1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በመቀሌ ወህኒ ቤት የሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጉዳይ

ሰኞ፣ መጋቢት 16 2016

እነዚህን የሰራዊት አባላት ለግዳጅ የላካቸው መንግስት እንደመሆኑ መንግስት ሊያስፈታቸውም ይገባል የሚሉት አስተያየት ሰጪው፤ የመከላከያ ሰራዊት አባላቱ “ታፍነው” ወደ እስር ቤት ገብተዋል ያሉትም ሰኔ 19 ቀን 2013 ዓ.ም. መንግስት የመከላከያ ሰራዊቱ ትግራይ ክልልን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ስያስተላልፍ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡

https://p.dw.com/p/4e6PB
Gefangener hinter Gittern (Symbolbild)
ምስል YAY Images/imago images

በመቀሌ ወህኒ ቤት የሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጉዳይ

“በትግራይ ለግዳጅ በሄድንበት ወቅት አብረውን የነበሩ ታፍነው የቀሩት አሉ በዚያ” ያሉን አሁን ላይ በኦሮሚያ ክልል በወታደራዊ ግዳጅ ላይ እንደሆኑ ገልጸው ስለቀድሞ ጓዶቻቸው አሁንም ድረስ በመቀሌ ወህኒ ቤት እስር ላይ መገኘት ያስረዱን አስተያየት ሰጪ ናቸው፡፡ ለደህንነታቸው ስባል ስማቸውን አይጥቀሱት እንጂ በሻለቃ ወታደራዊ ማዕረግ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ውስጥ እያገለገሉ እንደሆነ ያስረዱን አስተያየት ሰጪው፤ በቀድሞ የትግራይ ታጣቂዎች “ተቆርጠው ቀርተዋል” ያሉት ለ2 ዓመት ከመንፈቅ በላይ በእስር ቤት የቆዩቱ የሠራዊቱ አባላት ቁጥርም 449 መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

“አራት መቶ አርባ ዘጠኝ ናቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ 60ዎቹ መኮንኖች ናቸው፡፡ የበታች ሹሞችም እንዲሁ ይገኙበታል፡፡ እኛ በደንብ እናውቃለን፡፡ ጓዶቻችን እንደመሆናቸው የስልክ ልውውጥ እስካሁንም እናደርጋለን፤ ደግሞ ቤተሰብ  ስለሆንን ሂደው የሚጠዩቋቸው አሉ” ብለዋል፡፡

ትግራይ ውስጥ ታፍነው የነበሩ የሠራዊት አባላት  

እነዚህን የሰራዊት አባላት ለግዳጅ የላካቸው መንግስት እንደመሆኑ መንግስት ሊያስፈታቸውም ይገባል የሚሉት አስተያየት ሰጪው፤ የመከላከያ ሰራዊት አባላቱ “ታፍነው” ወደ እስር ቤት ገብተዋል ያሉትም ሰኔ 19 ቀን 2013 ዓ.ም. መንግስት የመከላከያ ሰራዊቱ ትግራይ ክልልን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ስያስተላልፍ እንደነበር ያስረዳሉ፡፡ “በጊዜው በሰቆጣ አቅጣጫ ስንወጣ ነበር ተቆርጠው የቀሩት፡፡ አንድ ላይ ነበርን እነሱ ሲቆረጡ ሰኔ 19 ቀን 2013 ዓ.ም ነበር፡፡ ስምምነት ተፈጽሟል ይወጣሉ በፕሪቶሪያው ስምምነት ቢባልም እስካሁን እስር ላይ ናቸው” ብለዋልም፡፡

የመቀሌ ከተማ
የመቀሌ ከተማ ምስል Million Haileselassie/DW

የተጠረጠሩበት ወንጀል

ሌላው በዚያ በመቀሌ ወህኒ ቤት ታስረው ከሚገኙት ውስጥ ሌላ ለዶቼቬለ አስተያየታቸውን የሰጡ እስካሁን በይፋ የተመሰረተባቸው ክስ አለመኖሩን በማስረዳት “እናንተ ተለይታችሁ የታሰራችሁት የጦር ወንጀል በመፈጸም ተጠርጥራችሁ ነው” እየተባልን ነው ይላሉ፡፡ “449 ሰው እዚህ ለይተው ያስቀሩን ‘Genocide’ ፈፅማችኋል በሚል ነው፡፡ ነገር ግን እኛ ምንም አይነት የፈጸምነው የዘር ፍጂት የለም፡፡ እኛ በሃላፊነታችን መሰረት ስንጠብቃችሁ ነበርን፤ ዛሬም-ነገም እንጠብቃችኋለን ነው ያልናቸው፡፡ በርግጥ የተፈጠረ ችግር ነበር፡፡ ያ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት ተፈቷልና እኛም የእርቁ ተቋዳሽ መሆን አለብን ብለን ነው የምናስበው” ሲሉም አስተያየታቸውን አጋርተዋል፡፡ “እኔም ሆንኩ ጓዶቼ የፈጸምነው ወንጀል የለም” የሚሉት አስተያየት ሰጪው፤ የተመሰረተባቸው ክስ እስካሁን አለመኖሩንም ገልጸው፤ የሚጠረጠሩበት ወንጀል እንኳ ቢኖር በማስረጃ ቢጠየቁ ፍላጎታቸው መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

እስካሁን አነጋግሮአቸው የሚያውቅ የሲቪልም ሆነ ወታደራዊ አመራር ስለመኖር አለመኖርም የተጠየቁት አስተያየት ሰጪው፤ “አንድ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ኮሚሽነር መጥተው አነጋግሮን ነበር፡፡ እኛም አገራዊ ኃላፊነታችንን ከመፈጸም ያለፈ ህዝብ ላይ የፈጸምነው በደል አለመኖሩን አስረድተን በነጻ እንዲለቁን አሊያም የተጠረጠርንበት ወንጀልም ካለ ለፌዴራል መንግስት አሳልፈው እንዲሰጡን ጠይቀናቸው ነበር” ነው ያሉት፡፡

ጥሪ የተደረገላቸው የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት 

የፕሪቶሪያ ስምምነት እና ከእስር የመፈታት ተስፋ

አስተያየት ሰጪ ወታደሮቹ በተቃራኒው ግን የፌዴራሉ መንግስት በፕሪቶሪያው ስምምነት ማግስት ተማርከው የነበሩትን የቀድሞ የትግራይ ተዋጊዎች እና በፌዴራል መንግስት እስር ላይ የነበሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት መለቀቃቸውን እንደሚውቁ ነው ያሚያስረዱት፡፡ “እኔ የማውቀው በአንድ ጊዜ እራሱ 18 መኪና ሙሉ ምርኮኞች ተለቀው ነበር፡፡ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የቀድሞ ወታደሮችም ከእስር ተፈተው አሁን አብረን እየሰራን እንገኛለን” ነው ያሉት፡፡

የመቀሌ ከተማ
የመቀሌ ከተማምስል Million Haileselassie/DW

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምላሽ

ይህን የአስተያየት ሰጪዎቹን ቅሬታ ይዘን ለአገር መከላከያ ሰራዊት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ እና ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ደውለን ተጨማሪ ኃሳቦችን ለመቀብል ተደጋጋሚ ጥረት ብናደርግም እስካሁን ጥረቱ አልሰመረም፡፡ በሳምንቱ መጨረሻ ይፋዊ መግለጫ ያወጣው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ እዳመለከተው ግን በትግራዩ ጦርነት ወቅት “ተማርከው ነበር” የተባሉ 112 የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት አባላት ዓርብ መጋቢት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ተጨማሪ 100 ደግሞ በማግስቱ ቅዳሜ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ባጠቃላይም 212 የሚሆኑት “በምህረት” መፈታታቸውን አስታውቋል። የቀረበው የወታደሮቹ ቅሬታ ግን በዚህም ቁጥር መሰረት በወህኒ ቤት የቀሩ የሰራዊቱ አባላት መኖራቸውን ይጠቁማል፡፡

ከሰሞኑ ተፈቱ የተባሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላቱ፤ የፌደራል መንግስት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጥቅምት 2015 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት ከመፈራረማቸው በፊት የተማረኩ መሆናቸውን ግን የትግራይ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሰሞነኛው መግለጫ ጠቅሷል። ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ከ16 ሺህ በላይ የመከላከያ ሰራዊት አባላት መለቀቃቸውንም ጽህፈት ቤቱ አስታውሷል።

ስዩም ጌቱ

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ