1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለዲያስፖራው በሀገሩ መዋለ ንዋይ ማፍሰስ ቀላል ነውን?

ልደት አበበ
ዓርብ፣ ግንቦት 16 2016

እንደ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሌሎች በውጭው ሀገራት የሚኖሩ አፍሪቃውያንም ሠርተው በሚያገኙት ገንዘብ ሀገራቸው ላይ መዋለ ንዋይ ለማፍሰስ ሲጥሩ ይስተዋላል። ነገር ግን ይህ ቀላል ነውን?

https://p.dw.com/p/4gDke
ኢትዮጵያውያን በጀርመን
ኢትዮጵያውያን በጀርመንምስል Endalkachew Fekade/DW

ለዲያስፖራው በሀገሩ መዋለ ንዋይ ማፍሰስ ቀላል ነውን?

እንደ የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት( IOM) መረጃ  11 ሚሊዮን የሚሆኑ አፍሪቃዊ ተወላጆች በአውሮፓ ብቻ ይኖራሉ። ይህ በጎርጎሮሲያኑ 2020 ዓ ም የተደረገ ጥናት ነው።  ከአፍሪቃ ወደ ተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚሄዱ በተለይም ወጣት አፍሪቃውያን ሀገራቸውን ያሉ ቤተሰቦችን ከመርዳት ባለፈ ባጠራቀሙት ገንዘብ ሀገራቸው ላይ መዋለ-ንዋይ ለማፍሰስ ፍላጎት ያሳያሉ። አፍሪካ ውስጥ መዋለ-ንዋይ ማፍሰስ ቀላል ነውን? ዶይቸ ቬለ የተለያዩ በውጭው ሀገራት የሚኖሩ አፍሪቃውያንን ተሞክሮ ጠይቋል። 
በውጭው ሀገር የሚኖሩ አፍሪቃውያን የሚሉትን ከመስማታችን በፊት በ 77 ከመቶው የእንግሊዘኛ ክፍል ዝግጅት የፌስ ቡክ ገጽ ላይ በጽሑፍ አስተያየታቸውን ያካፈሉንን እናሰማችሁ።
ንፎር ዊስደም ፤  "ዲያስፖራ ያሉ ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው ትንንሽ ድርጅቶችን ከፍተው ልንቀጥርበት የምንችልበት ሁኔታ ቢያመቻቹ እና ጥሬ ሀብታችንን ተጠቅመን እራሳችን የሚያስፈልጉንን ነገሮች ማምረት አለብን።" 
ሆኖራሪ ዱከ ፤  "ጦርነት፣ አለመረጋጋት እና የመንግስት ፖሊሲዎች ካሜሩን ውስጥ ለንግድ ሥራ ምቹ እንዳይሆኑ አድርጓል።" 
ሮዤ ሙዩንዛ ፤  «የፖለቲካ አለመረጋጋት እና አምባገነኖች ባሉባቸው ሀገራት ማንም ኢንቨስት ማድረግ አይችልም።»

የዲያስፖራ ፈተናዎች

ቤቲ ያውሰን መቀመጫዋን በታላቋ ብሪታንያ ያደረገች ጋናዊ ጋዜጠኛ ናት። ከሀገር ከወጣች ሦስት ዓመት ሆናት። በጋና የሸክላ ሥራ ከፍታ ነበር። ነገር ግን ከአንድ ዓመት በፊት ለማቆም ተገዳለች፣ ለዚህ አንዱ ምክንያት  በጋና ያለው የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ነው ትላለች። ሌላው ደግሞ « አዎ አፍሪቃ ውስጥ የሰው ኃይል በጣም ርካሽ ነው። ምክንያቱም ውጪ ሀገር እንደሚከፈለው አይደለም።  ነገር ግን ቦታው ላይ የሚያስፈልጉ ነገሮች ካልተገኙ ቢዝነሱን ሊንዱ ይችላሉ።»

ሳሙና
የሳሙና ማምረት ስራ ፈጠራ በካሜሮን ምስል DW

በታላቋ ብሪታንያ የጤና ባለሞያ የሆነችው ናድያ እስካሁን ሀገሯ ካሜሮን ላይ የሞከረችው ነገር የለም። ነገር ግን « የማቃቸው በርካታ የሞከሩ ሰዎች አሉ። አንዳንዶቹ ተስፋ ቆርጠው ትተውታል» ትላለች። ለዚህም በምክንያትነት የምታስቀምጣቸው ሦስት ነገሮች አሉ። « አንደኛ ወደ ሀገር ቤት ሄደሽ መዋለ ንዋይ ማፍሰስ ከፈለግሽ አንድ ሰው ያስፈልግሻል። ሌላ ሊረዳሽ ፣ ሊያመቻችልሽ የሚችል ሰው የሚያውቅ! ሁለተኛ ደግሞ መረጃ ነው። ካሜሪን ውስጥ መረጃ በቀላሉ አይገኝም። የምታገኚው መረጃ ከሦስት፣ አምስት ፣ ስድስተኛ  ወገን ነው።  ይህ መስተካከል ያለበት እና ለሁሉም በይፋ መሰጠት ያለበት ነገር ነው። ሰዎች እንዲገባቸው ሆኖ መቅረብ ይኖርበታል። ሦስተኛ ደግሞ ግብር ነው። ካሜሮን ለምሳሌ ቢዝነዝ መጀመር ለሚፈልግ ሰው ከፍተኛ የሆነ ግብር ነው የምታስከፍለው።»

ሆነስት ሮድጊ  እዚህ ጀርመን ሀገር የሚኖር የዚምባብዌ ተወላጅ ሥራ ፈጣሪ ነው። በሀገሩ ብዙ  መዋለ ንዋይ እንዳፈሰሰ ይናገራል። ይህን ሲያደርግ የገጠመው ትልቁ ፈተና ምን ይሆን? « ፈተናዎቻችን ከኬፕታውን እስከ ካይሮ ተመሳሳይ ይመስላሉ። አንድን የንግድ ተቋም ለማስመዝገብ ያለው ደንቡ ፣ አሠራሩ፣ ሂደቱ  የተወሳሰበ ነው። ናድያ እንዳለችው መረጃ እንኳን በቀላሉ ኦንላይን አይገኝም። ይህ ደግሞ ለሙስና በር ይከፍታል። ሌላው ደግሞ ውጭ ሀገር ሆኖ አፍሪቃ ውስጥ ብድር ማግኘት በጣም ከባድ ነው።  ሲቀጥል ውጭ ሀገር ተሆኖ በቦታው ላይ ያለውን የሸማቹን ፍላጎት መረዳት ከባድ ነው። ቤቲ የገጠማትም ይህ ይመስለኛል።  እና ደግሞ ቦታው ላይ ያለ ፣ ታማኝ እነዚህን መረጃዎች መስጠት የሚችል ሰው ማግኘት ከባድ ነው። » 

በኢትዮጵያስ መዋለ ንዋይ ማፍሰስ ለሚፈልጉ ዲያስፖራዎች ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?

በአዲስ አበባ በፋይናንስ ዘርፍ ተሰማርቶ የሚሰራው ወርቁ የታዘበው አለ። «በዋናነት የመንግሥት ፈፃሚ የሚባሉ አካላት ቀልጣፋ እና ከሙስና የፀዳ አገልግሎት ስለማይሰጡ እሱ ችግር አለ። ሁለተኛ ሰዎች መጥተውም እዚህ ኢንቨስት ለማድረግ የመሰረተ ልማት ችግር አለ። በዛ ልክ እዚህ መጥተው የሚሠሩበትን ዘርፍ መርጦ እና ወስኖ አለመምጣት ነው። ሲቀጥል ሥራውን በውጪው ዐይን መመልከት! ማለትም የሚጠብቁት ነገር በውጭው ባለው ነባራዊ ሁኔታ ልክ ይሆንና እዚህ ሲመጡ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ተቃራኒው ስለሚሆን ያለ መመቸት ሁኔታ አለ። እንደገና ደግሞ እዚህ ያለው የፀጥታ፤ የሰላሙ ሁኔታ ጋባዥ አይደለም። በአብዛኛው ቦታ በኢንቨስትመንት ሥም የገቡ ንብረቶች ይወድማሉ፣ ይሰረቃሉ፤ ይቃጠላሉ። እና ስጋት አለ። በመላው ሀገሪቱ በሚባል ሁኔታ ከፍተኛ የሆነ ሕገ ወጥነት አለ።»

አትላንታ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን
አትላንታ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የርዳታ ማሰባሰቢያ ዲያደርጉምስል Tariku Hailu/DW

ከግብር ክፍያ አንፃር ግን ወርቁ ኢትዮጵያ ውስጥ ለዲያስፖራ የተሻለ ሁኔታ አለ ይላል።« አሁን ባለው ሁኔታ በሀገር ውስጥ ካሉ ባለ ሀብቶች በተሻለ  ዲያስፖራው የተሻለ መብት እና ከግብር ነፃ የሆን እድል አለው። የግብር ጫናው ከፍተኛ ቢሆንም ከሀገር ውስጥ ነጋዴዎች በተሻለ እነሱን የሚያበረታታ ነው»

የአፍሪቃ ሀገራት መንግሥታት  ምን ቢያደርጉ ጥሩ ነው?  

ጋናዊቷ ናዲያ ሶሻል ሚዲያውን መረጃ ለማሰራጨት ቢጠቀሙ ጥሩ ነው ትላለች።« ዛሬ ሶሻል ሚዲያን ለተለያዩ ነገሮች መጠቀም ይቻላል። ተጽዕኖ ፈጣሪዎች መረጃውን እንዲያሰራጩ መጠቀም ይቻላል። ይኼውላቹሁ ንግድ መጀመር ከፈለጋቹህ እነዚህ ነገሮች አሉ። ብለው መረጃውን ሊያሰራጩ ይችላሉ።  ሌላው ወጣት መዋለ ንዋይ አፍሳሾችን ለማበረታታት ፕሮጀክት ለይቶ ለዛ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ መስጠት ሊሆን ይችላል። »

«አፍሪቃ በአቅሟ ያለውን ነገር ሁሉ  ለመዋለ ንዋሽ አፍሳሾች የሚስብ ማድረግ አለባት የሚለው ሆነስት ይህ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት እና ሌሎች ጥቅሞችም እንደሚረዳ ይናገራል። ስለሆነም መሻሻል የሚገባቸው ነገሮች ላይ ማተኮር ያስፈልጋል ባይ ነው።« ፖሊሲ አውጪዎች ለምሳሌ አላስፈላጊ የሆኑ ቢሮክራሲዎችን ሊቀንሱ ይችላሉ። ሰዎች አንድ ቦታ ጉዳያቸውን የሚያስጨርሱበት ሁኔታ ያስፈልጋል። ሩዋንዳ ጥሩ ምሳሌ ናት። እያንዳንዱን የህግ ፍቃድ በአንድ ጣሪያ ስር በኦንላይን እንዴት ማግኘት እንደሚቻል አሳይታናለች። ለዛ ሩዋንዳ ድረስ መሄድ አያስፈልግም። ይህ ሩዋንዳውያን አፍሪቃ ውስጥም የሚቻል መሆኑን አድርገው ዐሳይተውናል።» 

ናይጄሪያ ኒጀር ድንበር ላይ
ናይጄሪያ ኒጀር ድንበር ላይ እቃ የጫኑ የጭነት መኪናዎችምስል Mohammed Babangida/AP/picture alliance

ጋናዊቷ ቤቲም የምታክለው የመፍትኼ ሀሳብ አለ።« ሀገር ቤት መዋለ ንዋይ ማፍሰስ ከፈለግሽ ፣ ሀሳቡን እንኳን ከማፍለቅሽ በፊት መጀመሪያ ቢዝነዙ በማህበረሰቡ ላይ ምን አይነት ተፅዕኖ ይፈጥራል የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል።»  
የፋይናንስ ዘርፍ ባለሞያ የሆነው ወርቁ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ አዋጪ ያልሆነ የሥራ ዘርፍ የለም ባይ ነው።

ዲያስፖራው በየትኛው የስራ ዘርፍ ቢሰማራ ጥሩ ነው? 

« በሁሉም ዘርፍ በሚባል ደረጃ ከፍተኛ የሆነ የፍላጎት እና አቅርቦት ያለመመጣጠን አለ። ከመሰረታዊ ፍላጎቶች አንስቶ የቅንጦት እስከሚባሉት። ኢትዮጲያ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ግንባታ አለ። በግንባታ ዘርፍ መሰማራት ይቻላል። የአምራች ዘርፉም ትልቅ ነው፣ ፋይናንስ እና ቴክኖሎጂን የሚያገናኙት ፊንቴክ የተባሉ ድርጅቶች አሉ ፤ እነሱ ቢመጡ ያዋጣል። የኮምፒውተር ሳይንስ ባለሞያዎች ቢመጡ  ትልቅ ገበያ ይኖራቸው።…» ይላል ወርቁ።

ልደት አበበ

ማንተጋፍቶት ስለሺ