1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትግራይ ክልል ሴቶች ላይ የሚፈፀም ፆታዊ ጥቃት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ማክሰኞ፣ ኅዳር 17 2017

በትግራይ ክልል በሴቶች ላይ የሚፈፀም ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለፀ ። የትግራይ ክልል ሴቶች ማሕበር በአንድ ዓመት 783 ሴቶች ላይ የፆታ ጥቃት ተፈጽሞ 44 ሴቶች በግፍ ተገድለዋል ተብሏል ። የመብት ተቋማት እና የተጎጂ ቤተሰቦች በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች በተለየ ፍርድ ቤት እንዲታዩ መንግስትን ጠይቀዋል።

https://p.dw.com/p/4nRgy
Äthiopien Tigray | Studie zu geschlechtsspezifischer Gewalt
ምስል Million Hailesilassie/DW

83 ሴቶች ላይ የፆታ ጥቃት ተፈጽሞ 44 ሴቶች ተገድለዋል 24ቱ በባሎቻቸው ነው

በትግራይ ክልል በሴቶች ላይ የሚፈፀም ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለፀ ። የትግራይ ክልል ሴቶች ማሕበር በአንድ ዓመት 783 ሴቶች ላይ የፆታ ጥቃት ተፈጽሞ 44 ሴቶች በግፍ ተገድለዋል ተብሏል።  ከነዚህ መካከል ደግሞ 24ቱ በባሎቻቸው የተገደሉ መሆኑ ተመልክቷል ። በትግራይ ክልል በሴቶች መብት ዙርያ የሚሠሩ ተቋማት እና የተጎጂ ቤተሰቦች በክልሉ  በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች  በተለየ ፍርድ ቤት እንዲታዩ መንግስትን ጠይቀዋል።

የትግራይ ክልል ሴቶች ማሕበር ያካሄደው እና በቅርቡ ይፋ ያደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው፥ በአንድ አመት ግዜ ውስጥ በክልሉ 783 ፆታ መሰረት ያደረጉ በሴቶች ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች መመዝገባቸው የሚያመለክት ሲሆን፥ ከእነዚህ መካከል 44ቱ በሴቶች ግፍ የተፈፀሙ ግድያዎች ናቸው ብሏል። ከእነዚህ ግድያዎች ደግሞ 24ቱ የተፈፀሙት ባሎች በሚስቶቻቸው ላይ መሆኑ ተጠቅሷል። ለእነዚህ ግድያዎች እና ሌሎች ፆታዊ ጥቃቶች ፍትህ ማጣት ደግሞ በተበዳይ ቤተሰቦች ላይ እና በአጠቃላይ ማሕበረሰቡ ቁጣን የፈጠረ ነው። ባለፈው ጥቅምት ወር መጀመርያ በትግራይ ክልል ዉቅሮ ከተማ ተሞሽራ በሶስተኛ ቀን በተጠርጣሪ ባለቤትዋ የተገደለችው ሊድያ አለም ወላጅ አባት አቶ አለም ካሕሳይ የልጃቸው ሞት ከፍተኛ ሐዘን ውስጥ ከቷቸዋል።

«ተበድያለሁ፣ ተጎድቻለሁ፣ እንደ አባት እንደ ወንድ ሰው ማፅናናት ሲገባኝ አልቻልኩም ፣ ፍፁም አልቻልኩም» ይላሉ የሟች አባት አቶ አለም ። በሴቶች ላይ የተፈፀሙ ጥቃቶች በተለየ ችሎች እንዲታይም በተጎጂ ቤተሰቦች ጥያቄ ቀርቧል። የትግራይ ሴቶች ማሕበር እንደሚለው ለሚፈፀሙ ጥቃቶች ፍትህ አለመስጠት ወንጀሎች እንዲበራከቱ በር ከፍቷል።

የትግራይ ሴቶች ማሕበር ሥራ አስከያጅ ወይዘሮ አበባ ኃይለሥላሴ"ከእነዚህ 44 በግፍ የተገደሉ መካከል ፍትህ ያገኙ ስንት ናቸው ብለን ስንመለከት 6 ብቻ ናቸው። አንድ በመቐለ ባለፈው ሐሙስ ብይን ተሰጥቷታል። ከ12 ተመሳሳይ ጉዳዮች ነው አንዲት ብቻ መጨረሻ ያገኘችው። በሰሜን ምዕራብም እንዲሁ ከአስር መካከል፥ ሁለት ጉዳዮች መጨረሻ ደርሰዋል። ፍርዱ አጥጋቢ ይሁን አይደለም ሌላ ጉዳይ ሆኖ" ብለዋል።

 በሴቶች ላይ የሚደርስ በደል እንዲቆም በትግራይ ክልል ሰላማዊ ሰልፍ ። ፎቶ፦ ከማኅደር
በሴቶች ላይ የሚደርስ በደል እንዲቆም በትግራይ ክልል ሰላማዊ ሰልፍ ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Million Hailesilassie/DW

የጥቃቱ ሰለባ ቤተሰቦች፣ የትግራይ ሴቶች ማሕበር እና ይኾኖ የተሰኘ በፆታ ጥቃት መከላከል ዙርያ የሚሰራ ተቋማ፥ በዚህ አንገብጋቢ አጀንዳ ዙርያ ባዘጋጁት መድረክ የተናገረችው የይኮኖ ስራ አስከያጅ ፅዴና አባዲ፥ የተበራከቱት የፆታ ጥቃቶች በሁሉም የማሕበረሰብ ክፍል ላይ ስጋት ፈጥሯል ትላለች።

ፀዴና  "ከተገደለችው ሴት ጀርባ ያለው ሰው ለፍትህ መንግስት መወትወት አለበት። አንዲት ሴት ልጅ ተገደለች ማለት ጉዳቱ የበርካቶች ነው። ቤተሰቦችዋ፣ አካባቢዋ ጨምሮ ሁላችን ነው ፍርሃት እና ስጋት ውስጥ እየኖርን ነው" ብላለች።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለመከላከል እና አጥፊዎችን ለመቅጣት እየጣረ መሆኑን ገልጧል። የትግራይ ፍትህ ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አዲሱ ገብረሥላሴ፥ ፍትህን ለማረጋገጥ መንግስት ጥረት ላይ ነው ብለዋል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ፀሐይ ጫኔ