1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ግማሽ ሚሊየን የጉልበት ሠራተኛ ይፈለጋል ተባለ

ዓለምነው መኮንን
ረቡዕ፣ መስከረም 22 2017

በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ግማሽ ሚሊየን የጉልበት ሠራተኛ ይፈለጋል ተባለ ። ከፍተኛ ምርት የሚመረትበት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ አካባቢ በዚህ ዓመት በነበረው ከፍተኛ ዝናብና ተያያዥ ችግሮች ምክንያት ምርት ከለፈው ዓመት ከነበረው በ1/3ኛ፣ በዓመቱ ካቀደው ደግሞ በግማሽ ያክል ሊቀንስ እንደሚችል ተገልጧል ።

https://p.dw.com/p/4lL9T
Äthiopien Wolkait Tegede
ምስል Alemenew Mekonne/DW

ግማሽ ሚሊዮን የጉልበት ሠራተኛ ይፈለጋል

በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ግማሽ ሚሊየን የጉልበት ሠራተኛ ይፈለጋል ተባለ ። ከፍተኛ ምርት የሚመረትበት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ አካባቢ በዚህ ዓመት በነበረው ከፍተኛ ዝናብና ተያያዥ ችግሮች ምክንያት ምርት ከለፈው ዓመት ከነበረው በ1/3ኛ፣ በዓመቱ ካቀደው ደግሞ በግማሽ ያክል ሊቀንስ እንደሚችል ተገልጧል ።

ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ  ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ ጥጥና ሌሎች በገበያ ተፈላጊ የሆኑ የቅባት እህሎችን በስፋት ከሚያመርቱ የአገሪቱ አካባቢዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ በዚህ ዓመትም በአስተዳደሩ ስር በሚገኙ ወረዳዎች በ560ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ ሰሊጥ፣ ጥጥ፣ ማሽላ፣ ማሾና ሌሎች ሰብሎች ተዘርተው አንዳንዶቹ በመሰብሰብ ላይ ናቸው፡፡ ምርቱን ለመሰብሰብ  በየዓመቱ ክፍተኛ ቁጥር ያለው የጉልበት ሰራተኛ እንደሚፈልግ የአስተዳደሩ የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ዐወቀ መብራት ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡

ግማሽ ሚሊዮን የጉልበት ሠራተኛ ይፈለጋል

በየዓመቱ ለሰብል ስብሰባ እስከ አንድ ሚሊዮን የጉልበት ሠራተኛ እንደሚፈለግ ጠቁመው በዚህ ዓመትም ከመስከረም 21/2017 ዓ ም ጀምሮ በመላ አገሪቱ ለሚገኙ የጉልበት ሰራተኞች በሰሊጥ ስብሰባ እንዲሳተፉ ጥሪ አድርጓል፡፡

ኃላፊው እንዳሉት በተለይ የሰሊጥ ሰብል ለመሰብሰብ ከደረሰ ጀምሮ ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑ፣ ወዲያውኑ መሰብሰብ አለበት፣ ያ ካልሆነ ግን በቀላሉ በዝናብና በንፋስ ለብልሽት እንደሚዳረግ አመልክተዋል፡፡ እስከ አንድ ሚሊዮን ሰራተኛ የሚጠራበት ወቅት ቢኖርም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ለመሰብሰብ የደረሰው ሰሊጥ ብቻ በመሆኑ 500ሺህ የጉልበት ሰራተኛ ለስራው እንደሚፈለግ ገልጠዋል፡፡

ወደ አካባቢው ለሚመጡ የጉልበት ሰራተኞች አስፈላጊው የመጠለያ፣ የህክምናና የውሀ አቅርቦት መኖሩንና አካባቢውም ሰላም እንደሆነ ደግሞ የወልቃይት ጠገዴ  ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሸተ ደምለው ለዶይቼ ቬሌ በስልክ ተናግረዋል፡፡

Äthiopien Wolkait Tegede
ምስል Alemenew Mekonne/DW

ዝናብና ሌሎች ምክንያቶች ለምርት መቀነስ ያደረጉት አስተዋፅኦ

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአካባቢው የሚገኙና በግብርና ልማት የተሰማሩ ባለሀብቶች የዝናቡ መብዛት፣ የገበያ እጦትና አጠቃላይ ያለው ወቅታዊ የፀጥታ ችግር በአግባቡ ምርት ለማምረት እንዳላስቻላቸው ተናግረዋል፡፡

አስተያየት ከሰጡን ባለሀብቶች መካከል አንዱ ለዶቼ ቬሌ እንደገለጡት ባለፈው ዓመት በገበያ እጦት ምርት አውጥተው አልሸጡም፣ በእርግጥ ወደ ሱዳን ወስደው የሸጡ ባለሀብቶች እንዳሉም አስረድተዋል፡፡ " ፆም አዳሪዎች ሆነናል፣ እንዳንሞትም እንዳንድም ሆነን ነው ያለነው” ነው ያሉት እኚህ አስተያየት ሰጪ፡፡ ከወሎና ከጎጃም በመጡ የጉልበት ሰራተኞች በመታገዝ አሁን ምርት በመሰብሰብ ላይ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡

ሌላ በግብርና ልማት የተሰማሩ ባለሀብትም ተመሳሳይ አስተያየት አላቸው፡፡ የዝናብ መብዛት በብዙ እንደጎዳቸው አብራርተዋል፣ "በተለይ በአብደራፊና  በሁመራ አካባቢ በግብርና ልማት  የተሰማራን ባለሀብቶች ጉዳት ደርሶብናል” ብለዋል፡፡ ገበያውም በጣም እየጎዳቸው እንደሆነ የሚገልፁት እኚህ አስተያየት ሰጪ የገብርና ሥራው ወጪና ገቢውም ተመጣጣኝ እንዳልሆነ ነው የተናገሩት፡፡

ምርት ካለፈው ዓመት በ3 ሚሊዮን ኩንታል፤ ከእቅድ አንፃር በግማሽ ይቀንሳል

የአስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አወቀ፣ ባልተለመደ ሁኔታ በነበረው ከፍተኛ ዝናብ፣ በፀረተባይ፣ በነበረው የግብዓት አቅርቦት ችግርና በሌሎችም  ምክንያቶች በዚህ ዓመት ምርት ሊቀንስ እንደሚችል ሁለት ጊዜ የተደረጉ የመስክ ግምገማዎችን ለአብነት በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡

Äthiopien Wolkait Tegede
ምስል Alemenew Mekonne/DW

ባለፈው ዓመት በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ አጠቃላይ የተገኘው ምርት 9 ሚሊዮን ኩንታል እንደነበር ተናግራል፣ ይህ ምርት ዘንድሮ ከ2 ሚሊዮን እስከ 3 ሚሊዮን ኩንታል ሊቀንስ እንደሚችል ነው የጠቆሙት፡፡ በዘያዝነው ዓመት ደግሞ 12 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በተደረገ የቅድመ ምርት ግምገማ ምርቱ ከ6 እና 7 ሚሊዮን ኩንታል እንደማይበልጥ ነው ያስረዱት፡፡

ግብዓትን በተመለከተ ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት የሚመለከታቸው ሰዎች ስብሰባ ላይ በመሆናቸው አልተሳካም፡፡

ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ከጥቅምት 2013ቱ የሰሜኑ ጦርነት በፊት በትግራይ ክልል ይተዳደር የነበረ ሲሆን ከጦርነቱ በኋላ ደግሞ አሁን እንደ አንድ ዞን ሆኖ በአማራ ክልል እየተዳደረ የሚገኝ አካባቢ ነው፡፡

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ