1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትኩረት በአፍሪቃ፣ የደቡብ አፍሪቃ 30 ዓመት ዴሞክራሲ፣ ጎርፍ በአፍሪቃ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 19 2016

የሕዝቡ ምጣኔ ሐብታዊና ማሕበራዊ ፍላጎቶች በመጓደላቸዉ በገዢዉ የANC ፓርቲና በባለስልጣናቱ ላይ ያለዉ ቅሬታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለ ነዉ።የምጣኔ ሐብት ተንታኝ ዳንኤል ሲልከ እንደሚሉት ANC ዕዉቁ መሪዉ ኔልሰን ማንዴላ ገቢር ያደረጉትን የሥነ-ምግባር ሥርዓት አለማክበሩ የሐገሪቱን ሕዝብ ክፉኛ አበሳጭቷል።

https://p.dw.com/p/4fEuI
በ1994 ሚያዚያ 27 በተደረገዉ ምርጫ ያሸነፉት የኔልሰን ማንዴላ በዓለ ሲመት ሲከበር ከተገኘዉ ሕዝብ በከፊል
ደቡብ አፍሪቃ 1994 (እግአ) ተስፋ ያደረገዉ ሕዝብ የአዳዲስ መሪዎቹን በዓለ ሲመት በደስታ ሲከታተልምስል Hanner Frankenfeld/AFP/Getty Images

ትኩረት በአፍሪቃ፣ የደቡብ አፍሪቃ 30 ዓመት ዴሞክራሲ፣ ጎርፍ በአፍሪቃ

የዛሬዉ ትኩረት በአፍሪቃ ሁለት ርዕሶችን ይቃኛል።ደቡብ አፍሪቃ የመጀመሪያዉን ብዝሐ-ዘር ምርጫ ያደረገችበት ሰላሳኛ ዓመት ቀዳሚዉ ሲሆን፣ ሁለተኛዉ የምሥራቅና የምዕራብ አፍሪቃ ሐገራትን ያጥለቀለቀዉ ጎርፍ ያደረሰዉን ጉዳት የሚመቃኝ ነዉ።

ደቡብ አፍሪቃ የመጀመሪያዉን የብዝሐ-ዘር ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ካስተናገደች ዛሬ 30 ዓመት ደፈነች።ምርጫዉ ለዘመናት የፀናዉ የጥቂት ነጮች  የዘር መድሎ ሥርዓት በይፋ የተወገድበት፣ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ድምፁን የሰጠበት፣ከፍተኛ ተስፋ፣ ብሩሕ መፃኤ ዘመን ያማተረበትም ነበር።ምርጫዉ የዘር መድሎ ሥርዓትን ለማስወገድ ሲታገል የነበረዉ የደቡብ አፍሪቃዉያን የአፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት (ANC)ን ለድል አብቅቶ፣ ለ27 ዓመታት በእስር የማቀቁትን  ዕዉቁን የእኩልነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ የፕሬዝደንትነቱን ሥልጣን ሲይዙ ተስፋ የቋጠረዉ ሕዝብ በደስታ ፌስታ ቦርቆ ነበር።
                                          
የአንድነት፣ የሐገር ግንባታ ቃልም ናኘ።«ቁስሉ የሚሽርበት ጊዜ መጥቷል።የሚከፋፍለንን ልዩነት የሚያስወግድ ድልድይ የምንገነባበት ጊዜ አሁን ነዉ።የመገንባቱ ኃላፊነት የኛ ነዉ።»
ይሕ የአንድነት ጥሪ፣ ይሕ የዕኩልነት መልዕክት፣ ይሕ የበጎ ተስፋ በጎ ቃል ያኔ ከፕሪቶሪያ ሲንቆረቆረ፣ ድፍን ደቡብ አፍሪቃ በተስፋ፣ደስታ፣ሆታ ጨፍራ ስትቀልጥ ያኔ ከዚያዉ ከፕሪቶሪያ ዘግቤ ጊዜዉ ይሮጣል።ሰዉም ያልፋል።

ዛሬ ኔልሰን ማንዴላ የሉም።የነማንዴላን ርዕይ ከግብ ለማድረስ የተባበሩ፣ በዓለ ሲመታቸዉን ያደመቁ፣ ያደነቁት ኤፍ ዳብሊዉ ዴክላርክ፣ ዴዝሞንድ ቱቱ፣ ፊደል ካስትሮ፣ያሲር አረፋት፣ ቤናዚር ቡቶ፣ ልዕልት ዳያና፣ ሮበርት ሙጋቤ፣ መለስ ዜናዊና ሌሎችም የሉም።የማንዴላዉ የደቡብ አፍሪቃ የአፍሪቃ ብሔራዊ ምክር ቤት (ANC) ግን ዛሬም ሥልጣን ላይ ነዉ።ቀስተደመናዊቱ ሐገርም በነፃነቷ እንደኮራች አለች።የበጎ ተስፋ ቁንጮይቱ (Cape of Good Hope) ሐገር ሕዝብ የያኔ ተስፋ ግን ደብዘዝ፣ ምጣኔ ሐብቱ ቀሰስ፣ደንቀፍቀፍ፣ የደሐ-ሐብታሞች ልዩነት ቦርቀቅ ማለቱ እንጂ ቀቢፀ ተስፋዉ።

እመርታ ግን የወረቀት

ግን ብዙ ለዉጥ አለ።እርግጥ ነዉ አንዳዶች «የወረቀት ላይ እመርታ» ቢሉትም የቅይጦቹ ሐገር ታላላቅ ለዉጦችን አድርጋለች።ርዕሰ መንበሩን ጆሐንስበርግ ያደረገዉ የሮዛ-ላክሰመንበርግ መታሰቢያ ጥናት ተቋም የበላይ ኃላፊ ፍሬድሰን ጉይሉንጉ እንደሚሉት ደግሞ ደቡብ አፍሪቃ የመገናኛ ዘዴዎች፣ የሙያ፣የፆታና የማሕበረሰብ ማሕበራትን መብትን አስከብራለች።አንዳዶቹ ለዉጦች ለድፍን አለም አብነታዊ ናቸዉ።
«እንደ LGBTQ ያሉ አናሳዎችን ጨምሮ ለሐገሪቱ ሕዝብ መሰረታዊ ጠቃሚ መብቶችን ያጎናፀፈና የሚያስከብር በዓለም ካሉ በጣም ዘመናይ ሕገ መንግስታት አንዱ የሆነ ሐገ መንስት አላት። ገለልተኛና፣ በጣም ዉጤማ የሕግ ሥርዓት አላት።የደቡብ አፍሪቃ ፍርድ ቤቶች ሥራ ዉጤማና ገለልተኛ ነዉ።ይሕ ደግሞ ሙስናን የመሳሰሉ ጥፋቶችን ለመዋጋት በጣም ጠቃሚ ነዉ።ደቡብ አፍሪቃ ትምሕርት፣ መኖሪያ ቤት፣ዉኃ፣ መብራት የመሳሰሉ አቅርቦቶችን ለሕዝቧ እያዳረስች ነዉ።»

የመጀመሪያዉ የደቡብ አፍሪቃ ጥቁር ፕሬዝደንት ኔልሰን ማንዴላ (ከመሐል) በ1994
ከፊት ከግራ ወደ ቀኝ ምክትል ፕሬዝደንት ታቦ ኢምቤኪ፣ ፕሬዝደንት ኔልሰን ማንዴላና ሌለኛዉ ምክትል ፕሬዝደንት ኤፍ ዳብሊዉ ዴክላርክ ምስል Alexander Joe/AFP/Getty Images

የሙስና መስፋፋት

ደቡብ አፍሪቃ ከዚሕም በተጨማሪ ባለፉት 30 ዓመታት በጣም ንቁ፣ፈጥኖ ደራሽ፣ በቅጡ የደረጀና ለየቆመለትt መብት በርትቶ የሚታገል የሲቢል ማሕበረሰብ ገንብታለች።ይሁንና የገዢዉ ፓርቲ የANC ባለስልጣናት በተደጋጋሚ የሥልጣን ሽኩቻ መግጠማቸዉና አንዳዶቹ በሙስና መዘፈቃቸዉ ብዙ እያነጋገረ ነዉ።ሥራ አጥነት፣ወንጀል፣ ድሕነትና የኑሮ ዉድነት ያቺ ዉብ፣ሐብታም የቅይጦች ምድር ያስመዘገበችዉን ድል እያደበዘዘባት ነዉ።ጉሌይንጉ እንደሚሉት ዕድሜያቸዉ ከ34 ዓመት በታች ከሆኑ ከየሁለቱ ወጣቶች አንዱ ሥራ አጥ ነዉ።
አብዛኛዉ ደቡብ አፍሪቃዊ ንፁሕ የመጠጥ ዉኃና የኤሌክትሪክ ኃይል ያገኛል።ይሁንና የሐገሪቱ መንግስት በሚቆጣጠረዉ የኃል አቅራቢ ድርጅት ዉስጥ የተሰገሰጉ ሰራተኞች በሚያደርሱት ሻጥር ምክንያት ዉኃና መብራት በየጊዜዉ ይቆራረጣል።

በፖለቲካና ፖለቲከኞች ላይ ያለዉ ቅሬታ

የሕዝቡ ምጣኔ ሐብታዊና ማሕበራዊ ፍላጎቶች በመጓደላቸዉ በገዢዉ የANC ፓርቲና በባለስልጣናቱ ላይ ያለዉ ቅሬታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለ ነዉ።የምጣኔ ሐብት ተንታኝ ዳንኤል ሲልከ እንደሚሉት ANC ዕዉቁ መሪዉ ኔልሰን ማንዴላ ገቢር ያደረጉትን የሥነ-ምግባር ሥርዓት አለማክበሩ የሐገሪቱን ሕዝብ ክፉኛ አበሳጭቷል።

«የነፃነት ተፋላሚዉ ፓርቲ ANC በተለይ ኔልሰን ማንዴላ የደነገጉትን የሥነ ምግባር ሥርዓት አለመከተሉ በሕዝቡ ዘንድ ጥልቅ ቅሬታና ቁጣ አስከትሏል።እነዚሕ የሥነ ምግባር ደረጃዎች ባለፉት 20 በተለይም ባለፈዉ 10 እና 15 ዓመት መጣሳቸዉ በደቡብ አፍሪቃዉያን ሥነልቡና ላይ ከፍተኛ ድብርት፣ቀዉስና የሞራል መላሸቅ አስከትሏል።» 
በመጪዉ ግንቦት በሚደረገዉ ምርጫ ፕሬዝደንት ሲሪያል ራማፎዛ የሚመሩት ANC ካጠቃላዩ ድምፅ ሐምሳ ከመቶ እንኳን ማግኘቱ እያጠራጠረ ነዉ።የምርጫዉ ዉጤት አሁን እንደሚገመተዉ ከሆነ ላለፉት 30 ዓመታት ደቡብ አፍሪቃን በብቸኝነት የመራዉ ANC ከተቃዋሚዎቹ ጋር ተጣማሪ መንግስት ለመመሥረት ይገደዳል።

የጄኮብ ዙማ ዘመን ድቀት

ደቡብ አፍሪቃ ከ190ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ያስመዘገበችዉ ታላቅ ለዉጥ ክፉኛ ያሽቆለቆለዉ፣ ብዙዎች እንደሚያምኑት ፕሬዝደንት ጄኮብ ዙማ ሐገሪቱን በመሩበት እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ከ2009 እስከ 2018 በነበረዉ ጊዜ ነዉ።ዙማ እዚያዉ ANC ዉስጥና ከፓርቲዉ ዉጪ ባሉ ታማኞቻቸዉ አማካይነት የሐገሪቱን መንግስት  መዝብረዋል ይባላል።መንግስት ከኩባንዮች ጋር የሚያደርጋቸዉ ዉሎች፣ ኮንትራቶች፣ የዕቃ ግዢዎች በሙሉ የሚፈፀሙት ለዙማና ለቅርብ ታማኝ ባለስልጣኖቻቸዉ ጠቀም ያለ ዶላር ከሚያስታቅፉት ጋር ነበር።እንዲሕ ዓይነቱ ሙስና፣ ዋልጊነትና የመጠቃቀም ሥርዓት የኤኮኖሚ ባለሙያዉ ሲልከ እንደሚሉት የሐገሪቱን ምጣኔ ሐብት ከማክሰሩ በተጨማሪ ለፖለቲከኞችና ለመንግስት ሠራተኞች ንቅዘትን አስተምሯል።
አመርቃዡ የዘመነ-አፓርታይድ ቁስል
ይሁንና ደቡብ አፍሪቃ አሁን ያጋጠማትን ፈተና ጠለቅ አድርገዉ የሚያስተነትኑ ወገኖች ችግሮቹ ሁሉ በዙማ ወይም በANC ያገዛዝ ዘመን የተከሰቱ ብቻ ናቸዉ ብለዉ አያምኑም።የኔልሰን ማንዴላ መታሰቢያ ማዕከል ኃላፊ ቬርን ሐሪስ እንደሚሉት ለዘመናት የፀናዉ የዘር መድሎ ሥርዓት ያደረሰዉ ጫናና መቋሰል እስከዛሬ ለቀጠለዉ ችግር መሠረት ነዉ።አስከፊዉ አገዛዝ ያሰረፀዉ አሰራር፣መንፈስና አስተሳሰብ ሐሪስ እንደሚሉት እንደዘበት መረሳት የለበትም።
«አሁን የሚያጋጥሙን ብዙዎቹ ችግሮች ያኔ በደረሰዉ ቁስል ሥር የሰደዱ ናቸዉ።የማሕበረሰባችን ድር በዚያ ሥርዓት ዘመን ተበጣጥሷል።የሕብረተሰባችንን ቁስል ለማዳን፣የተበጣጠሰዉን ድር ለመቀጠል፣ ዴሞክራሲን ለማፅናት ረጅም ጊዜ እንደሚፈጅብን እናዉቅ ነበር።ነገር ግን ሁሉንም ረሳነዉና ሁሉንም ባጭር ጊዜ ዉስጥ መጠገን የምንችል መሰለን።እንደሚመስለኝ ይሕ አልጠቀመንም።»

የበጎ ተስፋ ቁንጮ

ደቡብ አፍሪቃ ሐገር ዉስጥ ካሳየቸዉ ጥሩ-መጥፎ ለዉጥ ጋር በዓለም አቀፍ መድረክ  ጭቆናን ግፍና በደልን የምትቃወም ሐገር መሆንዋን እያስመሰከረች ነዉ።ጉይሌንጉ እንደሚሉት ለብዙ ዘመናት በዘር መድሎ ሥርዓት ግፍ የማቀቀችዉ ሐገር የግፉአን ተሟጋች መሆኗ አይበዛባትም።የኢትዮጵያን ጨምሮ አፍሪቃ ዉስጥ የሚነሱ ግጭቶችን ለማስወገድ ሸምጋይም፣አግባቢም፣ ሰላም አስከባሪ ሠራዊት አዝማች፣ ገንዘብ ለጋሽም ናት።እስራኤል በፍልስጤም ሕዝብ ላይ የምትፈፅመዉን ግፍ ለማስቆምና ላደረሰችዉ ጥፋት እንድትጠይቅ ደቡብ አፍሪቃ በዓለም ፍርድ ቤት ክስ በመመስረት በዓለም የመጀመሪያዋ ሐገርም ሆናለች።ክሱ ባለፈዉ ታሕሳስ መደመጥ ከጀመረ ወዲሕ የበጎ ተስፋይቱ ሐገር የዓለም ርዕሥ እንደሆነች ነዉ።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሥራና አሰራር እንዲለወጥ፣ የቅኝ ገዢና ተገዢ ስርዓትን የሚከተለዉ የአፍሪቃና የምዕራባዉያን ግንኙነት እንዲቀየርም የቅይጦቹ ምድር እየታተረች ነዉ።

ራማፎዛ የሚመሩት ANC በመጪዉ ግንቦት በሚደረገዉ ምርጫ 50 ከመቶ ድምፅ ማግኘቱ ብዙ አጠራጥሯል
እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ከ2018 ጀምሮ ደቡብ አፍሪቃን በፕሬዝደንት የሚመሩት ሲሪየል ራማፎዛምስል Reuters/M. Hutchings

ጎርፍ በአፍሪቃ 

ፊሊፒንስ፣ ታይላድ፣ ባንግላዴሽና ሕንድን የመሳሰሉ የእስያ ሐገራትን የሚጠብሰዉ ከፍተኛ ሙቀት የሰዉ ነብስ ሲያጣፋ፣ ለወትሮዉ ሙቀት-ወበቅ ሐሩራቸዉ የሚናደፈዉ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችና ኦማንን የመሳሰሉ የመካከለኛዉ ምስራቅ ሐገራት የሚናፍቁት ዉኃ አለቅጥ ወርዶባቸዉ ተጥለቅልቀዋል።አፍሪቃ ምሥራቅና ምዕራብ ጠረፏ ላይ ጎርፍ ሲሞላዉ፣ የሰሐራ በረሐ የሚገርበት መሐል ግዛትዋ ነፋስ ሲገልበዉ ሰንብቷል።

ኃይለኛዉ ነፋስ ከሰሐረ በረሐ እየሰቀቀሰቀ ወደ ሰሜን ምዕራብ የሚያጓጉዘዉ አሸዋና አዋራ ቱርክና ግሪክ ከተሞች ላይ እየተሞጀረ ከተሞቹን ወይባማ ቀለም አልብሷቸዋል።ዝብርቅርቁ የተፈጥሮ ክስተት ለአማኞች የፈጣሪ ቁጣ ነዉ።ለአጥኚዎች የአየር ንብረት መዛባት፣ በጣሙን ደግሞ ኤል ኒኞ ነዉ።አምና  ጎርፍ 300 ሰዎች ከገደለባቸዉ  የአፍሪቃ ቀንድ ሐገራት ዘንድሮ እስካሁን ኢትዮጵያን ዘንግቷታል።በዚሁ ቢዘልቅ።ሶማሊያንም  ብዙ አልጨከነባትም።እስከ ትናንት 4 ሰዉ ሲሞት፣ 800 መፈናቀሉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታዉቋል።

ኬንያ መንገዶች ወንዝ መሰሉባት

ኬንያን ግን ጎርፍ ዘንድሮም አልማራትም። እንዲያዉም ብሷል።ባለፉት ተከታታይ ቀናት የጣለዉ ዝናብ ያስከተለዉ ጎርፍ  የርዕሰ ከተማ ናይሮቢን አዉራ መንገዶች ወደ ደራሽ ወንዝነት፣ ጉድባ፣ ጉርጎርጓዶችዋን  ወደ ኩሬነት ቀይሯቸዋል።
የኬንያ ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት ካለፈዉ መጋቢት እስከ ዛሬ ድረስ ጎርፍ ከ70 በላይ ሰዎች ወስዷል።በ10 ሺሕ የሚቆጠር አፈናቅሏል።ባለሥልጣናቱ ወደ ሐይቲ ሊያዘምቱ ያዘጋጁትን ፖሊስ ጭምር የአደጋ ሰለቦችን እዲያድን ለማዝመት ተገድደዋል።በጎርፍ ከተጥለቀለቁት አካባቢዎች አንዱ የማቻኮ ወረዳ አገረገዢ ትናንት እንዳስታወቁት አደጋዉ ለብሔራዊ ደሕንነት ሥጋት ነዉ።
«የማቻኮ ወረዳ የአደጋ መከላከያ ኮሚቴን አደራጅተናል።ኮሚቴዉ ብሔራዊ መንግስትን፣የፀጥታ አስከባሪ ተቋማትን፣ቀይ መስቀልን እያስተባበረ ነዉ።ከፖሊስ፣ከባሕር ኃይል፣ከሁሉም ወገኖች ጋር ተባብረን እየሰራን ነዉ።ምክንያቱም አደጋዉ የብሔራዊ ደሕንነት ጉዳይ ነዉ።»

ኬንያን ባጥለቀለቀዉ ጎርፍ ካለፈዉ መጋቢት ወዲሕ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ70 በልጧል
የኬንያ ርዕሠ ከተማ ናይሮቢን ያጥለቀለቀዉ ጎርፍ የከተማይቱን አዉራ መንገዶች ዘግቶ እንቅስቃሴዋን አዉኳልምስል Gerald Anderson/Anadolu/picture alliance

ታንዛኒያና ብሩንዲ

ታንዛኒያ ዉስጥ ጎርፍ ያደረሰዉ ጉዳት ከኬንያም የከፋ ነዉ።የሐገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ቃሲም ማጃሊዋ ትናንት እንዳስታወቁት ጎርፍ ታንዛኒያ ዉስጥ 155 ሠዎች ገድሏል።ከ200 ሺሕ የሚበልጥ ሕዝብ አንድም አፈናቅሏል አለያም ሐብት ንብረቱ ወድሞበታል።ብሩንዲ ካለፈዉ መስከረም ጀምሮ በግጭትም፣ በምግብ እጥረትም ከ200 ሺሕ በላይ ህዝብ ተፈናቅሎባታል።ሚያዚያ ከገባ ጀምሮ የጣለዉ ከባድ ዝናብ ደግሞ ወደ አንድ መቶ ሺሕ የሚጠጋ ሕዝብ አፈናቅሏል።በብሩንዲ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተጠሪ ቫዮሌት ኬንያና ካክዮምያ እንደሚሉት ጎርፉ የተፈናቃዩን ቁጥር በ25 ከመቶ አሳድጎታል።

የታንዛኒያ ጠቅላይ ሚንስትር እንዳሉት ጎርፉ 155 ሰዎች ገድሏል።ከ200 ሺሕ በላይ ጎድቷል።
ታናዛኒያን ያጥለቀለቀዉ ጎርፍ በርካታ አካባቢዎችንና ሰብሎችን ከጥቅም ዉጪ አድርጓልምስል Emmanuel Herman/Xinhua/picture alliance

 «ከመስከረም እስከ ሚያዚያ 7 ድረስ 203 ሺሕ 944 ሕዝብ ጉዳት እንደደረሰበት የሐገር ዉስጥ ተፈናቃዮች መከታተያ መስሪያ ቤት አስታዉቋል።19 ሺሕ 250 ቤቶች፣ 209 መማሪያ ክፍሎች ወድመዋል።አሁን የሐገር ዉስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር በ25 ከመቶ ጨምሯል።98 ሺሕ ህዝብ ተፈናቅሏል።»

ናጄሪያ፣ የእስረኞች ሲሳይ

ከምዕራብ አፍሪቃ በተለይ ማዕከላዊ ናጄሪያን ያጥለቀለዉ ጎርፍ ወሕኒ ለወረዱ ወንጀለኖች ወይም ተጠርጣሪዎች ሲሳይ ብጤ ነዉ የሆነዉ።ባለስልጣናት እንዳሉት ርዕሰ ከተማ አቡጃና አካባቢዉ ላይ ባለፈዉ ሐሙስ ለግማሽ ቀን የጣለዉ ዝናብ አካባቢዉን በጎርፍ ሲያጥለቀልቀዉ ሱሌጃ በተባለች ከተማ ወሕኒ ቤት ታስረዉ የነበሩ 120 እስረኞች በዉኃ የተሞላ እስር ቤታቸዉን ጥለዉ እልም።

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ