1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል የመንገዶች መዘጋት እያስከተለ ያለው ችግር

ዓለምነው መኮንን
ማክሰኞ፣ መስከረም 28 2017

ካለፈው ሐሙስ ጀምሮ በአማራ ክልል አብዛኛው አካባቢዎች የመጓጓዣ አገልግሎት በመቋረጡ ኅብረተሰቡ ለተለያዩ እንግልቶች መዳረጉን ገልጧል ። በተለያዩ ከተሞች ነዋሪ የሆኑ አስተያየት ሰጪዎች ለዶይቸ ቬለ እንደተናገሩት ከሆነ፦ በተለይ ለህክመና የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች መታከም አልቻሉም ብለዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4lXw9
Äthiopien Bahirdar
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

መንገዶች በመዘጋታቸው ነዋሪዎች ተቸግረናል አሉ

ካለፈው ሐሙስ ጀምሮ በአማራ ክልል አብዛኛው አካባቢዎች የመጓጓዣ አገልግሎት በመቋረጡ ኅብረተሰቡ ለተለያዩ እንግልቶች መዳረጉን ገልጧል ። በተለያዩ ከተሞች ነዋሪ የሆኑ አስተያየት ሰጪዎች ለዶይቸ ቬለ እንደተናገሩት ከሆነ፦  በተለይ ለህክመና የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች መታከም አልቻሉም ብለዋል ።

በአማራ ክልል ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮ በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንት በተለይ የመንገዶች በየጊዜው በፀጥታ ስጋት መዘጋት በኅብረተሰቡ የእለት ከእለት እንቅስቃሴ ላይ ጫና እየፈጠረ ነው ፡፡ ሰሞኑንም መንገዶች በመዘጋታቸው በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን እያስከተለ ነው ፡፡

በምዕራብ ጎጃም ዞን አንድ የደንበጫ ከተማ  ነዋሪ ካለፈው ሐሙስ ጀምሮ የትራንስፖርት እንቅስቃሴው የተዘጋ በመሆኑ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ የለም ነው ያሉት፡፡ ሰሞኑን መሰጠት የጀመረውን የፖሊዮ ክትባትም ማስጀመር እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡

እንደ አስተያየት ሰጪው መንገዶች በመዘጋታቸው የወረዳ ጠና ጣቢያ ባለሙያዎችን ወደ ከተማ ተርቶ ስለ ፖሊዮ ክትባት አሰጣጥ ስልጠና መስጠት ባለመቻሉ ክትባቱ በአካባቢው እተጀመረም ብለዋል፡፡

የምዕራብ ጎንደር መተማ ዮሐንስ ነዋሪ በበኩላቸው የቅርብ እንቅስቃሴዎች ቢኖሩም ወደ ጎንደርና ሌሎች ራቅ ወደዳሉ አካባቢዎች መንቀሳቀስ እንደማይቻል አመልክተዋል፣ ባለፈው በአካባቢው በነበረው የፋኖና የኢትዮጵያ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ግብይት ወደሚደረግበት የሱዳን ጠረፍ ከተማ ወደሆነችው ገላባትም በግባት እንደማቻል አስረድተዋል፡፡

ከጦርነቱ ጀምሮ የሱዳን መንግስት ደንበሩን በመዝጋቱ በአካባቢው በነበረው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ጫና እንደፈጠረ መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡ ኅሙማን ወደ ህክምና ሄደው መመለስ እንኳ ባለመቻላቸው ለተጨማሪ ወጪ እየተዳረጉ እንደሆነ ደግሞ በምስራቅ ጎጃም ዞን የደብረወርቅ ከተማ ነዋሪ ለዶይቼ ቬሌ አመልክተዋል፡፡ እርሳቸው በቅርብ የሚያውቋቸው ህሙማን ወደ ደብረማርቆስ ለህክምና ሄደው እስካሁን መመለስ እንዳልቻሉ ነው የገለፁልን፡፡

አማራ ክልል የመጓጓዣ አገልግሎት መቋረጥ
አማራ ክልል የመጓጓዣ አገልግሎት መቋረጥምስል Alemnew Mekonnen/DW

በሰሜን ሸዋ ዞን የአጣዬ ከተማ ነዋሪም በከተማ ውስጥ የባለሦስት ተሸከርካሪዎች እንቅስቃሴ ቢኖርም፣ ወደ አዲስ አበባና ደሴ ከተሞች የሚያልፉና ከአጣዬ ተነስተው የሚሄዱ ተሸከርካሪዎች እንደማታዩ ገልጠዋል፡፡

በከፊል የተሸከርካሪ እንቅስቃሴ ወደ አንዳንድ አካባቢዎች መኖሩን የገለፁልን ደግሞ በማዕከላዊ ጎንደር የጎንደር ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ ወደ ቆላማው የወልቃይትና ሁመራ አቅጣጫዎች ተሸከርካሪዎች ቢንቀሳቀሱም ወደ ባሕር ዳርና ወደ ሌሎች አካባቢዎች ግን የትራንስፖረት አገልግሎት እንደሌለ ነው ያመለከቱት፡፡ በዚህም ምክንያት የሸቀጦች ዋጋ መጨመሩን ነው ያስረዱን፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን የደሴ ከተማ አስተዳደር አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው ቅርብ ቅርብ ሉ ከተሞች የትራንስፖርት አገልግሎቶች ቢኖሩም ወደ አዲስ አበባ፣ ባህር ዳርና ወልዲያ ግን ከቆመ ቆቷል ብለዋል፡፡ የመንገዶች በየጊዜው መዘጋጋት በኅብረተሰቡ ኑሮ ላይ ጉዳቱ የከፋ መሆኑን አንየፈረስ ቤት ከተማ ነዋሪ ገልጠዋል፡፡ 

የመንገዶች በየጊዜው መዘጋጋት
የመንገዶች በየጊዜው መዘጋጋት ፦ አማራ ክልል፤ ባሕርዳርምስል Alemnew Mekonnen/DW

በተደጋጋሚ ጦርነት የሚካሄድባት ፈረስ ቤት  ከተማ የትራንስፖርትና የገበያ አገልግሎቶች ከቆሙ ከወር በላይ በመሆኑ ሸምቶ አዳሪው ማህበረሰብ በችግር ውስጥ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በባህር ዳር ከተማ ሁለት መናኸሪያዎች ተዘዋውረን እንደተመለከትነው ወደ መናኸሪው የሚገባም ሆነ የሚወጣ የህዝብ ትራንስፖረት አገልግሎት ሰጪ ተሸከርካሪዎች ዐይታዩም፡፡ 

በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የባህርዳር ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ አምሳሉ ጫኔ የመንገዶች በየጊዜው በፀጥታ ምክንያት  መዘጋጋት መድኃኒት ወደ ጤና ተቋማት ለማድረስ ችግር እየፈጠረባቸው እንደሆነ ገልጠዋል፡፡ ዓለም አቅፍ ተቋማት መድኃኒት ከቦታ ቦታ ለማድረስ የሚደረገውን ስራ እንዲግዙም ኃላፊው ጠይቀዋል፡፡ አጠቃላይ የመንገድ መዘጋትንና እየደረሰ ያለውን ችግር በተመለከተ ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ለክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ስልክ ብንደውልም ስልካቸውን ማንሳት አልቻሉም፡፡

ዓለምነው  መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሠ