ዜና | DW
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ
ማስታወቂያ
ማስታወቂያ

ዜና | 29.01.2020 | 00:00

አዲስ አበባ-የታገቱ ተማሪዎች ወላጆች

ከደንቢዶሎ ወደየቤተሰቦቻቸዉ ሲጓዙ ባለፈዉ ሕዳር የታገቱት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ጉዳይን የሚያጠራ ሶስት ቡድን መመስረቱን የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት አስታወቁ።የጠቅላይ ሚንስትር ቃል አቀባይ ፅሕፈት ቤት፣የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እና የሳይንስና ከፍተኛ ትምሕርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ተማሪዎቹ በታገቱበት አካባቢ ታጣቂ አማፂያን መሸመቃቸዉን አረጋግጠዋል።የፌደራሉ መንግስት ባለስልጣናት ስለተማሪዎቹ መታገት በይፋ መግለጫ ሲሰጡ የዛሬዉ ሁለተኛቸዉ ነዉ።በተያያዘ ዜና ከታጋቱት ተማሪዎች ቢያንስ የሶስቱ ወላጆች መንግስት ባደረገላቸዉ ጥሪ መሰረት ከያሉበት አዲስ አበባ መግባታቸዉን አስታዉቀዋል።በስልክ ያነጋገርናቸዉ አንድ አባት እንዳሉት አዲስ አበባ እንዲገቡ ከመጠራታቸዉ በስተቀር የተጠሩበትን ምክንያት በዝርዝር አያዉቁትም።ከደቡብ እና ሰሜን ጎንደር ተጉዘዉ ዛሬ አዲስ አበባ የገቡት ወላጆች እስከ ማምሻዉ ድረስ ያነጋገራቸዉ የመንግሥት ባለስልጣን እንደሌለ በስልክ አረጋግጠዉልናል።የታገቱት ተማሪዎቹ እንዲለቀቁ በአደባባይ ሰልፍና በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚደረገዉ ጥሪና ግፊት እንቀጠለ ነዉ።

አዲስ አበባ-የሽግግር መንግሥት ጥያቄ

ኢትዮጵያ ዉስጥ አዲስ «የእርቅና የሽግግር» መንግሥት እንዲመሰረት ሶስት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠየቁ።«አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት» የተባለዉ ስብስብ የሚያስተናብራቸዉ የፖለቲካ ማሕበራት መሪዎች እንደሚሉት ኢትዮጵያ አሳሳቢ የብሔራዊ ደሕነት ሥጋት ዉስጥ በመሆኗ ለመጪዉ ነሐሴ የተያዘዉ የምርጫ ጊዜ መራዘም አለበት ።በንባብ የተሰማዉ የፓርቲዎቹ መግለጫ በስልጣን ላይ ያለዉ መንግስት ሐገሪቱን ወደ ዴሞክራሲ ለማሸጋገር ብቃትም ፍላጎትም የለዉም ብሏል።ተቃዋሚ ፖለቲከኞቹ እንደሚሉት የምርጫዉ ጊዜ መወሰን ያለበት በመንግስትና በፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር እንጂ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መሆን አይገባዉም።

ሐረር-መንገዶች ባንኮችና ሱቆች ተዘጉ

ባለፈዉ ጥር 10ና 11 የከተራና የጥምቀት በዓል ሲከበር በተቀሰቀሰ ግጭት በርካታ ንብረት የወደመባት የሐረር ከተማ ዛሬ ደግሞ እንቅስቃሴዋ ታጉሎ ኦና ዉላለች። የከተማይቱ ነዋሪዎች እንደሚሉት ጥንታዊቱ ከተማ ዛሬ የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጦባት፣ ሱቆች፣ ባንኮችና ሌሎች አገልግሎት መስጪያ ተቋማት ተዘግተዉባት ነዉ የዋለችዉ።ሐረርን ከድሬዳዋ ጋር የሚያገናኘዉ አዉራ መንገድም ደንገጎ በተባለዉ አካባቢ መዘጋቱን የዓይን ምስክሮች አስታዉቀዋል።ከጂጂጋ ወደ አዲስ አበባ ይጓዙ የነበሩ የመንገደኛ አዉቶብሶች ባቢሌ ላይ መቆማቸዉም ተነግሯል።የሐረሪ ክልላዊ መንግሥት የፖሊስ ኮሚሽነር ረመዳን ዑመር አወዳይና ሐረማያ አካባቢ መንገድ መዘጋቱን መስማታቸዉን አስታዉቀዋል። ሐረር ከተማ ዉስጥም መንገድ ለመዝጋት የተደረገ ሙከራን ፖሊስ ማክሸፉን ኮሚሽነር ረመዳን አስታዉቀዋል።የድሬዳዋዉ ወኪላችን መሳይ ተክሉ የምስራቅ ሐረርጌ ፖሊስ ኃላፊዎችን ለማነጋገር ያደረገዉ ሙከራ ግን አልተሳካለትም።

ኦይቻ-የኮንጎ አማፂያን 15 ሰዉ ገደሉ

ምስራቃዊ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ዉስጥ የሸመቁ ታጣቂዎች ትናንት በከፈቱት ጥቃት 15 ሰዉ ገደሉ።ቤኒ የተባለችዉ የምሥራቃዊ ኮንጎ ግዛት ባለስልጣናት እንዳስታወቁት ማንነታቸዉን በዉል ያልጠቀሷቸዉ አማፂያን በከፈቱት ጥቃት ከገደሏቸዉ ሰዎች 14 የአንድ አካባቢ ነዋሪዎች ናቸዉ።የቤኔ ግዛት አስተዳዳሪ ዶናት ኪብዋና እንዳሉት 15ኛዉ ሟች ሌሎቹ ሰዎች ከተገደሉበት ራቅ ያለ መንደር የሚኖሩ ቄስ ነበሩ።ለበርካታ ዓመታት በአማፂያን እና በወሮበሎች ጥቃት በርካታ ሰዎች የሚገደሉባት ምሥራቃዊ ኮንጎ ካለፈዉ ሕዳር ወዲሕ የተገደሉባት ሰላማዊ ሰዎች ቁጥር ከመቶ በልጧል።

የተለያዩ-የትራምፕ ዕቅድና ድጋፍና ተቃዉሞዉ

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የፍልስጤም እስራኤሎችን የዘመናት ጠብ ለማስወገድ ይረዳል ያሉት የሁለት መንግስታት ዕቅድ ሌላ ዉዝግብ ቀስቅሷል።ትራምፕ «አዲስ» ያሉት ዕቅድ ምዕራባዊ እየሩሳሌምን ጨምሮ እስራኤል እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር በ1967ና ከዚያ በኋላ በኃይል የያዘችዉን የፍልስጤም ግዛት በሙሉ የእስራኤል ግማደ ግዛት አካል የሚያደርግ ነዉ።ዕቅዱን የእስራኤል መንግስት ሲቀበለዉ ፍልስጤሞች ነቅፈዉታል።ፕሬዝደንት ትራምፕ ዓለም አቀፍ ስምምነትን ጥሰዉ እየሩሳሌም የእስራኤል ርዕሰ-ከተማ እንደሆነ ዕዉቅና ከሰጡ ከ2017 (እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር) ጀምሮ ከትራምፕ መስተዳድር ጋር ግንኙነት ያቋረጠዉ የፍልስጤም መስተዳድር ዕቅዱን ዉድቅ አድርጎ ሌሎች ሐገራት ለፍልስጤም መንግስትነት ዕዉቅና እንዲሰጡ ጠይቋል።

የትራምፕ ዕቅድና መካከለኛዉ ምሥራቅ

የአረብ ሊግ ዋና ፀሐፊ አሕመድ አቡይ ጋይት ዕቅዱን «የፍልስጤሞችን መሠረታዊ መብት የሚጥስ» ብለዉታል።ሳዑዲ አረቢያ ከፍልስጤሞች ጎን እንደምትቆም ንጉሷ ሲያረጋግጡ፣ግብፅ ቀዝቀዝ ብላ፣ ፍልስጤምና እስራኤል የአሜሪካኖችን ዕቅድ በጥሞና አንዲያጤኑት መክራለች።ሶሪያ ዕቅዱን «አረቦችን ለማጥፋት» የተሸረበዉ ሴራ አካል ብላዋለች።ባሕሬን እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ዕቅዱን ደግፈዉታል።የአረብ ሊግ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች በዕቅዱ ላይ ለመነጋገር የፊታችን ቅዳሜ ይሰበሰባሉ።ከተቀሩት ሐገራት ቱርክ ዕቅዱን ለመካከለኛዉ ምሥራቅ ሰላም የማይፈይድ ስትለዉ፣ የኢራን ላዕላይ መሪ አያቶላሕ ዓሊ ኻሚኒ «የአሜሪካ ዲያቢሎሳዊ መርሕ ዉጤት» ብለዉታል። የአዉሮጳ ሕብረት የዕቅዱን ዝርዝር አጥንቶ አቋሙን እንደሚያሳዉቅ ሲገልጥ፣ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን እንደሚሉት ዕቅዱ «ፍፁም ያልሆነ ግን ተስፋ ሰጪ።» ነዉ።

የተለያዩ፟-የኮሮናተሕዋሲ ስርጭት ና ጥንቃቄዉ

ቻይና እና ከቻይና የተዛመተዉን የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭትን ለመከላከል አየር መንገዶች ከእና ወደ ቻይና የሚያደርጉትን ጉዞ አቋረጡ። የየሐገሩ መንግስታት ዜጎቻቸዉን ከቻይና ሲያሸሹ፣ከቻይና ወደየ ሐገራቸዉ የሚገቡ ተጓዦችን ደግሞ በተገለለ ሕክምና ማዕከላት እያኖሩ ነዉ።እስከ ዛሬ ቀትር ድረስ የአዉሮጳና የሰሜን አሜሪካን ጨምሮ ስምንት አየር መንገዶች ከእና ወደ ቻይና የሚያደርጉትን መደበኛ በረራ አቋርጠዋል።ቻይናን የምታጎራብተዉ ካዛክስታን በበኩሏ ወደ ግዛትዋ ለሚጓዙ ቻይናዉያን የመግቢያ ፈቃድ ወይም ቪዛ መስጠት አቁማለች።ሁለቱን ሐገራት የሚያገናኙ የባቡር መስመሮችን ከመጪዉ አርብ ጀምሮ፣ከና ወደ ቻይና የሚደረጉ የአዉሮፕላን በረራዎችን ደግሞ ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ ለማቋረጥ ወስናለች።ከና ወደ ቻይና በየቀኑ ስድስቴ የሚበረዉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን በረረዉን ለማቋረጥ ስለማቀድ አለማቀዱ እስካሁን በይፋ ያለዉ ነገር የለም።

ኮሮናተሕዋሲ-ያደረሰዉ ጉዳት

ባለፈዉ ታሕሳስ ማብቂያ ዉሐን በተባለችዉ የቻይና ግዛት የመጀመሪያዉን ሰዉ የለከፈዉ ገዳይ ተሕዋሲ እስከ ዛሬ ድረስ 132 ሰዎች ገድሏል።ከ6ሺሕ 2 መቶ የሚበልጡ ሰዎች ተለክፈዋል።ጉንፋን መሰል ስሜትና ምልክት ያለዉ በሽታ እስካሁን ድረስ መድሐኒትም ሆነ ክትባት አልተገኘለትም።የቻይና ሳይንቲስቶች የመከላከያ ክትባት ለማግኘት እየጣሩ መሆኑን የተላላፊ በሽታ ከፍተኛ ሳይንቲስት ሊ ላንዩዋን ዛሬ አስታወቀዋል።«ክትባት ለማምረት የተወሰነ ሒደት ያስፈልጋል።ከበሽተኛ ከተወሰደ ሕዋስ ዝርያዉን እያዳበርን ነዉ።ለክትባት የሚያስፈልገዉን ንጥረ ነገር ለማግኘት አንድ ወር ያስፈልጋል።ከተገኘ በኋላ ለመሞከር ቢያንስ ግማሽ ወር፣የመጨረሻዉን ዉጤት ለማፅደቅ ደግሞ ከአንድ ወር እስከ አንድ ወር ከ15 ቀን ተጨማሪ ጊዜ ይጠይቃል።»የቻይና ፕሬዝደንት ሺ ዢፒንግ ተሕዋሲዉን የመቆጣጠሩን ጥረት «ከባድና ዉስብስብ» ብለዉታል።ተሕዋሲዉ በ19ኝ ሐገራት ተዛምቷል።NM/EB