በጎንደር ፍንዳታ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 3 ደረሰ
ቅዳሜ፣ የካቲት 19 2014
በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ አዘዞ በተባለው ክፍለ ከተማ ትናንት በአንድ ፖሊስ ጣቢያ በደረሰ ፍንዳታ ሶስት ሰዎች መገደላቸውን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ። የጎንደር ከተማ አስተዳደር የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳንኤል ውበት ለዶይቼ ቬለ በስልክ እንደተናገሩት ትናንት ከሰዓት በኋላ አንድ ጭልጋ ከተባለ አካበቢ መነሻውን ያደረገ ተሸከርካሪ ወደ አዘዞ 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ ለፍተሻ በተወሰደ ጊዜ ከመኪናው ውስጥ በተከሰተ ፍንዳታ በፖሊስ ጣቢያው በነበሩ የፖሊስ አባላት በሁለቱ ላይ የሞትና በሰባቱ ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሷል። በቦታው የነበሩ ለሎች ሁለት ሲቪሎች ደግሞ ቆስለዋል ብለዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊው ዛሬ ለዶይቼ ቬሌ በሰጡት ተጨማሪ መረጃ ከቆሰሉት ሲቪሎች መካከል አንድ የአዘዞ ጠዳ ክፍለ ከተማ አመራር የነበሩ ግለሰብ ህይወት ማለፉን አረጋግጠዋል።
በወቅቱ በስፍራው ከነበሩ የፖሊስ አባላት መካከል ከአደጋው ለጥቂት የተረፈች አንድ የፖሊስ አባል እንዳለችው ፖሊሶች በፍተሸላይ እንዳሉ በተፈጠረ ፍንዳታ ሁለት ሰዎች ወዲያውኑ ሲሞቱ ተመልክታለች።
በሁኔታው በመደናገጥ ለደቂቃዎች መሬት ላይ ወድቃ እንደነበረና ከዚያ በኋላ የእርዳታ ጥሪ ማድረጓን የፖሊስ አባሏ ለዶይቼ ቬሌ ተናግራለች።
ሌላው በአካባቢው የነበሩ የዓይን እማኝ መረጃ ለመያዝ ለፍተሻ የመጣውን መኪናው በካሜራ ሲቀርፅ የነበረ ግለሰብ በፍንዳታው ሲወድቅ ማየታቸውንና በአካባቢው የነበረ ሰው ተደናግጦ መበታተኑን ተናግረዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ስለሁኔታው እንዲያስረዱን በስልክ ብንጠይቅም በራሳቸው ምክንያት ፈቃደኛ አልሆኑም።
ጉዳዩ በፖሊስ እየተጣራ በመሆኑ ተጨማሪ መረጃ ለመስጠት እንደማይችሉ የጎንደር ከተማ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ተናግረዋል።
የቆሰሉ የፖሊስ አባላትና አንድ ሲቪል በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው እንደሆነ ታውቋል። ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግሁት ጥረት አልተሳካም።
በአማራ ክልል ሰፊ የሆነ የህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ልውውጥ መኖሩን የየአካባቢ ፖሊሶች በየጊዜው ለአከባቢያቸው የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳይ መስሪያ ቤቶች የሚሰጡት መግለጫ ያሳያል።
ዓለምነው መኮንን
እሸቴ በቀለ