1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢቮን አኪ ሳውይር የ 2024 የጀርመን አፍሪቃ ሽልማት አሸናፊ

ማክሰኞ፣ መስከረም 14 2017

የጀርመን አፍሪቃ ድርጅት እንደሚለው አኪ ሳውይር በፕሮጀክቶቻቸው በቱሪዝም፣ በቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ መሠረተ ልማትን በማስፋፋት፣ እና በአረንጓዴ ኤኮኖሚ የስራ እና የውረታ ወይም የኢንቬስትመንት እድሎችን እየፈጠሩ ነው። ከዚህ ሌላ በትራንስፖርት ዘርፍም አዳዲስ ሃሳቦችን ያፈልቃሉ።

https://p.dw.com/p/4l1Jf
ከግራ ወደ ቀኝ የንስ ክራውስ ማሰ በሴራልዮን የጀርመን አምባሳደር፣ኢቮን አኪ ሳውይር የጀርመን አፍሪቃ ሽልማት አሸናፊ እና የጀርመን አፍሪቃ ድርጅት ዋና ፀፊ ዛቢነ ኦድህያምቦ
ከግራ ወደ ቀኝ የንስ ክራውስ ማሰ በሴራልዮን የጀርመን አምባሳደር፣ኢቮን አኪ ሳውይር የጀርመን አፍሪቃ ሽልማት አሸናፊ እና የጀርመን አፍሪቃ ድርጅት ዋና ፀፊ ዛቢነ ኦድህያምቦምስል DW

ኢቮን አኪ ሳውይር የዘንድሮው የጀርመን አፍሪቃ ሽልማት አሸናፊ


የሴራልዮን ዋና ከተማ የፍሪታውን ከንቲባ ኢቮን አኪ ሳውየር ለዘንድሮው የጀርመን አፍሪቃ ሽልማት ተመርጠዋል። የጀመሩትን ሁሌም ከፍፃሜ የሚያደርሱት ተሸላሚዋ ኢቮን አኪ ሳውየር ከተማቸውን በብዙ ዘርፎች ለማሳደግ በቅተዋል። ፋና ወጊም አድርገውታል።

ኢቮን አኪ ሳውይር  ከፕሮጀክታቸው አንዱን ሲያስጎበኙ
ኢቮን አኪ ሳውይር ከፕሮጀክታቸው አንዱን ሲያስጎበኙምስል DW

ኢቮን አኪ ሳውይር ምን ሰሩ?

የምዕራብ አፍሪቃዊቷ አገር የሴራልዮን ዋና ከተማ ፍሪታውን በአሁኑ ጊዜ ፈሳሽ ቆሻሻን አክሞና አጣርቶ ለልዩ ልዩ ጥቅሞች እንዲውል የሚያደርግ ቦታ አለው። በከተማይቱ 160 የውሀ ማጠራቀሚያዎች እና የዝናብ ውሀ የሚከማችበትም ስርዓቶችም አሏት። የመጸዳጃ ቤት ቆሻሻዎችም ወደ ብስባሽ ባዮጋዝና ማሞቂያ ሸክላዎች የሚቀየሩበት አሰራር አላት ከተማዋ።  ይህ ደግሞ ምግብ ለማብሰል ዛፎች እንዳይቆረጡ በማድረግ ለደን ጥበቃ አስተዋጽኦ ያደርጋል።  የከተማይቱ የውሀ አቅርቦት ዘላቂነትም ተሻሽሏል። በፀሐይ ኃይል በሚሰሩ የውሀ ማጣሪያ ስርዓቶች ባሏቸው ኪዮስኮች  በርካታ ማኅበረሰቦች ለመጀመሪያ ጊዜ ንጹህ ውሀ እንዲያገኙ ረድቷል። ሴቶችም የራሳቸውን ንግድ እንዲጀምሩ አግዟቸዋል። ሴቶች ከአቅራቢያቸው ውሀ ሲያገኙ ፣ ለወሲባዊ ጥቃት የሚያጋልጣቸውን ከቤት ራቅ ብሎ ውሀ መቅዳትን መቀነስም ያስችላል ።

የጎርጎሪዮሳዊው 2023 የጀርመን አፍሪቃ ሽልማት ለካሜሮን ብሔራዊ የሴቶች ስብስብ ተሰጠ

 አኪ ሳውይር ለጀርመን አፍሪቃ ሽልማት እንዴት በቁ 

የጀርመን አፍሪቃ ድርጅት በጀርመንኛው ምህጻር DAS ኢቮን አኪ ሳዌሬን ለዘንድሮው የጀርመን አፍሪቃ ሽልማት የመረጣቸው ለዘላቂ የከተማ ልማትና የማኅበረሰብ ተሳትፎ ላሳዩት ቁርጠኝነት ነው።  ይህን ቁርጠኝነታቸውም ድርጅቱ የጸና ነው ያለው። «ከተማዋ በዘላቂነት  መኖር የሚቻልባት እና  ሁሉንም እኩል ተጠቃሚ የምታደርግ እንድትሆን የተመኙበትን ራዕያቸውን ደረጃ በደረጃ እየተገበሩ ነው።»ብሏል ሸላሚው ድርጅት ሴራልዮን የተወለዱት የ56 ዓመትዋ ኢቮን አኪ ሳዌርን ያደጉት ጋናና ካናዳ ነው ። ከፍተኛ ትምሕርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ለንደን ውስጥ ከ25 ዓመታት በላይ በፋይናንስ ሙያና በኦዲተርነት ሰርተዋል። በሴራልዮን በህዝብ አገልግሎት ዘርፍ ውስጥ መስራት የጀመሩት በጎርጎሮሳዊው 2014 እና 2015 በደረሰው የኤቦላ ወረርሽኝ ወቅት ነው።በኋላም በ2018 ለአስርት ዓመታት የርስ በርስ ጦርነት የተካሄደባት የሴራልዮን ዋና ከተማ የፍሪታውን ከንቲባ ሆኑ ታወዳጅዋ ፖለቲከኛ በሰኔ 2023 ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን ተመረጡ። 

ኢቮን አኪ ሳዌሬንይ የፍሪታውን ከንቲባ
ኢቮን አኪ ሳዌሬይ የፍሪታውን ከንቲባ ምስል Bryan Bedder/Getty Images for Bloomberg Philanthropies

የአኪ ሳዌር ፕሮጀክቶችና ዓላማቸው

የጀርመን አፍሪቃ ድርጅት እንደሚለው አኪ ሳዌር በፕሮጀክቶቻቸው በቱሪዝም፣ በቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ መሠረተ ልማትን በማስፋፋት፣ እና በአረንጓዴ ኤኮኖሚ የስራ እና የውረታ ወይም የኢንቬስትመንት እድሎችን እየፈጠሩ ነው። ከዚህ ሌላ በትራንስፖርት ዘርፍም አዳዲስ ሃሳቦችን ያፈልቃሉ። ለምሳሌ በፍሪታውን የትራፊክ መጨናነቅንና የአየር ብክለትን ለመቀነስ በአየር ላይ በሚዘረጋ በኤሌክትሪክ ገመድ የሚንቀሳቀሱ የኬብል መኪናዎችን በፍሪታውን መጠቀሙ ያዋጣ እንደሆነ ጥናት እንዲካሄድ አድርገዋል። ይህ ከተሳካም ነዋሪዎች ወደ ማዕከላዊ ከተማ ቀበሌዎች ጊዜ ሳይፈጁ ለመጓጓዝ ያስችላቸዋል። የኬብል መኪና የሚገነባ ከሆነ ፍሪታውንን ከላይ ሆኖ የማite እድል ይሰጣል። በአኪ ሳውይር የከንቲባነት ዓመታት 977 ሺህ አዳዲስ ዛፎች ተተክለዋል። ዓላማውም የአየር ንብረት ለውጥ ያሳደራቸውን ተጽእኖዎች መቀነስና የከተማዋን ዛፎች መጠበቅ ነው። በዚህ አሰራር ውስጥም ዜጎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት መንገድም አለ። ዛፍ የሚተክሉ እና እድገታቸውንም በዲጂታል መንገድ የሚከታተሉ ዜጎችም ገቢ ያገኛሉ።

ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የዘንድሮው የጀርመን አፍሪቃ ሽልማት አሸናፊ

የፍሪታውን ከተማ ልምዷን ለሌሎች የአፍሪቃ ከተሞች እያካፈለች ነው

ፍሪታውን ምክር እየተቀበሉ ነው። የጀርመን አፍሪቃ ድርጅት ኢቮን አኪ ሳውይር ለአፍሪቃ ፖለቲከኞች አነሳሽ ናቸው ይላል። ለምሳሌ የከተማይቱ ነዋሪዎች በዘላቂነት በውሳኔዎችና አተገባበራቸው ላይ እንዴት ተካፋይ እንደሚሆኑም ምሳሌ ናቸው።ከስራቸe መካከል የሰዎችን ሕይወት መቀየር አንዱ ተግባራቸው ነው።  በዚህ ስራ ውስጥም  ከመንግሥት በተጨማሪ የንግዱ ማኅበረሰብ እና የሲቪል ማኅበራት ተወካዮች ይሳተፋሉ። አኪ ሳውይር ምድራችንን አረንጓዴ ከማድረግና ከልማት ዘርፍ ጋር በተያያዙ ስራዎች ላይ ማተኮር የኤኮኖሚ እደገትን ያፋጥናል፣ በከተማችንም ለመጪው ትውልድ የሚሆን ሀብት ይፈጥራል ብለዋል።

 

ኢቮን አኪ ሳዌሬይ ከከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር
ኢቮን አኪ ሳዌሬይ ከከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ምስል DW

የሽልማቱ ስነ ስርዓት በጎርጎሮሳዊው ጥቅምት 16 በበርሊን ይካሄዳል

ለጀርመን አፍሪቃ ሽልማት በመመረጣቸው ከልክ በላይ እንደተደሰቱና ክብር እንደሚሰማቸው ለዶቼቬለ የተናገሩት አኪ ሳውይር ሽልማቱ በግል የተሰጣቸው እውቅና ብቻ ሳይሆን ለመላ ሀገሪቱ እንደተሰጠ እውቅና እቆጥረዋለሁ። የምቀበለው ከተማዋን የመቀየር ዓላማ ይዘው ከኔ ጋር በሚሰሩ የስራ ባልደረቦቼና በፍሪታውን ከተማ ነዋሪዎች ስም ነው የምቀበለው» ብለዋል።እርሳቸው እንዳሉት እዚህ የደረሱት ያለተግዳሮቶች አይደለም። ሆኖም ስራችን በሀገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም እውቅና በማግኘቱ በጣም ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።የጀርመን አፍሪቃ ሽልማት ለደቡብ አፍሪቃዊቷ

አኪ ሳውይር የጎርጎሮሳዊውን 2024 የጀርመን አፍሪቃ ሽልማት የሚቀበሉት ከሦስት ሳምንት በኋላ በርሊን ውስጥ ከጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቤርብል ባስ ነው። 20 ዳኞች ያሉት ሸላሚው የጀርመን አፍሪቃ ድርጅት አኪ ሳውይርን ለሽልማቱ የመረጠው ከቀረቡለት በርካታ እጩዎች መካከል ነበር። በጀርመን ከጎርጎሮሳዊው 1993 አንስቶ የሚበረከተው ይህ የተከበረ ሽልማት ለዴሞክራሲ፣ለሰላም ለሰብዓዊ መብቶችለዘላቂ ልማት ፣ለምርምር ስራዎች ለኪነጥበብ እና ባህል እንዲሁም በአፍሪቃ ማኅበራዊ ጉዳዮች በጽናት አስተዋጽኦ ላደረጉ  አፍሪቃውያን ነው ።

 

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ