1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢሕአፓ ምክትል ሊቀ መንበር ተፈቱ ፣ ሊቀ መንበሩ ታሰሩ

ሐሙስ፣ መጋቢት 19 2016

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ሊቀ መንበር ረዳት ፕሮፌሰር ዝናቡ አበራ መታሰራቸው ተገለፀ። የፓርቲው ሊቀ መንበር ማክሰኞ ዕለት በፖሊስ በቁጥጥር ሥር ሲውሉ «የእርስ በእርስ ጦርነት ይብቃ» በሚል ሰላማዊ ሰልፍ ለማዘጋጀት ሲንቀሳቀሱ ተይዘው አዋሽ አርባ ለወራት በእሥር ላይ የቆዩት የፓርቲው ምክትል ሊቀ መንበር ሰሞኑን ተፈተዋል።

https://p.dw.com/p/4eEBh
የፍትህ ተምሳሌታዊ ፎቶ
የኢሕአፓ ምክትል ሊቀ መንበር ተፈቱ ፣ ሊቀ መንበሩ ታሰሩምስል Fotolia/Sebastian Duda

የኢህአፓ መሪዎች እስር

 

ፖለቲከኞች የታሠሩት ምክንያት ምንድን ነበር?

ኅዳር 30 ቀን 2016 ዓ. ም «ጦርነት ይቁም ሰላም ይስፈን»፤ ሁሉን አቀፍ ውይይት እና ድርድር ከታጣቂ ኃይሎች ጋር ይካሄድ፣ በአማራ ማንነታቸው የታሰሩ በአስቸኳይ ይፈቱ፣ የተፈናቀሉ ዜጎች የፖለቲካ መጠቀሚያ አይሁኑ» የሚሉ መፈክሮችን የያዘ ሰላማ ሰልፍ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ 13 ፖለቲከኞች አራቱ ኅዳር 27 ቀን ተይዘው ነበር። ከእነዚህ አንዱ የኢሕአፓ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበር መጋቤ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት ሲሆኑ ለሦስት ወራት ታስረው ባለፈው ሐሙስ ተለቀዋል።

«ፋኖን እና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትን ትደግፋለህ በሚል አንድ ጊዜ ምርመራ አድርገውልኝ ነበር። ሰልፍን ሽፋን በማድረግ በአቋራጭ ሥልጣን ለማግኘት፣ አዲስ አበባን ለመበጥበጥ እና የሁከት ማዕከል ለማድረግ ተንቀሳቅሰሃል በሚል» አንድ ጊዜ እንደተመረመሩም ገልፀዋል።

«አካልን ነፃ የማውጣት ክስ» ጠበቆች አቅርበው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተቀብሎት በአስቸኳይ ይፈቱ የሚል ትእዛዝ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም ያ ሳይሆን ቀርቶ በእሥር ከርመው በምን እንደተፈቱ እንኳን ሳያውቁ እና ማብራሪያም ሳይሰጣቸው መፈታታቸውን የገለፁት ፖለቲከኛው አብረዋቸው ታሥረው የነበሩት የትንሣኤ ሰባ እንደርታ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርም መለቀቃቸውን ተናግረዋል። ታሥረውበት የቆዩት አዋሽ አርባ የተባለው ስፍራ ከአስከፊነቱ አንፃር እንዲዘጋ ጠይቀዋል።

የኢሕአፖ ሊቀ መንበር መታሠር

ከትናንት በፊት ማክሰኛ የኢሕአፓ ሊቀ መንበር ረዳት ፕሮፌሰር ዝናቡ አበራ መታሠራቸውን የነገሩን መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት ትናንት ፍርድ ቤት መቅረባቸውንና የጊዜ ቀጠሮ እንደተጠየቀባቸው ገልፀዋል። የፓርቲ መሪው መንግሥት ፖለቲከኞችን ከማሳደድ ይቆጠብ ሲሉ ጠይቀዋል።

የፌዴራል የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል የተባለው አካል አራቱን የሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪዎች በያዘበት ወቅት በአዲስ አበባ «የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ያቀዱ» በሚል የተጠረጠሩ 97 ሰዎችን ማሰሩን ገልጾ ነበር።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ