1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ ለሽግግር ፍትህ ዝግጁ ነች?

Eshete Bekele
እሑድ፣ መጋቢት 17 2015

ኢትዮጵያ ለሽግግር ፍትህ ዝግጁ ነች? የፍትህ ሚኒስቴር ካቋቋመው ከፍተኛ የባለሙያዎች ቡድን አቶ ምስጋናው ሙሉጌታ እና ዶ/ር ማርሸት ታደሰ፤ በሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት የሰብዓዊ መብቶች መርሐ-ግብር ተባባሪ ዳይሬክተር ዶክተር አባድር ኢብራሒም እና ዘ-ሔግ በሚገኝ ፍርድ ቤት በአማካሪነት የሚሰሩት አቶ ካሳሁን ሞላ በውይይቱ ተሳትፈዋል

https://p.dw.com/p/4PF8q
Äthiopien | Tigray Krise Nahrungsmangel
ምስል Ben Curtis/AP Photo/picture alliance

ውይይት፦ ኢትዮጵያ ለሽግግር ፍትህ ዝግጁ ነች?

ኢትዮጵያ ከብርቱ ጦርነት እና በተለያዩ አካባቢዎች ከተከሰቱ ደም አፋሳሽ ግጭቶች በኋላ ለሽግግር ፍትህ በዝግጅት ላይ ትገኛለች። የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በፕሪቶሪያ በተፈረመ ግጭት የማቆም ሥምምነት ጋብ ቢልም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ዜጎችን ለሞት፣ መፈናቀል እና ንብረትን ለውድመት የሚዳርጉ ግጭቶች ኹነኛ መፍትሔ አሁንም አላገኙም። 

የፍትህ ሚኒስቴር ያቋቋመው የከፍተኛ ባለሙያዎች ቡድን ባዘጋጀው ሰነድ ግጭት፣ የርስ በርስ ጦርነት፣ የዜጎች ስደት እና ሞት የበረታበት የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የሽግግር ፍትህን አስፈላጊ እንደሚያደርገው ያትታል። ይኸ በ36 ገጾች የተቀነበበ ሰነድ እንደሚለው "የተሳካ የሽግግር ፍትህ ሒደት ለሀገረ-መንግሥቱ ግንባታ እና ቀጣይነት" ከፍ ያለ ሚና ይኖረዋል። በኢትዮጵያ የተፈጸሙ በደሎች እንዲሽሩ፤ ቁርሾዎች እንዲጠገኑ በማድረግ ወደ ዴሞክራሲ የሚደገው ሽግግር እንዲሳካ እና ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ሊያደርግ እንደሚችልም ታምኖበታል። የሽግግር ፍትህ ሥርዓት ለሰብዓዊ መብቶች መከበር እና ለየህግ የበላይነት መረጋገጥ የማይተካ አስተዋጽዖ እንደሚኖረውም ባለሙያዎቹ በሰነዱ አስፍረዋል። 

ይኸ በጥር 2015 ይፋ የተደረገ እና ከባለ ድርሻ አካላት ግብዓት ለመሰብሰብ የተዘጋጀ ሰነድ በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ከተሞች እንዲሁም በአስራ አንዱም ክልሎች ውይይት የሚደረግበት ነው። ከውይይቶቹ በኋላ በግንቦት ወር የፍትህ ሚኒስቴር ያቋቋመው የባለሙያዎች ቡድን “አጠቃላይ፣ የተቀናጀ እና አውድ-ተኮር የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ሰነድ” ያዘጋጃል። ከሰነዱ በኋላ ፖሊሲ ሲጸድቅ ኢትዮጵያ ወደ ሽግግር ፍትህ ትግበራ ትገባለች። 

ይኸ የእንወያይ መሰናዶ ኢትዮጵያ ለሽግግር ፍትህ ዝግጁ ነች? ሲል ያጠይቃል። በውይይቱ የፍትህ ሚኒስቴር ካቋቋመው ከፍተኛ የባለሙያዎች ቡድን አቶ ምስጋናው ሙሉጌታ እና ዶክተር ማርሸት ታደሰ፤ በሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት የሰብዓዊ መብቶች መርሐ-ግብር ተባባሪ ዳይሬክተር ዶክተር አባድር ኢብራሒም እና ዘ-ሔግ በሚገኝ ፍርድ ቤት በአማካሪነት የሚሰሩት አቶ ካሳሁን ሞላ ተሳትፈዋል። 

ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ 

እሸቴ በቀለ