1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሰሜን ሸዋ ከመንገድ መከፈት 6 ቀን በኋላ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 4 2016

በሰሜን ሸዋ አጣየና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ለፀጥታ ሥራ በሚል ለ6 ሳምንታት ያህል ተዘግቶ የነበረው መንገድ ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ክፍት ሆኖ መቀጠሉ ተገለጠ ። መንገዱ ተዘግቶ በቆየበት ወቅት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተከስተው መሰንበታቸውንም ገልፀዋል ።

https://p.dw.com/p/4ehnp
ሸዋ ሮቢት ከተማ በከፊል፦ ፎቶ ከማኅደር
ሸዋ ሮቢት ከተማ በከፊል፦ ፎቶ ከማኅደር ምስል Maria Gerth-Niculescu/DW

ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተከስተው ቆይተዋል

በሰሜን ሸዋ አጣየና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ለፀጥታ ሥራ በሚል ለ6 ሳምንታት ያህል ተዘግቶ የነበረው መንገድ ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ክፍት ሆኖ መቀጠሉ ተገለጠ ። የደሴ ደብረ ብርሃንና የደብረ ብርሃን ደሴ መንገድ ከዚህ ሳምንት መጀመሪያ ጀምሮ ክፍት መደረጉን ነዋሪዎችና የየአካባቢ ባለስልጣናት ተናግረዋል ። መንገዱ ተዘግቶ በቆየበት ወቅት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተከስተው መሰንበታቸውንም ገልፀዋል ። 

በአማራ ክልል በተለይም ካለፈው ነሐሴ 2015 ዓ.ም መጀመሪያ ጀምሮ የፀጥታ ችግሮች በክልሉ ነዋሪዎች ላይ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን አስከትሏል፡፡ ከሕይወት መጥፋትና ከንብረት ውድመት ባሻገር የመንገዶች መዘጋጋት በነዋሪዎች የእለት ከእለት እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡

የማዕከላዊ ሸዋ እዝ ጣቢያ (Command Post) ለፀጥታ ሥራ በሚል ከየካቲት 16 ጀምሮ ከደብረ ብርሐን ወደ ደሴና ከደሴ ወደ ደብረብርሃን የሚወስደውን መንገድ ዝግ እንዲሆን ትዕዛዝ አስተላልፎ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ግን መንገዱ ለትራፊክ ክፍት መሆኑንና በአካባቢው አንፃራዊ ሰላም መስፈኑን በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አንድ የአጣየ ከተማ ነዋሪ ለዶይቼ ቬሌ በስልክ የተናገሩት፡፡

በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ሐብታሙ እሸቱ መንገዱ ዝግ በነበረበት ወቅት በርከት ያሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መከሰታቸውን ጠቅሰው ሆኖም መንገዱ በዚህ ሳምንት ለትራፊክ ክፍት መሆኑን ህብረተሰቡ ወደ ተለመደው መደበኛ እንቅስቃሴ ተመልሷል ብለዋል፡፡

ሌላ  የአጣየ ከተማ ነዋሪ ባለፉት 6 ሳምንታት በመንገዱ መዘጋት ምክንያት በኅብረተሰቡ ላይ ጫና ፈጥሮ መቆየቱን ተናግረዋል፣ አሁን መንገዱ መከፈቱንና የከተማዋ እንቅስቃሴም እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጠዋል፡፡

"በጤና ላይ ችግር ፈጥሯል፣ በርካታ ወላዶች፣ በሽተኞች ለከፍተኛ ህክምና መሸኛ ተፀፎላቸው መሄድ አልቻሉም፣ በሌላ ቦታ (በአፋር ክልል በኩል) ዞረው ለመሄድ ሲሞክሩ ደግሞ መንገዱ አስቸጋሪ ስለሆነ ሰዎች እየተጎዱ ነፍሰ ጡሮች ለአደጋ ሲጋለጡ ነበር፣ ባንኮችም በዚህ አጋጣሚ ተዘግተው ነበር የቆዩት” ብለዋል፡፡

መንገዱ በመዘጋቱ መንገደኞች በአፋር ክልል በኩል ዞረው ለመሄድ ሲሞክሩ ነበር
መንገዱ በመዘጋቱ መንገደኞች በአፋር ክልል በኩል ዞረው ለመሄድ ሲሞክሩ ነበር። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Seyoum Getu/DW

በአማራ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን በሸዋ ሮቢት ከተማ የሚገኝ የፀጥታ ክፍል ሻምበል አዛዥ እንደሆኑ የነገሩን ኢንስፔክተር ኪዳኔ ጌታቸው ከህብረተሰቡ ጋር በተደረጉ ተከታታይ ውይይቶች የአካባቢው ሰላም እየተመለሰ በመምታቱ መንገዶች ተከፍተዋል ብለዋል፡፡

አክለውም፣ «እዚህ ያለው እዝ ጣቢያ  (Command Post) ሰፊ ሥራ እየሠራ ነው፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደርም የነበሩ ግጭቶችን ወደ ሰላማዊ መንገድ በማምጣት፣ ከሐገር ሽማግሌና ካለው ማኅበረሰብ ጋር በመወያየት ያው ችግሩ እንዲፈታ ተደርጓል፣ አሁን ሸዋ ሮቢት አካባቢ አንፃራዊ ሰላም ነው ያለው፣ በየደረጃው ሕዝባዊ ውይይቶች ይደረጋሉ፣ አሁን ይህን ያክል ችግሮች አሉ ብሎ ማስቀመጥ አይቻልም ። ከሰኞ እለት ጀምሮ የትራፊክ ፍሰቱ የተሻለ ነው። ያው እንቅስቃሴዎች አሉ፡» ነው ያሉት፡፡

መንገዱ በተዘጋበት ወቅት እናቶችና አቅመ ደካሞች ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስ ተቸግረው እንደነበርም ኢንስፔክተር ኪዳኔ ተናግረዋል። ሰላሙ እየተሻሻለ በመምጣቱና መንገዶች በመከፈታቸው ችግሮች እተቃለሉ እየመጡ መሆናቸውንም ነግረውናል፡፡

የማዕከላዊ ሸዋ እዝ ጣቢያ (Central Shewa Command Post) "ፅንፈኛ” ብሎ በጠራቸው ኃይሎች ላይ ርምጃ እየተወሰደ መሆኑን በመግለፅና "ለህዝቦች ደህንነት” በሚል መንገዱ ከየካቲት አጋማሽ ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ መዘጋቱን አሳውቆ ነበር፡፡

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ