1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ሳይጠበቅ ድንገት ጣሪያ የነካው የምግብ ዘይት ዋጋ ጉዳይ

ሰኞ፣ የካቲት 28 2014

ያልተጠበቀ የዘይት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ነዋሪዎችና በምግብ ቤት ስራ የተሰማሩ ወገኖች ለችግር መዳረጋቸውን አመለከቱ፣ የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ በዩክሬንና በሩሲያ መካከል የተፈጠረውን ጦርነት በመጠቀም አንዳንድ ነጋዴዎች የምግብ ዘይት ሊጠፋ ነው ብለው በማስወራት የዘይት ዋጋ እንዲጨምር አድርገዋል ይላል፣

https://p.dw.com/p/487dP
Äthiopien Bahir Dar | Speiseöl
ምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

ያልተጠበቀ የዘይት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ነዋሪዎችና በምግብ ቤት ስራ የተሰማሩ ወገኖች ለችግር መዳረጋቸውን አመለከቱ፣ የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ በዩክሬንና በሩሲያ መካከል የተፈጠረውን ጦርነት በመጠቀም አንዳንድ ነጋዴዎች የምግብ ዘይት ሊጠፋ ነው ብለው በማስወራት የዘይት ዋጋ እንዲጨምር አድርገዋል ይላል፣ አምራቾች በበኩላቸው የውጭ ምንዛሬ እጥረት የምርት መቀነስ ፈጥሮብናል ብለዋል፡፡
ባለፉት 3 እና 4 ቀናት የዘይት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደገቡ ነዋሪዎችና የምግብ ቤት ባለቤቶች አማርረዋል። 
በባሕርዳር ከተማ አንድ የምግብ ቤት ባለቤት የዘይት ዋጋ በማይታሰብ ሁኔታ ዋጋው በመጨመሩ ምግብ አዘጋጅቶ ለመሸጥ ወይም በምግብ ላይ ዋጋ ለመጨመርም ተቸግረዋል። በአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የገበያ ጥናት ባለሙያ ወ/ሮ ጤና ደጉ ጭማሪ መኖሩን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል። በአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አቢታ ገበየሁ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ ከማዕከል የተላከ የምግብ ዘይት ከዛሬ ጀምሮ እንደሚሰራጭ ጠቁመው፣ አንዳንድ ነጋዴዎች የዩክሬንና የሩሲያን ጦርነት መነሻ በማድረግ ዋጋ ለመጨመር ጥረት እያደረጉ ነው በማለት ከስሰዋል።
ከውጪ የሚመጣን የዘይት ምርት ሊያስቀሩ ይችላሉ ተብለውሥራ ስለጀመሩት የዘይት ፋብሪካዎች ዋጋውን ከማባባስ ውጪ የፈየዱት ነገር የለም ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰጠኝ እንግዳው በበኩላቸው ፌቤላ የምግብ ዘይት ፋብሪካ ባለፈው አንድ ዓመት 105 ሺህ ሜትሪክ ቶን ድፍድፍ የፓልም ዘይት ከውጪ በማስገባት 66 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ማሰራጨቱን ተናግረዋል። በኮቪድ፣ በምግብ ዘይት ዋጋ መጨመር፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረትና በሌሎችም ምክንያቶች ፋብሪካው የማምረት አቅሙ በግማሽ ቢቀንስም በዋጋ ላይ ግን ምንም ጫማሪ አልተደረገም ነው ያሉት፡፡
በቅርቡ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን ደፍድፍ የፓልም ዘይት ወደ ምርት በመቀየር በፍጥነት ወደገበያ እንደሚያቀርቡም ዳይሬክተሩ አመልክተዋል። የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የዘይት ዋጋ ዝርዝር ይፋ አድርጓል፡፡
በዚህም መሰረት ህብረት ስራ ማህበራት ፓልም ዘይት ከአለ ከጅምላ 20 ሊትር በ1ሺህ 575 ብር፣ 5 ሊትር በ408 ብር፣ 3 ሊትር በ251 ብር እንዲገዙ ሲወስን ቸርቻሪዎች ደግሞ ለተጠቃሚው 20 ሊትር ዘይት 1ሺህ 642 ብር፣ 5 ሊትር ዘይት 426 ብር፣ 3 ሊትር ዘይት 262 ብር እንዲሸጡ ወስኗል። 


ዓለምነው መኮንን

ታምራት ዲንሳ

ማንተጋፍቶት ስለሺ