1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ሰዎች በርሐብ እየሞቱ ነው»የተፈናቃዮች አቤቱታ

ዓለምነው መኮንን
ረቡዕ፣ መስከረም 8 2017

በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋዎች ለከፋ የምግብ እህል እጥረት መጋለጣቸውን ዐሳወቁ ። መንግስት የአቅርቦት ችግር እንዳለበት አመልክቷል ። ሰዎች በርሐብ እየሞቱ ነው፣ ለልመናም የወጡ ተፈናቃዮች እንዳሉም ተነግሯል፡፡

https://p.dw.com/p/4kmZw
Äthiopien IDPs in der Region Amhara
ምስል Alemenw Mekonnen/DW

ነዋሪዎች ለከፋ የምግብ እህል እጥረት ተጋልጠዋል

በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ለከፋ የምግብ እህል እጥረት መጋለጣቸውን ዐሳወቁ ። መንግስት የአቅርቦት ችግር እንዳለበት አመልክቷል ። ሰዎች በርሐብ እየሞቱ ነው፣ ለልመናም የወጡ ተፈናቃዮች እንዳሉም ተነግሯል፡፡

 በአማራ ክልል ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል በደቡብ ወሎ ሐይቅ በአካባቢ ከተማ በሚገኝ የመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ  ተፈናቃዮች ለከፍተኛ የርሀብ አደጋ እንደተጋለጡ ተናግረዋል፣ እርዳታ ካገኙም ወር እንዳለፋቸው ነው የሚገልፁት፣ አንዳንዶቹ እንዲያውም ለልመና መውጣታቸውን ተፈናቃዮች ይናገራሉ፡፡

ተፈናቃዩ በጣም ተቸግሯል ያሉት እጂህ ተፈናቃይ፣ ባለፈው የተሰጠው 15 ኪሎ ዱቄትም አልቋል ነው ያሉት፡፡ የሚሰጠው ርዳታ በቂ ባለመሆኑ አንዳንዶቹ ለልመና ወጥተዋል ብለዋል፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን መካነ ሰላም ከተማ "ለገአማራ” በሚባል መጠለያ የሚኖሩ ሌላ ተፈናቃይ ችግሩ መባባሱንና በርሀብ ሰዎች መሞታቸውን ገልፀዋል፡፡

ምንም ምግብ እንደሌለ የገለፁት እኚህ ተፈናቃ ደግሞ በርሀብ፣ በብርድና በበሽታ ሰዎች እየተሰቃዩ እንደሆነ አመልክተዋል፣ እንደ አስተያየተ ሰጪዋ ባለፉት ጥቂት ቀናት ሶስት ተፈናቃዮች ከርሀብ ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው አልፏል፡፡

ነሐሴ መጀመሪያ ላይ 15 ኪሎ ዱቄት መውሰዳቸውን የሚገልፁት አንድ አስተያየት ሰጪ፣ ከ15 ኪሎዋ ተቀንሶ ለትራንስፖርትና ለሌሎች አገልግሎቶች ወጪዎች በመሆኑ  ለምግብ እህል እጥረት በእጅጉ እንደተጋለጡ ነው ያመለከቱት፡፡

ከምስራቅ ወለጋ የተፈናቀሉና 5 ህፃናትን የያዙ እናትም ህጻናቱን ለማስተዳደር እንዳልቻሉ ነው ለዶይቼ ቬሌ ያስረዱት፣ የቀን ስራ ይሰሩ የነበሩት በለቤታቸውም አሁን የሚሰራ ስራ ባለመኖሩ ገቢያቸው በእጅጉ ማሽቆልቆሉን አብራርተዋል፡፡

በአማራ ክልል የተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ በርካታ ተፈናቃዮች ይገኛሉ ። ፎቶ ከክምችት ማኅደር
በአማራ ክልል የተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ በርካታ ተፈናቃዮች ይገኛሉ ። ፎቶ ከክምችት ማኅደርምስል Alamata City Youth League

የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አሊ ሰኢድ የእርዳታ እህል እንዲቀርብ ለክልል ማሳወቃቸውን አመልክተው ሆኖም ምላሽ እስካሁን አልተገኘም ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳሬክተር አቶ ብርሀኑ ዘውዱ በሰጡት ምላሽ ደግም በመጠለያ ያሉ ወገኖችን ይረዱ የነበሩ ረጂ ተቋማት ቁጥራቸው መቀነሱን ተናግረዋል፣ ከማህበረሰቡ ጋር የሚኖሩትን የሚረዳ መንግስታዊ ያልሆ ተቋምም እንደሌለ አመልክተው ያለውን ክፍተት መንግስት እየሞላ ነው ብለዋል፣ ያም ሆኖ የእርዳታ አቅርቦት ችግር አለ ነው ያሉት፡፡

አሁን ያጋጠመውን የርዳታ አቅርቦት ችግር በተመለከተ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እያደረጉበት እንደሆነና እርዳታ እንዲቀርብ ትረት ይደረጋል ብለዋል፡፡ በአማራ ክልል በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ችግሮች ከ2 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች የርዳታ እህል ጠባቂዎች  እንደሆኑም ኮሚሽኑ አመልክቷል፡፡

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ፀሐይ ጫኔ