1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ምርጫ አስፈፃሚዎቹ የዩንቨርስቲ ምሩቃን

ልደት አበበ/ Lidet Abebe
ዓርብ፣ መጋቢት 17 2013

ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ ሳምንት በሺዎች የሚቆጠሩ ምሩቅ ተማሪዎች የምርጫ አስፈፃሚነት ስልጠና ወስደዋል።  በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ሰልጣኞች እንደገለፁልን ከሆነ ሁሉም የተሰጣቸውን ሀላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ ናቸው። ስላገኙት ስልጠና እና ስለሚጠብቃቸው ስራ ጠይቀናቸዋል።

https://p.dw.com/p/3rDPg
Äthiopien Registrierung für  Sidama-Referendum
ምስል፦ DW/S. Wegayehu

ምርጫ አስፈፃሚዎቹ የዩንቨርስቲ ምሩቃን

ኢትዮጵያ ውስጥ ለ6ኛው አጠቃላይ ሀገር አቀፍ ምርጫ የሚደረገው ዝግጅት  ቀጥሏል። ምርጫ ለማካሄድ ምርጫ አስፈፃሚዎች ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል። መራጮች ወደ ምርጫ ጣቢያ ሲሄዱም በአካል አግኝተው የሚያነጋግሯቸው ሰዎች ናቸው።  ታድያ እንዴት ምርጫ አስፈፃሚ ይኮናል? ምን አይነት የስራ ኃላፊነትስ አለው? 
ተመስገን መዝገቡ ባለፈው ጥር ወር ከባህርዳር ዮንቨርስቲ በኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት ተመርቋል።  ሰሞኑን ደግሞ በአማራ ክልል በምርጫ አስፈፃሚነት ለማገልገል ስልጠና ከወሰዱት መካከል ነው። ስለ ምርጫ የተወሰነ ግንዛቤ ቢኖረኝም «በዚህ ስልጠና ደግሞ የተሻለ በግሌ ላሉኝ ጥያቄዎች መልስ አግኝቼበታለሁ» የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ ነው «ስራችን መራጮችን መመዝገብ ነው የሚሆነው።  የምርጫ ቅስቀሳ ላይ አንሳተፍም። ምዝገባው ላይ ጥርት ያለ፣ ምንም አድሎ የሌለው ስራ ለመስራት የምንጠራበትን ቀን እየተጠባበኩኝ ነው ያለሁት።» ይላል። ከዚህ በፊት በምርጫ ተሳትፎ ወይም ድምፅ ሰጥቶ አያውቅም። የ24 ዓመቱ ወጣት የተመዘገብኩት ምርጫ ቦርድ ባዘጋጀው መሠረት በኦንላይን ነበር ይላል። አንዳንዶቹ በፁሁፍ ሌሎቹ ደግሞ ስልክ ተደውሎላቸው ማክሰኞ እና ዕርብ ስልጠና እንዲወስዱ መጠራታቸውንም ነግሮናል።

የ25 ዓመቷ ወጣት ኤቢሴ በኦሮሚያ ክልል ስልጠናውን ወስዳለች። « ስልጠናው በሁለት አሰልጣኞች በኦሮምኛ ቋንቅ ነበር የተሰጠን። ስልጠናው በብዛት ዘንድሮ ለተመረቁ ልጆች ስለነበረ የሚሰጠው ኦሮምኛ ለማይችሉ በአማርኛ ይተረጎምላቸው ነበር።» ትላለች። በስልጠናው የረካችው ኤቢሴ  የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል መራጮች እንዴት ርቀታቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው እና የፀጥታ ችግር ቢነሳ አስፈፃሚዎቹ እንዴት ከፖሊስ ጋር መስራት እንዳለባቸው ስልጠና መውሰዳቸውንም ታስረዳለች።  እሷም መብቷን ተጠቅማ ዘንድሮ ትመርጣለች።

በትክክል መቼ ስራ እንደሚጀምሩ ወጣቶቹ ገና አያውቁትም። የሚጠሩበትን ቀን እየተጠባበቁ ይገኛሉ። ኤቢሴ ውልም ተፈራርመን ጨርሰናል ትላለች። ነገር ግን ውሉ መጀመሪያ ላይ ከጠበቀችው የተለየ ሆኖ አግኝተዋለች። « ያኔ ማስታወቂያው ላይ አይተን ስንመዘገብ ለአራት ወር እንደምንሰራ ነበር። አሁን ውሉ እጃችን ውስጥ ሲገባ ግን ለ 47 ቀን ብቻ ነው የሚለው።»  
ምንም እንኳን በርካታ ተመዝጋቢዎች እንደጠበቁት የምርጫ አስፈፃሚነቱ ስራ ለአራት ወር የሚቆይ ባይሆንም ለተዋዋሉበት 47 ቀናት አበል ይታሰብላቸዋል። የስራ ልምድ ሰርተፍኬት እና የድጋፍ ደብዳቤም ቦርዱ የሚሰጥ መሆኑን አስታውቋል። ኤቢሴ ወደፊት በተማረችበት የኮምፒውተር እንጂነሪንግ ስራ ለማፈላለግ አቅዳለች። ይህ የምርጫ ተሳትፎዋም ወደፊት ስራ ለማፈላለግ እንደሚረዳት ተስፋ አላት። በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን  ሾላ ከተማ  ባለ አንድ ቀበሌ ምርጫ አስፈፃሚ ሆኖ የተመደበው ተመስገን እስካሁን ስራ አላገኘም። እሱም በተማረበት ሙያ እንደሚያፈላልግ ነግሮናል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ለማካሔድ ከ 140 ሺህ በላይ አስፈጻሚዎች እንደሚያስፈልጉ ድረገፁ ላይ ያወጣው ማስታወቂያ ይጠቁማል። የእነዚህም ምርጫ አስፈፃሚዎች  ፍቃደኝነትን፣ ገለልተኝነትን እና ብቃትን እንደሚያረጋግጥም ምርጫ ቦርዱ ገልጿል። ወጣት ኤደን ከቅርብ ወራት አንስቶ ለደቡብ ክልል ምርጫ ቦርድ ትሰራለች ። የስርዓተ ፆታ ባለሙያ ናት። «ምርጫ አስፈፃሚዎች በምንመለምል ጊዜ ከሶስት አስፈሚዎች አንዷ ሴት እንድትሆን የምናስገድድበት ሁኔታ አለ።» ትላለች። ኤደንን ጨምሮ በዚህ የምርጫ አስፈፃሚነት የሚሳተፉት ወጣቶች መሆናቸው« ወጣቱ ስለ ምርጫ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረዉ ይረዳል» ትላለች ኤደን። « ምክንያቱም ወጣቱ የነገ ሀገር ተረካቢ ነው። ልክ ለሴቶች እንደሚሰራው ሁሉ ወጣቶች ተሳታፊ እንዲሆኑ በአግባቡ ቢሮው እየሰራ ይገኛል።» በማለት ትልቅ ለውጥ እንዳለ ትናገራለች።
ተመስገን መንገሻ የሐዋሳ ከተማ ምርጫ አስፈፃሚ ነው። የወጣቶች ተሳትፎ ለዲሞክራሲ ባህል አስፈላጊ መሆኑን አንስቶ « ብቃታችንንም ማሳየት የምንችልበት ጥሩ አጋጣሚ ተፈጥሯል» ይላል።  «  ምርጫ ለማስፈፀም  ድሮ ወጣት አይችልም። ወጣት ደካማ ነው ይባላል። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ወጣቶች ምን ያህል እንደምንችል እያሳየን ነው።» በማለት ብዙ ነገሮችን መማሩን ተመስገን ይናገራል። በሐዋሳ ከተማ የ IT ባለሙያ ሆኖ ምርጫውን ለማስፈፀም የሚያግዘው ስለሺ፤  ቀደም ሲል እንደሰማናቸው ወጣቶች ሁሉ በምርጫ አስፈፃሚነት ብቻ ሳይሆን ድምፅ በመስጠትም ሲሳተፍ ይህ የመጀመሪያው ጊዜ ነው የሚሆነው። « ምርጫው ሰላማዊ እና ፍትኃዊ ሆኖ እንዲያልቅ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት የራሳቸውን ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል። » ሲል ስለሺ አደራ ይባል። 

Äthiopien Die politischen Parteien gründen einen Versammlungsrat - Hawassa
ምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW


ልደት አበበ 

ነጋሽ መሀመድ