1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ነጻ ሚዲያ የሚኖረው ሚና - ትኩረት እንዲሰጠው ተጠየቀ

ሐሙስ፣ መጋቢት 3 2018

ባሉት ወራቶች በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የተወሰዱት ተከታታይ እርምጃዎች በኢትዮጵያ የሚዲያ ነፃነት እና ጋዜጠኝነት ሞያ ላይ ከፍተኛ ጫና የታየበት ነበር ሲል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር ይፋ ባደረገዉ የዳሰሳ ዘገባ አስታወቀ። በሽብርተኝነት ወንጀል የተከሰሱት ጋዜጠኞች ጉዳይ ሌላዉ ርዕስም ነዉ።

https://p.dw.com/p/5AIcf
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር (EMMPA)
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር (EMMPA) ምስል፦ EMMPA

ነጻ ሚዲያ የሚኖረው ሚና ትኩረት እንዲሰጠው ተጠየቀ

ነጻ ሚዲያ የሚኖረው ሚና ትኩረት እንዲሰጠው ተጠየቀ

የካቲት 2018 በኢትዮጵያ የሚዲያ ነፃነት ላይ ከፍተኛ ተግዳሮት የታየበት ወር ሆኖ አልፏል ሲል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር (EMMPA) ትናንት የኢትዮጵያ የሚዲያ ሁኔታ ዘገባዉን ይፋ አደረገ። እንደ ማህበሩ ባለፉት ወራት በኢትዮጵያ ሚዲያዎች ላይ የታዩት እርምጃዎች ፤ ጠቅላላ ምርጫን ጨምሮ ሀገሪቱ ከፊት ካሉባት ወሳኝ ሁነቶች ቀደም ብለዉ የተወሰዱ ናቸዉ።  
ያለፈዉ የካቲት ወር እና ከዝያ ቀደም ብለዉ ባሉት ወራቶች በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን (EMA) የተወሰዱት  ተከታታይ  እርምጃዎች  በኢትዮጵያ የሚዲያ ነፃነት እና ጋዜጠኝነት ሞያ ላይ ከፍተኛ ጫና የታየበት ነበር ሲል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር (EMMPA) አስታዉቋል። በእርግጥ ማህበሩ በየወሩ በሚዲያ ላይ የታዩ አንኳር ጉዳዮችን እየለየ እና እየገመገመ ጠንካራ ስራዎችን እውቅና የሚሰጥበት የታዩ ስህተቶችን ደግሞ እየጠቆመ መፍትሄ እንዲያገኙ የሚጠይቅበት ወርሃዊ የሚዲያ ዳሰሳዉን በተለያዩ ምክንያቶች አቋርጦ እንደነበርም አስታዉቋል። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር፤ ባለፉት ወራቶች ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚሰሩ ነፃ ሚዲያዎች ፈቃድ መሰረዝ ፤ እና የዓለም አቀፍ ጋዜጠኞችን ዕውቅና የመነፈግ እርምጃ እንዳሳሰበዉ የገለጹት ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ  የማህበሩ ፀሐፊ አቶ ዳዊት አስታጥቄ ናቸዉ። 

«የካቲት 2018 በኢትዮጵያ የሚዲያ ነፃነት ላይ ከፍተኛ ተግዳሮት የታየበት ወር ሆኖ አልፏል።  ''ወሩ  ኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን (EMA) የተወሰዱ ተከታታይ  እርምጃዎች እና ሙያው ላይ ጫና የሚያሳድሩ እርምጃዎች የተወሰዱበት ሲሆን፣ የሀገር ውስጥ ሚዲያዎችን ፈቃድ ከመሰረዝ ባለፈ የዓለም አቀፍ ጋዜጠኞችን ዕውቅና እስከ መንፈግ የተደረሰበት ነበር። ርምጃው  ሀገሪቱ ከፊት ካሉባት ወሳኝ ሁነቶች ማለትም ከሀገራዊ  ምክክር እንዲሁም ግንቦት ወር ላይ ከሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ጥቂት ወራት ቀደም ብሎ የተወሰዱ እርምጃዎች መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡ በየካቲት ወር እና ከዚያ ቀደም  ባሉ ወራት አምስት የመገናኛ ብዙኃን ርምጃ ተወስኖባቸዋል። ወሩ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን (EMA) በተወሰዱ ተከታታይ  እርምጃዎች  የሀገር ውስጥ ሚዲያዎችን ፈቃድ ከመሰረዝ ባለፈ የዓለም አቀፍ ጋዜጠኞችን ዕውቅና እስከ መንፈግ ደርሷል።» 

አዲስ ስታንዳርድ ድረ-ገጽ
አዲስ ስታንዳርድ ድረ-ገጽምስል፦ Eshete Bekele/DW

ማህበሩ አንድን ሚዲያ ተሰርዘሃል ፤ የስራ ፈቃድህ አልታደሰም በሚል አንድን ሚዲያ የማገድ እርምጃ ለኢትዮጵያ የሚዲያ ምህዳር ችግርን የሚፈጥር በመሆኑ ይህ አይነቱ እርምጃ መቆም አለበት ብለን እናስባለን ሲል ማህበሩ ገልጿል።  ነፃ ሚዲያ ለታማኝ እና ግልፅ ለሆነ የምርጫ ሥርዓት  የጀርባ አጥንት ነው። እንደ ዋዜማ እና አዲስ ስታንዳርድ ያሉ ተቋማት የምዝገባ ፈቃድ አና የሥራ ፈቃድ መሰረዝ፣ የሃሳብ ልዩነቶች ተገቢው ቦታ ተሰጥቷቸው እንዳይስተናገዱ  እና  በሰኔ ወር በሚካሄደው ምርጫ ላይ የተለያዩ እይታዎች እንዳይኖሩ መራጩ ህዝብ መረጃን መሠረት ያደረገ ውሳኔ እንዳይወስን ዕድል ይነፍገዋል ሲል ማህበሩ ገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ ፤ እንደ ጀርመን ሬድዮ DW፤ ሮይተርስ እና አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ያሉ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ላይ ያነጣጠሩት ርምጃዎች እንዲሁ፤ ኢትዮጵያን ከዓለም አቀፉ የሚዲያ መድረክ ከማግለል ባለፈ፤ የህዝብን ብዝሃነት ያለው መረጃ የማግኘት መብትን መገደቡብ ማህበሩ ጠቁሟል።  የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ፈቃድን አለማደስ አልያም መሰረዝ ድርጊት ፤ የውጭ ሚዲያዎች በሀገር ውስጥ ጉዳዮች ላይ የሚሰጡትን ትችት እንደማይታገሥ የሚያሳይ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል ሲልም ማህበሩ ጽፏል። የኢትዮጵያመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን እንደ "ብሔራዊ ጥቅምን አደጋ ላይ መጣል" እና "የሚዲያ ሥነ-ምግባር" ጥሰት ብሎ  በደምሣሣው  ከማቅረብ ውጪ ግልጽ ያልሆኑ ድንጋጌዎችን መጠቀሙ የ2013ቱ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅን መንፈስ የሚቃረን መሆኑን ማህበሩ አስታዉቋል።

የዶቼ ቬሌ የድምፅ መቅረጫ
የዶቼ ቬሌ የድምፅ መቅረጫ ምስል፦ Achille Abboud/imago images

በሽብርተኝነት ወንጀል የተከሰሱት ጋዜጠኞች ጉዳይ

ሦስት ዓመታት እስር ላይ የሚገኙ በሽብርተኝነት ወንጀል የተከሰሱት ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው  ፣ጎበዜ ሲሳይ፣ መስከረም አበራ እና ገነት አስማማው  አስፈላጊው የሕግ ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ እና ፍትሐዊ፣ ግልጽ እና ሕጋዊ ሥርዓቱን የጠበቀ የፍርድ ሂደት ማግኘት እንዳለባቸው ብሎ እንደሚያምን ማህበሩ ባወጣዉ የሚዲያ ዳሰሳ ዘገባ ይፋ ሌላዉ ጉዳይ ነዉ።  

«በሽብርተኝነት ወንጀል የተከሰሱት ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው  ፣ጎበዜ ሲሳይ፣ መስከረም አበራ እና ገነት አስማማው  አስፈላጊው የሕግ ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ እና ፍትሐዊ፣ ግልጽ እና ሕጋዊ ሥርዓቱን የጠበቀ የፍርድ ሂደት ማግኘት እንዳለባቸው እናምናለን። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዓቃቤ ህግ ያቀረበው ማስረጃ ጋዜጠኞቹን በሽብርተኛነት የሚያስከስስ ነው ብሎ በመወሰኑ የፊታችን ግንቦት ወር መከላከያ እንዲያቀርቡ ቀጠሮ ተይዟል፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታት ገደማ በእስር መቆየታቸው እና የቀረበባቸው ክስ ክብደት በኢትዮጵያ ያለውን የፕሬስ ነፃነትን አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ፍትህ እንዲያገኙ እንጠይቃለን ።»

ፎቶ ከማህደር፤ የፍትህ ምልክት
ፎቶ ከማህደር፤ የፍትህ ምልክት ምስል፦ Udo Herrmann/CHROMORANGE/picture alliance

ባለፈዉ ሳምንት የኢንተርናሽናል ሚድያ ሰፖርት( አይ ኤም ኤስ ) የጋዜጠኞች ደህንነት የግምገማ አስመልክቶ በአዲስ አበባ ይፋ ያደረገው ጥናት እንደምያሳየዉ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት 2025 ብቻ በኢትዮጵያ 44 ጋዜጠኞች ላይ እስርና አፈናመፈጸውን አስነብቧል። ይህ አሳሳቢና የፕሬስ ነፃነትን አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን ሁሉም ሊገነዘብ እንደሚገባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር አፅንኦት ሰቷል። ከዚህ ሌላ ማህበሩ የተሻለ ሃገር እና ማህበረሰብ ለመገንባት ነጻ ሚዲያ የሚኖረው ሚና ትኩረት እንዲሰጠው አጥብቆ  ጠይቋል።

አዜብ ታደሰ

ዮሃንስ ገብረግዚአብሔር