1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እንወያይ፤ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ሚና ከየት ወዴት?

እሑድ፣ ጥር 26 2016

በዉጭ የሚኖረዉ ኢትዮጵያዊና ትዉልደ ኢትዮጵያዊ (ዲያስፖራ) በኢትዮጵያ ፖለቲካ፤ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ፤ ከፍተኛ ሚናን እንደሚጫወት ይታወቃል። አሁን አሁን ግን አብዛኛዉ ዲያስፖራ በዘላቂ የአገሪቱ ጥቅሞች ላይ አንድ ላይ መቆሙ ቀርቶ፤ ተጻራሪና ግዚያዊ የሆኑ የቡድን ፍላጎቶችን ይዞ በየፊናው ቆሞ መታየቱ የተለመደ ሁኗል። ችግሩ ምን ይሆን?

https://p.dw.com/p/4c1TH
ኢትዮጵያዉያን ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድን በፍራንክፈርት ስቴድየም ሲቀበሉ - 31.10.2018
ኢትዮጵያዉያን ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድን በፍራንክፈርት ስቴድየም ሲቀበሉ - 31.10.2018ምስል DW/W. Tesfalem

እንወያይ፤ በአንድ ላይ ቆመው ለኢትዮጵያ ይጮሁ የነበሩ ዲያስፖራዎች ዛሬ የት ናቸዉ?

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ሚና ከየት ወዴት?

በዉጭ ዓለም የሚኖረዉ የኢትዮጵያዊ እና ትዉልደ ኢትዮጵያዊ (ዲያስፖራ) በኢትዮጵያ ፖለቲካ፤ ኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ሚናን እንደሚጫወት ይታወቃል። በኢኮኖሚዉ ገንዘቡን ወደ አገር ቤት በመላክ(በሪሚታንስ)በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ ያስገባል፤ ከፍተኛ ድጋፍም አድርጓል፤ እያደረገም ነዉ። በፖለቲካዉ ረገድም በአገሪቱ ፖለቲካዊ ለዉጥ እስከ ማምጣት የደረሰ ሚና ሲጫወት ታይቷል። በማኅበራዊም ደረጃም ቢሆን በተለያዩ ሃገራት የሚኖረዉ፣ ዲያስፖራ ከግለሰብ አንስቶ በልዩ ልዩ ተቋማት በመደራጀት የጤና ተቋማትን እና ትምህርት ቤቶችን፤ አነስተኛ እና መለስተኛ የተባሉ የማምረቻ ኩባንያዎችን፤ ሆቴሎችን፤ትምህርት ቤቶችን፤ የጤና ተቋማትን እና የመሳሰሉትን በመገንባት ከፍተኛ ድርሻ አለዉ። የዛሬ ስድስት ዓመት በኢትዮጵያ የተካሄደዉን ለዉጥ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ባስተላለፉት ጥሪ መሰረት በአስር ሽዎች የሚቆጠሩ ዲያስፖራዎች ወደ ሃገር ቤት ገብተዉ፤ መዋለንዋይን አፍስሰዋል፤ ኢንቬስትመንቶችን አካሂደዋል።

በጋራ ቆመው ለኢትዮጵያ ይጮሁ የነበሩ ወገኖች ዛሬ የት ናቸዉ?

ይሁንና ከስሜን ኢትዮጳያው ጦርነት በተለይም  በአማራው ክልል ከተቀሰቀሰው ተቃውሞና ጦርነት ወዲህ ሁኔታዎች መለወጣቸው ገህድ ወቷል።  በአንድ ላይ ቆመው ለኢትዮጵያ ይጮሁ የነበሩ ወገኖች ዛሬ ተክፋፍለውና አንዳንዴም ተጻረው ቆመው ነው የሚታዩት። በእነዚህ ቡድኖች አንጻር የተቋቋሙ የሚዲያ አውታሮችም ከሀገራዊ አጀንዳዎችና የጋራ እሴቶች ይልቅ በእርስ በእርስ ፍትጊያና መወነጃጀል ተጠምደው ይታያሉ። በዘላቂ የአገሪቱ ጥቅሞች ላይ አንድ ላይ መቆሙ ቀርቶ ተጻራሪና ግዚያዊ የሆኑ የቡድን ፍላጎቶችን ይዞ በየፊናው ዉዝግብ መታየቱ የተለመደ ሁኗል። ይህ አክሄድና መከፋፈል ግን ዓለማቀፉን ህብረተስብ ለውዥምበር ከመዳረግ አልፎ  ውጤት ማስገኘቱን ብዙዎች ይጠራጠራሉ።  በአገሩ ጉዳይ በርካታ አስተጽዋጾ ሲያደርግ የነበረውና ብዙም የሚጠበቅበት የኢትዮያ ዲያስፖራ እንዴት እንዲህ ሊከፋፈልና ተዋጾው ሊቀንስ፤ ተሰሚነቱም ሊቀንስ፤ አንዳንዶች እንደሚሉትም አፍራሽ  ሊሆን ቻለ? የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ሚና ከየት ወዴት? ችግሩ ምን ይሆን? የእንወያይ ዋናው መነጋገሪያ አጀንዳ ነው።

በዉይይቱ ሃሳባቸዉን እንዲያካፍሉን የጋበዝናቸዉ፤

አቶ ዳንኤል መስፍን፤ በኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት፤ የዲያስፖራ የመረጃ እና ጥናት ተጠባባቂ  ዳይሬክተር ፤

ዶክተር ፀጋዬ ደግነህ፤ ከበርሊን ጀርመን የኤኮኖሚና የአስተዳደር ምሁር፤ በኢትዮጵያም በዲያስፖራ ዘርፍ ለትዉልድ አርአያ የሚሆን አስተዋፅኦ በማድረጋቸዉ በ 2015 ጳጉሜ ወር ላይ የዓመቱ በጎ ሰዉ በመሆን የተሸለሙ እና  ወደ ኢትዮጵያ እዉቀት ማስተላለፍ ዘርፍ የሚሰሩ።

አቶ በትሩ ገብረግዚአብሔር  በሰሜን አሜሪካ አስር የተለያዩ ድርጅቶች በጋራ የተሰባሰቡበት የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ማኀበራት ጉባኤ(ኢሕማጉ) አመራር አባል፤

እንዲሁም፤ አቶ አንዷለም ታደሰ ከስዊድን ወደ ኢትዮጵያ ደብብ ክልል ወደትዉልድ ቀያቸዉ፤ ወላይታ ተመልሰዉ ከአራት ዓመት ኑሮ በኋላ አሁን በስደት ወደነበሩበት ወደ ስቶክሆልም ስዊድን የተመለሱ የጤና ምሑር ናቸዉ። ተወያዮች ሃሳባችሁን ለማካፈል በዶቼ ቬለ የእንወያይ መድረክ በመቅረባቸዉ እናመሰግናለን።

ሙሉ ዉይይቱን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ተከታትለዉ፤ እስሮም አስተያየቶን እንዲጽፉ እንጋብዛለን!

አዜብ ታደሰ