ኹከት የቀላቀለዉ የቀኝ ጽንፈኞች ተቃዉሞ በታላቅዋ ብሪታንያ
ሐሙስ፣ ነሐሴ 2 2016በሰሜን ምዕራብ እንግሊዝ የባሕር ዳርቻ ከተማ ሳውዝፖርት በቴይለር ስዊፍት ስም በተዘጋጄ የዳንስ ድግስ ላይ በጅምላ በተሰራጨ የተሳሳተ መረጃ ምክንያት የተቀሰቀሰዉ ተቃዉሞ ዛሬም እንደቀጠለ ነዉ። በተለይ በመጤዎች ላይ ያነጣጠረዉ የቀኝ ጽንፈኞች የአደባባይ ተቃዉሞ በተለይ ሙስሊሞች ላይ ያነጣጠረ ነዉ ተብሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ኬይር ስታርመርወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል። በቁጥጥር ስር የዋሉም አሉ።
ብሪታንያ ውስጥ የሦስት ሴት ልጆች ሕይወት የጠፋበት የጩቤ ጥቃት በኋላ የተሳሳተ መረጃ ከተሰራጨ በኋላ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ዒላማ ያደረገ ረብሻ በመላ ሀገሪቱ እየተስፋፋ መሆኑ ተመልክቷል። ትናንት እሑድ በሰሜን እንግሊዝ ፤ ሮዘርሃም ከተማ የጥገኝነት ጠያቂዎች መኖሪያ ነው ተብሎ በሚታሰበው ሆቴል የቀኝ ዘመም ቡድኖች ጥቃት ለማድረስ ሆቴሉን ሰብረው ገብተዋል። በርካታ ፖሊሶችም ጥገኝነት ጠያቂዎችን ለማዳን ሲታገሉ መጎዳታቸው ተገልጿል።
በብሪታንያ ከተሞች ከተከሰቱ የመጤ ጠል ቡድኖች ከፈጸሙት ተከታታይ ጥቃት ካለፈዉ ሳምንት የጀመረዉ ኹከት የቅርብ ጊዜው ነው። ቅዳሜ ዕለት በሊቨርፑል፣ ማንቸስተር፣ ብሪስቶል፣ ብላክፑል እና ሃል እንዲሁም በሰሜን አየርላንድ ቤልፋስት በተደረጉ መጤ ጠል የቀኝ አክራሪ ሰልፎች፤ ላይ በተቀሰቀሰ ኹከት ከ 150 የሚጡ ሰዎች ታስረዋል።
በቅርቡ አክስኤል ሩዳኩባና የተባለ አንድ የ17 ዓመት ወጣት ሦስት ታዳጊዎችን በስለት ወግቶ ገድሏል በሚል ተጠርጥሮ የተከሰሰ ሲሆን፤ ተጠርጣሪው ወጣት ብሪታንያ ተወልዶ ያደገ መሆኑንም የሀገሪቱ ፖሊስ ገልጿል። ተጠርጣሪው ወደ የወጣቶች ማቆያ ጣቢያ ተወስዶ ጥቅምት ወር ላይ ፍርድ ቤት ይቀርባልም ተብሏል።
ያም ሆኖ የቀኝ አክራሪ የማኅበራዊ መገናኛ ገፆች የሳውዝፖርቱ ጥቃት ተጠርጣሪ፤ በጀልባ ወደ እንግሊዝ የገባ ጥገኝነት ጠያቂ ነው በሚል የውሸት መረጃ በማሰራጨታቸው፤ በሀገሪቱ በሚገኙ ጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ ጥቃት ለማድረስ በተደረገው ሙከራ ሁኸት ተፈጥሯል።
ብጥብጡ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬይር ስታርመር ወደ መንበረ ሥልጣን ከመጡ ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ የመጀመሪያው ትልቅ ፈተና ሆኖ ታይቷል። ብጥብጡን ያወገጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዘራፊዎች የሀገሪቱን ሀዘን እየጠለፉ ነው፤ አስቸኳይ ፍርድ እንዲተላለፋባቸዉ ሲሉ ዛሬ አሳስበዋል።
ፖሊስ ከጥቃቱ ጀርባ የእንግሊዝ መከላከያ ሊግ የሚባለው ፀረ እስልምና ድርጅት አለ ብሎ እንደሚምን ተመልክቷል። «ተስፋ እንጂ ጥላቻ አያስፈልግም» /Hope Not Hate/ የተባለው የጸረ-ዘረኝነት ዘመቻ ቡድን በሳምንቱ መጨረሻ ሊደረጉ የታቀዱ 30 ተጨማሪ፤ ዝግጅቶችን ደርሼባቸዋለሁ ብሏል።
መንግሥት ፤ በብሪታንያ በመኖሪያ ቤት እጥረት ሳቢያ የጥገኝነት ጥያቄዎችን በሆቴል የማስተናገድ እርምጃ፣ በእንግሊዝ የቀኝ ክንፍ እና የስደት ጠያቂ ግለሰቦች ለዓመታት በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲቀርብበት ቆይቷል።
የለንደኑ ወኪላችን ድልነሳ ጌታነህ ስጋት ስለቀሰቀሰዉ የብሪታንያዉ ተቃዉሞ አነጋግረነዋል። ሙሉ ቃለ ምልልሱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ!
ድል ነሳ ጌታነህ / አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሰ