1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አጣዬ በ3 ቀናት ብርቱ ውጊያ ሕይወት ጠፍቷል

ሐሙስ፣ መጋቢት 12 2016

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተደጋጋሚ በታጣቂዎች ውድመት እና ቃጠሎ የደረሰባት አጣየ ከተማ ዙሪያ ካለፈው ሦስት ቀናት ጀምሮ በአካባቢው ነዋሪዎችና “ከሌላ ቦታ መጥተዋል” በተባሉ ኃይሎች መካከል ብርቱ ውጊያ ሲካሄድ መሰንበቱን ተገለጠ ። በውጊያው የሰዎች ሕይወት ማለፉን የዓይን እማኞች ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል ።

https://p.dw.com/p/4dyg1
Äthiopien I Keine Bewegung in der Region Oromia - Militante hatten vor jeder Bewegung gewarnt
ምስል Seyoum Getu/DW

ዛሬ አልፎ አልፎ የተኩስ ድምፅ ይሰማል

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተደጋጋሚ በታጣቂዎች ውድመት እና ቃጠሎ የደረሰባት አጣየ ከተማ ዙሪያ ካለፈው ሦስት ቀናት ጀምሮ በአካባቢው ነዋሪዎችና "ከሌላ ቦታ መጥተዋል” በተባሉ ኃይሎች መካከል ብርቱ ውጊያ ሲካሄድ መሰንበቱን ተገለጠ ። በውጊያው የሰዎች ሕይወት ማለፉን የዓይን እማኞች ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል ። እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ፦ ዛሬ አልፎ አልፎ የተኩስ ድምፅ ይሰማል፣ በከተማዋ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ የለም ። 

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አጣየ ከተማ ዙሪያ ሰሞኑን ሞትን ያስከተለ ውጊያ እንደነበር ነው ነዋሪዎቹ ለዶይቼ ቬለ የገለፁት፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ "ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ” ያሏቸው ኃይሎች ለሁለት ቀናት ከሚሊሺያዎችና አካባቢው ሚሊሺዎች ጋር ውጊያ ካደረጉ በኋላ ትናንት ከሰዓት በኋላ ወደመጡበት ተመልሰዋል ብለዋል።

" የተለያዩ ኃይሎች ከትናንት ወዲያ ተደራጅተው መጥተው  ጥቃት ከፍተው ነበር አጣየ ከተማ ላይ ሙሉቀን ሲታኮሱ ዋሉ፣ ከሚሊሺያዎችና ከከተማው ናዋሪ ጋር ፣ ሲታኮሱ ውለው ሄዱ፣ ትናንትና በድጋሜ መጡ፣ ከተማ ውስጥ ለመግባት ሙከራ አድርገው ነበር፣ እስከ ቀኑ 6 ሰዓት ውጊያ አደረጉ፣ እስከ 9 ሰዓት የማትቃት ሙከራ አደረጉ ወደ 10 ሰዓት ላይ ተመትተው ተመልሰዋል፡፡” ብለዋል፡፡

ውጊያው በማንና በማን መካከል ነው ተብለው የተጠየቁት አንድ የአጣየ ከተማ ነዋሪ አስተያት ሰጪ፣ "የአማራ ሚሊሺያና የግል ታጣቂዎች አሉ፣ ከዚያኛው በኩል ደግሞ ከተለያዩ ከተለያየ ቦታ የተሰባሰበ ኦነግ ሸኔ ነው፣ ህይወታቸው ካለፉት ውስጥ መታወቂያቸው ሲታይ የአካባቢ ሰዎች አይደሉም፣ ከሌላ ቦታ የመጡ ናቸው፡፡” ነው ያሉት፡፡

በውጊያው በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት መድረሱን  የሚናገሩት አስተያየት ሰጪው ጉዳቱ አሁን ከሚባለው በላይ ሊሆን እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡

" አጠቃላይ ጉዳቱን ማየት አልቻልንም፣ 6 ሰዎች በእኛ በኩል ህይወታቸው አልፏል፣ ከሌላው በኩል ብዙ ነው፣ አጣየ ከተማ ውስጥ አንድ ቦታ ላይ 4 አስከሬን ታይቷል፣ ሌላም ቦታላይ አለ፡፡”

ሌላ የከተማዋ ነዋሪ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የአጣየ ከተማ የታጣቂዎች ኢላማ ሆናለች ብለዋል፣ ሰሞኑንም እንደተለመደው በከተማዋና ከተማዋ ዙሪያ ጥቃት ተከፍቶባት ነበር  ነው ያሉት፡፡

በየጊዜው በከተማዋና አካባቢዋ ላይ የሚደረገው ጥቃት የከተማዋን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች በእጅጉ ጎድቷል ሲሉ ገልጠዋል፡፡

ጉዳዩን አስመልክተን ተጨማሪ አስተያየት እንዲሰጡን  በአማራ ክልል ለኦሮሞ ብሔረሰብ ሰአስተዳደር ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ አሊ መሐመድ ስልክ ደውልን ነበር፡፡

"አሁን በጉዳዩ ዙሪያ ከአጎራባች አመራሮችና የቀበሌ አመራሮች ጋር ውይይት ለማድረግ ከሰዓት በኋላ ፕሮግራም ይዘናል፣ ከዚያ በኋላ ብንነጋገር ይሻላል፡፡” የሚል ምላሽ ሰጥተውናል፡፡

በአካባቢው አሁን የመከላከያ ሰራዊት የገባ በመሆኑ አልፎ አልፎ ከሚሰማ የተኩስ ድምጽ ውጪ ዛሬ አካባቢው በአንጻራዊነት የተሻ ለ የፀጥታ ሁኔታ መኖሩንም አስተያየት ሰጪዎቹ አመልክተዋል፡፡

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር የሚመለከተው አካል በስልክ አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ