1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሸዋሮቢት ላይ ሰዎች መገደላቸው

ሰኞ፣ ሰኔ 27 2014

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሸዋ ሮቢት ከተማ ውስጥ የመንግሥት ኃይሎች የወለጋውን ጭፍጨፋ በተቃወሙ ዜጎች ላይ በወሰዱት እርምጃ ከስምንት እስከ 12 የሚገመቱ ንጹሐን ሰዎች መገደላቸውን የዓይን እማኞች ለዶይቼ ቬሌ ተናገሩ። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በበኩሉ ከሰልፉ ጋር በተያያዘ አባላቱ መታሰራቸውን አመልክቷል።

https://p.dw.com/p/4DdXz
Äthiopien | Bürgerkrieg | Tigray | Shewa Robit
ምስል Maria Gerth-Niculescu/DW

ሸዋሮቢት ላይ ሰዎች መገደላቸው

ሰኔ 11/2014 ዓ ም በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ በንጹሐን ላይ የደረሰውን ጭፍጨፋ ተከትሎ በተለያዩ አንዳንድ የአማራ ክልል አካባቢዎች ድርጊቱን የሚያወግዙ ሰልፎች ሲካሄደ ሰንብተዋል። አንዳንድ ሰልፎች ደግሞ ኃይል በተጨመረበር ሁኔታ በፀጥታ ኃይሎች እንዳይካሄዱ ተደርገዋል። ባለፈው ሳምንት መጨረሻም በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሸዋ ሮቢት ከተማ በተመሳሳይ የወለጋውን ጭፍጨፋ በመቃዎም ሰላማዊ ሰልፍ መደረጉንና በሰላም መጠናቀቁን አንድ የከተማዋ ነዋሪ አመልክተዋል፡፡ ሆኖም ከሰልፉ በኋላ ሰልፉን አስተባብረዋል ተብለው የታሰሩ ወጣቶች እንዲፈቱ የመንግሥት አካላት ቢጠየቁም ጉዳዩ በፍርድ ቤት መጠናቀቅ አለበት የሚል ምላሽ በመስጠታቸው  በነዋሪዎችና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ሕይወት መጥፋቱን እኝሁ የዓይን እማኝ ለዶይቼ ቬሌ አስረድተዋል፡፡ የዓይን እማኙ ባለፈው ዓርብ በተፈፀመው  በዚሁ ጥቃት ከሰባት እስከ ስምንት የሚገመቱ ሰዎች መገደላቸውን አረጋጫለሁ ይላሉ።  ሌላው የሸዋ ሮቢት ነዋሪም ሰልፉ በመልካም ሁኔታ መካሄዱን አስታውሰው ሆኖም የታሰሩ ወጣቶች ይፈቱልን በሚል በተፈጠረው አለመግባባት ወደ 12 ሰዎች ተገድለዋል ባይ ናቸው። የአማራ ብሔራ ንቅናቄ (አብን) የብሔራዊ ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር ቴዎድሮስ ተክለማሪያም ሸዋ ሮቢት ከተማ ውስጥ ከነበረው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ አመራሮቹና አባለቱ መታሰራቸውንና ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት እስከ ዛሬ  ከቀኑ 9 ሰዓት ድረስም አልተፈቱም ብለዋል። የችግሩን መነሻና በሁለቱም አካላት በኩል የደረሰውን ጉዳት እንዲያስረዱን ለሸዋ ሮቢት ከተማ ሰላምና ፀጥታ ኃላፊ ለአቶ እንዳለ ገብረመድህንን ደውለን መረጃ እንደሌላቸው አመልክተዋል። ለተጨማሪ አስተያየት ለአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊና ለሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ብንደውልም ስላካቸው አይነሳም፣ የሰሜን ሸዋ ዞን ሰላምና ፀጥታ ኃላፊ ደግሞ ጉዳዩ የሸዋ ሮቢት ከተማ አስተዳደርን እንደሚመለከት ገልፀውልናል፣ የሸዋሮቢት ከተማ ከንቲባ ደግሞ ስልካቸው ዝግ ነው።

ዓለምነው መኮንን 

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ