስት አመታት ያህል ካቋረጡ በኋላ ነበር እንደገና በጎርጎሮሳዊው 2022 መጨረሻ ላይ ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩት።
በሺህዎች የሚቆጠሩ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል
በደቡብ ሱዳኑ ጦርነት ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰደተኞች ደንበር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን የአካባቢው አስተዳደርና የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) አስታወቁ። የጋምቤላ ክልል ዋንታዋ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጋትዊች ቡዝ የተመዘገቡና ያልተመዘገቡ ቁጥራቸው 50ሺህ የሚደርስ ስደተኞች ማታርና ሙን በተባሉ የወረዳው አካባቢዎች እንደተጠለሉ ለዶቼቬለ ተናግረዋል። አቶ ጋትዊች ስደተኞቹ በቂ ምግብ አያገኙም ብለዋል
UNHCR ለዶቼቬለ በደብዳቤ እንዳሳወቀው ከ35ሺህ በላይ አዳዲስ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል። እንደ UNHCR ከስደተኞቹ ሴቶችና ህጻናት ያመዝናሉ። በድንገት አካባቢያቸውን ጥለው በመውጣታቸውም ለምግብ እጥረት፣ ለህክምና እጦት፣ ለመጠለያና ለሌሎች ችግሮች ተጋልጠዋል ፡፡ የሰደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት የጋምቤላ ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ መዝገበ ገብረማሪያም ለስደተኞቹ የመጠለያ ስፍራ ለመገንባት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ለዶቼቬለ መናገራቸውን አለምነው መኮንን ዘግቧል።
ጄኔቫ ከግንቦት መጨረሻ ወዲህ በጋዛ 800 ሰዎች ተገድለዋል
ካለፈው ጎርጎሮሳዊው ግንቦት መጨረሻ ወዲህ በጋዛ እርዳታ ለማግኘት ከሞከሩ ሰዎች ወደ 800 የሚጠጉት እንደተገደሉ የተመድ ዛሬ አስታወቀ። ድርጅቱ እንዳለው አብዛኛዎቹ የተገደሉት በዩናይትድ ስቴትስና እስራኤል በሚደገፈው የጋዛ ሰብዓዊ ድርጅት እርዳታ መስጫ ቦታዎች አቅራቢያ ነው። ድርጅቱ ስራ የጀመረው እስራኤል በጋዛ ከሁለት ወራት በላይ እርዳታ መስጠት ካቆመች በኋላ ነው። የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ ቃል አቀባይ ራቢና ሻምዳሳኒ እንዳሉት ድርጅቱ ስራ ከጀመረበት ከግንቦት መጨረሻ አንስቶ እስከ ጎርጎሮሳዊው ሐምሌ መጀመሪያ ድረስ በድርጅቱ አቅራቢያ 615 ሰዎች ተገድለዋል። ሌሎች 183 ደግሞ እርዳታ የጫኑ መኪናዎች በሚያልፉባቸው ስፍራዎች ነው የተገደሉት። አብዛኛዎቹም የተኩስ ጥቃቶች ናቸው የደረሱባቸው። ምግብ ሲያድል የነበረው የእርዳታ ድርጅቱ ግን በአቅራቢያው ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት አልተፈጸምም ብሏል። የእስራኤል ጦር በምግብ ማደያው ማዕከላት አካባቢ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ለተከፈተው ተኩስ ሃላፊነቱን የሚወስደው ሃማስ ነው ሲል ከሷል። ከተወሰደው ትምሕርትም መሬት ላይ ለሚገኙ የእስራኤል ጦር ኃይላት ትዕዛዝ መተላለፉን ተናግሯል።
ኪቭ ሩስያ በአንድ የማዋለጃ ሆስፒታል ላይ የድሮን ጥቃት አካሄደች
ሩስያ በዩክሬን ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ካርኪቭ ማዕከል በአንድ የማዋለጃ ሆስፒታል ላይ ባደረሰችው የድሮን ጥቃት 9 ሰዎች ሲቆስሉ፤ ሆስፒታሉም ጉዳት እንደደረሰበት ባለሥልጣናት አስታወቁ። ከጥቃቱ በኋላ በሆስፒታሉ ውስጥ የነበሩ እናቶች ከህጻናት ልጆቻቸው ጋር ሆስፒታሉን ለቀው ወደ ሌላ የህክምና ተቋም እንዲሄዱ ተደርጓል። በጥቃቱ የቆሰሉት ሆስፒታሉ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ይሁኑ ሌሎች አልተገለጸም ። ሩስያ ሰሞኑን በዩክሬን ከተሞች የድሮን፣ የረዥም ርቀት ተወንጫፊና የክሩዝ ሚሳይሎች እንዲሁም የቦምብ ጥቃቶች ማጠናከሯ ዩክሬን የአየር መከላከያዋን ለማሻሻሻል አጣዳፊ ጥረቶች እንድታደርግ አስገድዷታል።
በዩክሬን የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ተልዕኮ እንዳለው በጎርጎሮሳዊው ሰኔ ዩክሬን ላይ በተካሄዱ ጥቃቶች 232 ሰዎች ሲገደሉ 1, 343 ደግሞ ቆስለዋል። ይህ የዩክሬንና ሩስያ ጦርነት ከተጀመረበት ከዛሬ ሦስት ዓመት ወዲህ በወር ብዙ ሰዎች የሞቱበት እና የቆሰሉበት ሆኗል። የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ምዕራባውያን አጋሮቻቸው ቃል የገቡላቸውን የጦር መሣሪያ በፍጥነት እንዲያቀርቡላቸው ትናንት ሮም ውስጥ በተካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ተማጽነዋል። ዩክሬን በአሁኑ ጊዜ የሩስያን የሚሳይል ጥቃት ለመቋቋም ከምንም በላይ ተጨማሪ ዩናይትድ ስቴትስ ሰራሽ ፓትርየት የተባለው የአየር መቃወሚያ ስርዓቶች ያስፈልጓታል። ሻሄድስ የተባሉ ሩስያ ሰራሽ ድሮኖችን መተው የሚጥሉ የጦር መሣሪያዎችንም ትሻለች። ዜሌንስኪ ፣ አጋሮቻቸው 10 ተጨማሪ የፓትርየት ሚሳይል ስርዓትና ሚሳይሎች እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል። ጀርመን ሁለቱን ገዝታ ለዩክሬን ለማስተላለፍ ዝግጁ መሆንዋን ስታሳውቅ ኖርዌይ ደግሞ ሌላ አንድ ሚሳይል ልትገዛላት ተስማምታለች። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከአሜሪካን መሣሪያዎቹን ገዝተው ለዩክሬን ለሚሰጡ የኔቶ አባል ሀገራት ሀገራቸው ፓትርየቶችን ጨምሮ ሌሎች የጦር መሳሪያዎችን እንደምትልክላቸው ትናንት ተናግረዋል። ትራምፕ ኤን ቢሲ ለተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃለ ምልልስ ስለ ሩስያ ዋነኛ ያሉትን መግለጫ ሰኞ እንዲሚሰጡም አስታውቀዋል።
ብራሰልስ የአውሮጳ ኅብረት በአሜሪካን ላያ ያቀረበው ወቀሳ
አሜሪካን በተመድ ድርጅት ልዩ ባለሞያ ላይ ማዕቀቦች ለመጣል መወሰኗ ክፉኛ እንዳሳዘነው የአውሮጳ ኅብረት ዛሬ አስታወቀ። ኅብረቱ ይህን ያለው፣ በተመድ የፍልስጤማውያን ግዛቶች ጉዳይ ልዩ ባለሞያ ፍራንቼስካ አልባኔዝ ፣ዋሽንግተን በጋዛ የምትከተለውን መርህ ከተቹ በኋላ አሜሪካን ማዕቀቦችን ልትጥልባቸው ውሳኔ በማሳለፏ ነው።
ዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፣አልባኔዝ ዋሽንግተንን ከተቹ በኋላ በዚህ ሳምንት ረቡዕ የፍልስጤማውያን ጉዳዮች ባለሞያዋ ላይ ማዕቀብ እንደሚጥሉባቸው አስታውቀዋል። አሜሪካ በፍራንቼስካ አልባኔዝ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ ተቀባይነት የሌለው በማለት ያጣጣለው የተባበሩት መንግሥታት ሊቀለበስ እንደሚገባ ጥሪ አቅርቧል። የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሃላፊ ፎልከር ቱርክ የተመድና የዓለም አቀፍ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድቤትን የመሳሰሉ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተሿሚዎችን ማጥቃትና ማስፈራራት እንዲቆም ጠይቀዋል። ዩናይትድ ስቴትስ በእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ነታንያሁ ላይ የእስር ማዘዣ እንዲቆረጥ የወሰኑ አራት የዓለም አቀፍ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት ዳኞች ዩናይትድ ስቴትስ እንዳይገቡ ማዕቀብ ጥላለች። አልባኔዝ በእስራኤል ላይ ያለማቋረጥ በሚያቀርቡት ትችትና እስራኤል በጋዛ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመች ነው ሲሉ በሚሰነዝሩት የረጅም ጊዜ ክስ እስራኤልና አንዳንድ አጋሮቿ ከባድ ትችቶች ያወርዱባቸዋል። ትውልደ-ኢጣሊያዊቷ አልባኔዝ በዚህ ወር ባወጡት ዘገባ ከእስራኤል ህገ ወጥ ወረራ፣ የዘር መድልዎ እና አሁን ትፈጽማለች ባሉት የዘር ማጥፋት ከፈጠረው ኢኮኖሚ አትርፈዋል ያሏቸውን ኩባንያዎች አውግዘዋል። አልባኔዝ ካወገዟቸው ኩባንያዎች አብዛኞቹ አሜሪካውያን ናቸው። የጋዛ እና የዌስት ባንክ ጉዳዮችን የሚመረምሩት ፍራንቼስካ አልባኔዝ ኃላፊነቱን የተረከቡት በጎርጎሮሳዊው 2022 ዓ.ም. ነበር።
ትራምፕ በጎርፍ የተጎዳውን ቴክሳስን ሊጎበኙ ነው
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቢያንስ 120 ሰዎች የተገደሉበት የጎርፍ አደጋ የደረሰበትን የቴክሳስን አካባቢ ዛሬ ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ትራምፕ በጎርፉ ክፉኛ የተጎዱ አካባቢዎችን ተዘዋውረው ይመለከታሉ ተብሏል ። የመንግስት የአደጋ ጊዜ የዘመቻ ማዕከላትን ለተጎጂዎች ከማንም ቀድመው የደረሱ ሰዎችን እና የጎርፉ ሰላባ ቤተሰቦችንም ያነጋግራሉ ። ከሟቾቹ መካከል 27 ልጃገረዶች ይገኙበታል ። ልጆቹ ያረፉበት ስፍራ ከባዱ ጎርፍ የደረሰበት አካባቢ እንደነበር ኒውዮርክ ታይምስ በቅርቡ ያወጣው የምርመራ ገዘባ አስታውቆ ነበር ። በአደጋው ከአንድ መቶ ስልሳ በላይ ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም። የጠፉትን ለመፈለግ የሚካሄደው ዘመቻ እንደቀጠለ ነው። ከአንድ ሳምንት በፊት የደረሰው ይኽው የጎርፍ አደጋ በሰብልና በከብት ሀብት ላይ ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ እንደሚሆን ቢገመትም በትክክል ምን ያህል እንደሆነ ግን በግልጽ አልታወቀም።
ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ