1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አንጋፋው ድምጻዊ ጌታቸው ካሣ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

ረቡዕ፣ የካቲት 13 2016

የአንጋፋው ድምጻዊ ጌታቸው ካሣ ህልፈት የተሰማው ዛሬ ማለዳ ነበር። ህክምናውን ሲከታተል በነበረበት የካቲት 12 ሆስፒታል ህይወቱ ያለፈችው ሌሊት ላይ መሆኑን አንጋፋው የሙዚቃ ባለሙያ ዳዊት ይፍሩ በተለይ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4chtI
Mikrophon Mikrofon Symbolbild Pop Musik Bühne Sänger Band
ምስል Fotolia/nikkytok

በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ከ50 በላይ ዓመታት ነግሶ የኖረው የጌታቸው ካሳ ህልፈት

የአንጋፋው ድምጻዊ ጌታቸው ካሣ ህልፈት የተሰማው ዛሬ ማለዳ ነበር። ህክምናውን ሲከታተል በነበረበት የካቲት 12 ሆስፒታል ህይወቱ ያለፈችው ሌሊት ላይ መሆኑን አንጋፋው የሙዚቃ ባለሙያ ዳዊት ይፍሩ በተለይ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ጌታቸው ካሳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጤናው ሁኔታ እጅጉን ማሽቆልቆሉን ተከትሎ የሙዚቀኛው የቅርብ ሰዎች እና አጋሮች በመረባረብ ሆስፒታል እንዳስገቡት መረጃዎች ያመለክታሉ ።  የድምጻዊ ጌታቸው ካሳ የቀብር ስነ ስረዓት በሚፈጸምበት ሁኔታ ላይ ምክክር እየተደረገ መሆኑን ለመረዳት ችለናል።

 ጌታቸው ካሣ ዘመናዊ ሙዚቃ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተጀመረ አንስቶ አሁን ባበረከቷቸው የሙዚቃ ስራዎቻቸው አንቱታን ካተረፉ ድምጻዊያን መካከል አንዱ እንደነበር በርካቶች ይመሰክሩለታል።

የጌታቸው ህልፈት ከሆስፒታል ተደውሎ እንደተነገራቸው የነገሩን አንጋፋው የሙዚቃ ሰው ዳዊት ይፍሩ ፤ ጌታቸው ኢትዮጵያ ካፈራቻቸውአንጋፋ የሙዚቃ ሰዎች መካከል አንዱ እንደነበር ያወሳሉ ።ድምጻዊ ዓለማየሁ እሸቴ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

« ጌታቸው ካሣ እንግዲህ አንጋፋ ከሚባሉ መካከል ነው ። ደረጃው ያ ነው ። ግን ጌታቸው ካሣ ስራ የጀመረው በናይት ክለብ ነው ። ሱምብሬሮ የሚባል ክለብ ፣ ፓትሪስሊሙምባ የሚባል ክለብ ፣ ከዚያ በኋላ ዙላ ክለብ እያለ ኢትዮ ስታር ባንድ ፣ ዋልያስ ባንድ  እያለ ሁሉንም ባንድ አካቷል። በዚህ ዘመናት ውስጥ እንግዲህ በርካታ  ሀገራዊ የሆኑ ሙዚቃዎችን  ሰርቷል።»

 ሀገሬን አትንኳት ፣ ትዝ ባለኝ ጊዜ ፣ የከረመ ፍቅር

በርካቶች በተለያየዩ ምዕራፎች የተከፋፈሉትን የህይወት ምራፎቻቸውን መለስ ብለው ከሚመለከቱባቸው ዘመን ተሻጋሪ የሙዚቃ ስራዎች መካከል ጌታቸው ካሳ ያበረከታቸው  ቀዳሚ ተጠቃሾች ናቸው ።

 ጌታቸው ካሣ በበርካታ የሙዚቃ ወዳጆች እና አድናቂዎች ልብ ውስጥ ያስቀረውን አጋጣሚ የሚያስታውሱት ዳዊት በተለይ የትዝታ ዜማ ከሚዜምበት የተለመደ መንገድ ወጥቶ አዲስ ስልት ይዞ መቅረቡ የሙዚቃ ስራዎቹ ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል ፤ ይላሉ ።

«መጀመሪያ ጊዜ እርሱ የታወቀበት ትዝታ ድሮ በቫልት ብቻ የሚሰራ እና በዚያ ላይ ያተኮረ ነበር። ጌታቸው ግን ትዝታን በቫልት እና ፈጠን ባለ ሙዚቃ አሬንጅ በማድረግ በዚያ ላይ በጊታር ታጅቦ የሰራበት ነገር ጌታቸውን በሀገር አቀፍ ደረጃ ሊያሳውቀው በቅቷል። »

እውነት ጌታቸው የሙዚቃውን ኖታ እያነበበ ዓይኑን ጨፍኖ በመድረክ ላይ ሲቀነቅን ስሜቱ በቀላሉ ወደ ሌሎች እንደሚጋባ ብዙዎች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ ። ድምጻዊው ለሀገሩ ያለው ስሜት ከድምጻዊነት ባሻገር የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋችነቱ የጥምር ችሎታ ባለቤት ከሆኑ ጥቂት ድምጻውያን አንዱ እንደሚያደርገው ነው ዳዊት የሚናገሩት ። የትግርኛ ሙዚቃው ንጉስ ኪሮስ ዓለማየሁ ሲታወስ 

« ሀገሩን እንግዲህ በትጋት ያገለገለ ነው ፤ ምንም እንኳ ውጭ ሀገር ለረዥም ዘመንን ቢኖርም ዜግነቱን ሳይቀይር ኢትዮጵያዊነቱን ይዞ እስካሁን የዘለቀ ድምጻዊ ነው ። ጌታቸውን ለየት የሚያደርገው ደግሞ የሙዚቃ መሳሪያ መጫወት ይችላል፤ ድራም መጫወት ይችላል። ድራም እየተጫወተ ይዘፍናል። ዜማዎች ይደርሳል፤ ግጥሞችንም ይጽፋል፤ እና ስራዎቹን በሙሉ ደግሞ መድረክ ላይ ሲያቀርብ በስሜት ነው ፣ »

ጥቂት የማይባሉ ቀደምት እና አንጋፋ ሙዘቀኞች የመጨረሻዎቹን የህይወት ዘመናቸውን እነርሱን በማይመጥን ሁኔታ ውስጥ ሲያሳልፉ መሰማቱ እየተለመደ መምጣቱ ይነገራል። ጌታቸው ካሣም በተመሳሳይ መንገ,ድ ወደ ሆስፒታል ከመወሰዱ በፊት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደነበር ጠይቀን ተረድተናል።

ሙዚቀኛው ዳዊት ይፍሩም በዚሁ ሃሳብ ይስማማሉ ፤ ጌታቸው ስሙን እና ዝናውን የየሚመጥን ህይወት አሳልፏል ብዬ አልገምትም ይላሉ።

«ጌታቸው በሰራው እና ባለው ዝና ልክ ኖሯል ብዬ አልገምትም ፤ እርሱ ለኑሮ ያለው አመለካከት በጣም ቀለል ያለ ነው። በጣም መሽቀርቀርም አይፈልግም ፤ የሙዚቃ መብቶቹን ተጠቅሞ ቢሆን ኖሮ እንደሌሎቹ ኖሮ ያልፍ ነበር »የኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ በተስፋዬ ለማ

ከ50 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ የሙዚቃ እንዱስትሪ ውስጥ ገዝፎ የኖረው ድምጻዊ ህያው ሥራዎቹን ትቶ ላይመለስ ሄዷል፤ የቀብር ስነስረዓቱም የፊታችን ዓርብ የካቲት 15 ቀን 2016 ዓ,ም ሲፈጸም ፤ በዕለቱ አስቀድሞ ጠዋት ላይ በብሔራዊ ቴያትር ወዳጅ ዘመዶቹ ፣ የሙያ አጋሩቹ እና አድናቂዎቹ የአስክሬን ሽኝት እንደሚያደርጉለት ሙዚቀኛ ዳዊት ይፍሩ ነግረውናል፤ ዶይቼ ቬለም ለድምጻዊው ወዳጅ ዘመድ ፤ የሙያ አጋሮቹን ጓደኞቹ መጽናናትን ይመኛል።

ታምራት ዲንሳ 

ኂሩት መለሰ