1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአበርገለው ረሀብ በህጻናትና አቅመ ደካሞች ላይ ከፍቷል

ሰኞ፣ የካቲት 18 2016

በሆስፒታሉ ሕክምና እና የምግብ ድጋፍ የሚደረግለት ህፃኑ ሀፍቱ ንጉሱ አሁን በጥቂትም ቢሆን መሻሻል እያሳየ ነው። ባለፈው ክረምት ዝናብ ባለመዝነቡ ምንም ዓይነት ምርት ያላገኙት አርሶአደሮቹ የህፃኑ ወላጆች፥ አሁን ላይ መላ ቤተሰብ ለረሃብ ተጋልጠው ይገኛሉ። ለተእግዚሄር እና ልጆችዋ ካለፈው ጥቅምት ወር ወዲህ በከተሞች በልመና ተሰማርተዋል።

https://p.dw.com/p/4cuFZ
ድርቅ እና ረሃብ በትግራይ
ድርቅ እና ረሃብ በትግራይምስል Million Hailesilassie/DW

የአበርገለው ረሀብ በህጻናት ላይ ከፍቷል

በትግራይ በከፍተኛ ሁኔታ በድርቅና ረሃብ ከተጠቁ አካባቢዎች መካከል አንዱ አበርገለ የጭላ ወረዳ ነው። በተደጋጋሚ በድርቅ የሚጠቃው አካባቢ ዘንድሮ ደግሞ ዝናብ አለመዝነቡ ተከትሎ የእንስሳት እና የሰው ምግብ ጠፍቷል፣ በርካቶች አካባቢው ጥለው እየለቀቁ ነው። ረሀቡ በተለይም በህፃናት እና አቅመ ደካሞች ከፍቷል።

በከፍተኛ የምግብ እጥረት የተጎዳው የሁለት ዓመቱ ህፃን ሀፍቱ በመቶዎች ከሚቆጠሩት ተመሳሳይ ችግር የገጠማቸው እና በየጭላ ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው ካሉት ህፃናት መካከል አንዱ ነው። የህፃኑ እናት ለተእግዚሄር ገብረ ህፃኑ በምግብ እጥረት በከፋ ሁኔታ ሲጎዳ ወደ ሆስፒታሉ እንዳመጣችው ትናገራለች። ለተእግዚሄር "ልጄ በረሃቡ እጅግ ሲጎዳ፥ ወደዚህ ሆስፒታል ይዤው መጣሁ። የዛሬ ሳምንት ነው ወደዚህ ይዤው የመጣሁት። ፕላምፕሌት የሚባል የታሸገ ምግብ ሰጡት። እሱ ሲበላ ነው የሰነበተው" ትላለች።

በትግራይ ክልል አጽቢ ወረዳ በሶስት ወራት 111 ሰዎች በረሐብ መሞታቸውን ባለሥልጣናት ለዶይቼ ቬለ ገጹ

ሳምንት ለሚሆን ግዜ በሆስፒታሉ ሕክምና እና የምግብ ድጋፍ እየተደረገለት ያለው ህፃኑ ሀፍቱ ንጉሱ፥ አሁን ላይ በጥቂትም ቢሆን መሻሻል እያሳየ ነው። ባለፈው ክረምት ዝናብ አለመዝነቡ ተከትሎ ምንም ዓይነት ምርት ያላገኙት አርሶአደሮቹ የህፃኑ ወላጆች፥ አሁን ላይ መላ ቤተሰብ ለረሃብ ተጋልጠው ይገኛሉ። ድርቅና ረሃቡ ተከትሎ፥ ለተእግዚሄር እና ልጆችዋ ካለፈው ጥቅምት ወር ወዲህ በከተሞች በልመና ተሰማርተዋል። "ችግራችን ረሃብ ነው። የደረቀ እንጀራ ካገኘን ነው የምንበላው። የዘራነው አልበቀለም፥ ያገኘነው እርዳታም የለም። ካለፈው ጥቅምት ወር ወዲህ እየለመንን ነው የምንተዳደረው" ባይ ናት።ተመሳሳይ ችግር በመላ ትግራይ ተንሰራፍቶ ይገኛል። ረሃቡ ያስከተለው በሽታ በተለይም በህፃናት እና አቅመ ደካሞች ላይ ከፍቷል። የቻሉ እግራቸው ወደመራቸው ተሰደው ምግብ የሚለምኑ ሲሆን፥ አቅም የሌላው ባለበት መጪው ምናልባትም የከፋውን ይጠብቃል። በየጭላ ሆስፒታል የሕፃናት ሕክምና ክፍል ሐላፊው ነርስ ዮሴፍ ገብረሚካኤል እንደሚለው ባለፉት ሶስት ወራት ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ በምግብ እጥረት የተጠቁ ህፃናት ቁጥር በሶስት እጥፍ አድጓል።

ድርቅ እና ረሃብ በትግራይ
ድርቅ እና ረሃብ በትግራይምስል Mariel Mueller/ Haileselassie Million/DW

 

 

ግጭት የጋረደው ድርቅና የርሃብ አደጋ

እነዚህ ህፃናት ላይ የገጠመው የከፋ የምግብ እጥረት፥ በህፃናቱ ዘላቂ ሕይወት ላይ የከፋ ጫና እንደሚኖረው የሕክምና ባለሙያው ጨምሮ ይገልፃል። የጭላ አበርገለ ወረዳ በጦርነቱ እጅግ በጣም ከተጎዱ አካባቢዎች አንዱ ነው። የጦርነቱ ቅሪት በየመንገዱ በግልፅ ይታያል። ከጦርነቱ በቅጡ ያላገገመው ህዝብ አሁን ደግሞ ድርቅና ረሃብ ተጋርጦበታል።  የየጭላ ነዋሪ የሆኑትና በረሃብ ምክንያት ለከፋ ሁኔታ ተጋልጠው ያሉት የእምባየ ገብረስላሴ ቤተሰብ አስቸኳይ እርዳታ ካልደረሰ የሚጠብቃቸው ሞት መሆኑ ይናገራሉ። በረሃቡ ጉዳይ የክልሉ አስተዳደር እና የፌደራል መንግስት የተለያየ መረጃዎች ያቀርባሉ። የትግራይ አስተዳደር እንደሚለው በክልሉ ካለ አጠቃላይ ህዝብ ከ90 በመቶ በላይ እርዳታ ይጠብቃል።

ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ