1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

እንወያይ፣ የእስራኤል-ዩናይትድ ስቴትስና የኢራን ጦርነት ዳፋ ለአፍሪቃ ቀንድ

ነጋሽ መሐመድ
እሑድ፣ መጋቢት 27 2018

የዓለም የቱሪዝም፣ የዓየር መንገድና የሆቴል ኩባንዮች ከስረዋል።የከፋዉ ኢራን የሆርሙስ ወሽመጥን መዝጋትዋ ነዉ።የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ ዘይት፣ የማደበሪያ ንጥረ ነገር፣ ማዕድናት፣ የግብርና ዉጤቶችና ሌሎች ሸቀጦች የሚተላለፍበበት መስመር በመዘጋቱ ጦርነቱን የከፈቱት የዩናይትድ ስቴትስና የእስራኤልን ጨምሮ የዓለም ምጣኔ ሐብት እየተሽመደመደ ነዉ።

https://p.dw.com/p/5BdgB
የየመን አንሳር አላሕ ወይም ሁቲዎች በጋዛዉ ጦርነት ከመቷቸዉ መርከቦች አንዱ።አብዛኛ የመንን የሚቆጣጠሩት የአንሳር አላሕ ተዋጊዎች በቀይ ባሕር ላይ ከእና ወደ እስራኤል የሚቀዝፉ መርከቦችን  ይመቱ ነበር።አሁንም የብብ ኤል መንደብን መተላለፊያ ለመዝጋት እየዛቱ ነዉ
የየመን አንሳር አላሕ ወይም ሁቲዎች በጋዛዉ ጦርነት ከመቷቸዉ መርከቦች አንዱ።አብዛኛ የመንን የሚቆጣጠሩት የአንሳር አላሕ ተዋጊዎች በቀይ ባሕር ላይ ከእና ወደ እስራኤል የሚቀዝፉ መርከቦችን ይመቱ ነበር።አሁንም የብብ ኤል መንደብን መተላለፊያ ለመዝጋት እየዛቱ ነዉምስል፦ EUNAVFOR ASPIDES/Handout/REUTERS

እንወያይ፣ የእስራኤል-ዩናይትድ ስቴትስና የኢራን ጦርነት ዳፋ ለአፍሪቃ ቀንድ

 

እስራኤልና ዩናይትድ ስቴትስ ባለፈዉ የካቲት 21፣2018 ኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነትና የኢራን አፀፋ የመካከለኛዉ ምሥራቅ ሐገራትን እያወደመ፣ የዓለምን ምጣኔ ሐብት እያሽመደመደ ነዉ።የዋሽግተንና የቴል አቪቭ መሪዎች በድርድር መሐል በኢራን ላይ ጦርነት ለማወጃቸዉ የሚሰጡት ምክንያት መሪዎቹ እንዳሉበት ጊዜና ስሜት የሚለዋወጥ በመሆኑ ትክክለኛ አላማቸዉን በግልፅ ማወቅ ለተንታኖች አ,ስቸጋሪ ነዉ።

የዩናትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕናየእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቢኒያሚን ኔታንያሁ  ዓላማ-ግቡን፣ አንዴ የኢራንን ሥርዓት በኃይል ለመቀየር፣ ሌላ ጊዜ የኢራንን ሕዝብ ነፃ ለማዉጣት በትራምፕ ቋንቋ ኢራንን ለኢራኖች ለማስረከብ፣ ደግሞ ሌላ ጊዜ የኢራንን የኑክሌርና የሚሳዬል ተቋማትና መርሐ- ግብሮችን ለማዉደም ባሉት ጦርነት የኢራን መሪዎችን ጨምሮ ብዙ ሺዎች አልቀዋል።ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል።

የኢራን፣ የእስራኤል፣ የሊባኖስ፣ የኢራቅ፣ የዮርዳኖስና የፋርስ ወይም የአረብ ባሕረ ሠላጤ አካባቢ ሐገራት የመሠረተ ልማት አዉታሮች ወድመዋል።የዓለም የቱሪዝም፣ የዓየር መንገድና የሆቴል ኩባንዮች ከስረዋል።የከፋዉ ኢራን የሆርሙስ ሰርጥ ወይም ወሽመጥን መዝጋትዋ ነዉ።የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ ዘይት፣ የማደበሪያ ንጥረ ነገር፣ ማዕድናት፣ የግብርና ዉጤቶችና ሌሎች ሸቀጦች የሚተላለፍበበት መስመር በመዘጋቱ ጦርነቱን የከፈቱት የዩናይትድ ስቴትስና የእስራኤልን ጨምሮ የዓለም ምጣኔ ሐብት እየተሽመደመደ ነዉ።

ጉዳቱ በሁሉም ሐገራት ላይ ቢሆንምኢትዮጵያን በመሳሰሉ ደሐ የአፍሪቃ ሐገራት ላይ ያሳደረዉ ከፍተኛ ጫና የየሐገራቱን ሕዝብ ኑሮ እያመሰቃቀለዉ ነዉ።የዚያኑ ያክል አንዳድ ተንታኞች እንደሚሉት ጦርነቱና ሥጋቱ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ይጫራል ተብሎ የሚፈራዉን ሌላ ዙር ጦርነት ባያስቀረዉ እንኳን ለጊዜዉም ቢሆን አዳፍኖታል።በየሰበብ አስባቡ ይሰማ የነበረዉ የአዲስ አበባና የአስመራ የዉጊያ ዛቻና ፉከራ ቀንሷል።

ይሁንና ባለፈዉ ሳምንት የየመንአንሳር አላሕ ወይም ሁቲዎች ኢራንን ደግፈዉ ከጦርነቱ መግባታቸዉ፣ በተለይም የባብ-ኤል መንዳብ የባሕር በርን ለመዝጋት መዛታቸዉ ለአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ ሐገራት ተጨማሪ ሥጋት ሆኗል።ሁለተኛ ወሩን የያዘዉ የእስራኤል-አሜሪካ ጦርነት በአፍሪቃ ቀንድ ላይ ያሳረፈዉ  ጫና፣ ሥጋትና ደረጃዉ የዛሬ ዉይይታችን ርዕሥ ነዉ።ሶስት እንግዶች አሉን።

ሙሉ ዉይይቱን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ

ነጋሽ መሐመድ